ምዕራፍ 142
1 ጸሎት፤ በዋሻ በነበረ ጊዜ፤ የዳዊት ትምህርት። 1 በቃሌ ወደ እግዚአብሔር ጮኽሁ፤ በቃሌ ወደ እግዚአብሔር ለመንሁ።
2 ልመናዬን በፊቱ አፈስሳለሁ፤ መከራዬንም በፊቴ እናገራለሁ።
3 ነፍሴ በውስጤ ባለቀች ጊዜ መንገዴን አወቅሁ፤ በምሄድባት በዚያች መንገድ ወጥመድን ሰወሩብኝ።
4 ወደ ቀኝ ተመለከትሁ አየሁም፥ የሚያውቀኝም አጣሁ፤ መሸሸጊያም የለኝም፥ ስለ ነፍሴም የሚመራመር የለም።
5 አቤቱ፥ ወደ አንተ ጮኽሁ። አንተ ተስፋዬ ነህ፥ በሕያዋንም ምድር አንተ እድል ፈንታዬ ነህ አልሁ።
6 እጅግ ተቸግሬአለሁና ወደ ልመናዬ አድምጥ፤ በርትተውብኛልና ከሚያሳድዱኝ አድነኝ።
7 አቤቱ፥ ስምህን አመሰግን ዘንድ፤ ነፍሴን ከወህኒ አውጣት፤ ዋጋዬን እስክትሰጠኝ ድረስ ጻድቃን እኔን ይጠብቃሉ።