ምዕራፍ 10
1 አቤቱ፥ ለምን ርቀህ ቆምህ? በመከራም ጊዜ ለምን ትሰወራለህ?
2 በኃጢአተኛ ትዕቢት ድሀ ይናደዳል፤ ባሰቡት ተንኰላቸው ተጠመዱ።
3 ኃጢአተኛ በነፍሱ ፈቃድ ይወደሳልና፥ ዓመፀኛም ይባርካል።
4 ኃጢአተኛ እግዚአብሔርን አበሳጨው፥ እንደ ቍጣውም ብዛት አይመራመረውም በእርሱ ፊት እግዚአብሔር የለም።
5 መንገዱ ሁሉ የረከሰ ነው፥ ፍርድህም በፊቱ የፈረሰ ነው፥ ጠላቶችንም ሁሉ ይገዛቸዋል።
6 በልቡ ይላል። ለልጅ ልጅ አልታወክም ክፉም አያገኘኝም።
7 አፉ መርገምንና ሽንገላን ተንኰልን የተመላ ነው፤ ከምላሱ በታች ጉዳትና መከራ ነው።
8 በመንደሮች መሸመቅያ ይቀመጣል ንጹሓንን በስውር ይገድል ዘንድ፤ ዓይኖቹም ወደ ድኃ ይመለከታሉ።
9 እንደ አንበሳ በችፍግ ዱር በስውር ይሸምቃል፤ ድሀውን ለመንጠቅ ያደባል፤ ድሀውን ይነጥቀዋል በአሽክላውም ይስበዋል።
10 ድሀ ይዋረዳል፥ ይጐብጣል፤ በኃያላኑም እጅግ ይወድቃል።
11 በልቡም ይላል። እግዚአብሔር ረስቶኛል፤ ፈጽሞም እንዳያይ ፊቱን ሰወረ።
12 አቤቱ አምላክ ሆይ፥ ተነሥ እጅህም ከፍ ከፍ ትበል፤ ድሆችን አትርሳ።
13 ኃጢአተኛ ስለ ምን እግዚአብሔርን አስቈጣው? በልቡ። አይመራመረኝም ይላልና።
14 አየኸው፥ አንተ ክፋትንና ቍጣን ትመለከታለህና በእጅህ ፍዳውን ለመስጠት፤ ድሀ ራሱን ለአንተ ይተዋል፥ ለድሀ አደግም ረዳቱ አንተ ነህ።
15 የኃጢአተኛንና የክፉን ክንድ ስበር፥ የኃጢአቱንም ብድራት ክፈል ሌላ እስከማይገኝ ድረስ።
16 እግዚአብሔር ለዘላለም ይነግሣል፤ አሕዛብ ከምድሩ ይጠፋሉ።
17 እግዚአብሔር የድሆችን ምኞት ሰማ፥ ጆሮውም የልባቸውን አሳብ አደመጠች፥
18 ፍርዱ ለድሀ አደግና ለችግረኛ ይደረግ ዘንድ፥ ሰዎች በምድር ላይ አፋቸውን ከፍ ከፍ ማድረግ እንዳይደግሙ።