ምዕራፍ 47

1 ለመዘምራን አለቃ፤ የቆሬ ልጆች መዝሙር። 1 አሕዛብ ሁላችሁ፥ እጆቻችሁን አጨብጭቡ፥ በደስታ ቃልም ለእግዚአብሔር እልል በሉ።
2 እግዚአብሔር ልዑል ግሩምም ነውና፥ በምድር ሁሉ ላይም ታላቅ ንጉሥ ነውና።
3 አሕዛብን ከእኛ በታች፥ ወገኖችንም ከእግራችን በታች አስገዛልን።
4 ለርስቱ እኛን መረጠን፥ የወደደውን የያዕቆብን ውበት።
5 አምላክ በእልልታ፥ እግዚአብሔር በመለከት ድምፅ ዐረገ።
6 ዘምሩ፥ ለአምላካችን ዘምሩ፤ ዘምሩ፥ ለንጉሣችን ዘምሩ።
7 እግዚአብሔር ለምድር ሁሉ ንጉሥ ነውና፤ በማስተዋል ዘምሩ።
8 እግዚአብሔር በአሕዛብ ላይ ነገሠ፤ እግዚአብሔር በቅድስናው ዙፋን ይቀመጣል።
9 የምድር ኃይለኞች ለእግዚአብሔር ናቸውና የአሕዛብ አለቆች ወደ አብርሃም አምላክ ተሰበሰቡ፤ እርሱንም ከፍ ከፍ አደረጉት።