ምዕራፍ 108
1 የዳዊት የምስጋና መዝሙር። 1 ልቤ ጽኑ ነው፥ አቤቱ፥ ልቤ ጽኑ ነው፤ እቀኛለሁ በክብሬም እዘምራለሁ።
2 በገና ሆይ፥ ተነሥ፥ መሰንቆም፤ እኔም ማልጄ እነሣለሁ።
3 አቤቱ፥ በአሕዛብ መካከል አመሰግንሃለሁ፥ በወገኖችም መካከል እዘምርልሃለሁ፤
4 ምሕረትህ በሰማይ ላይ ታላቅ ናትና፥ እውነትህም እስከ ደመናት ድረስ ነውና።
5 አቤቱ፥ በሰማያት ላይ ከፍ ከፍ በል፥ ክብርህም በምድር ሁሉ ላይ ትሁን።
6 ወዳጆችህ ይድኑ ዘንድ፤ በቀኝህ አድን አድምጠኝም።
7 እግዚአብሔር በቅድስናው ተናገረ። ደስ ይለኛል፥ ሴኬምንም እካፈላለሁ፥ የሱኮትንም ሸለቆ እሰፍራለሁ።
8 ገለዓድ የእኔ ነው ምናሴም የእኔ ነው፤ ኤፍሬም የራሴ መጠጊያ ነው። ይሁዳ ንጉሤ ነው።
9 ሞዓብ መታጠቢያዬ ነው፥ በኤዶምያስ ላይም ጫማዬን እዘረጋለሁ፤ ፍልስጥኤም ይገዙልኛል።
10 ወደ ጽኑ ከተማ ማን ይወስደኛል? ማንስ እስከ ኤዶምያስ ይመራኛል?
11 አቤቱ፥ የጣልኸኝ አንተ አይደለህምን? አምላክ ሆይ፥ ከሠራዊታችን ጋር አትወጣም።
12 በመከራችን ረድኤትን ስጠን፤ የሰውም ማዳን ከንቱ ነው።
13 በእግዚአብሔር ኃይልን እናደርጋለን፤ እርሱም የሚያስጨንቁንን ያዋርዳቸዋል።