ምዕራፍ 92
1 በሰንበት ቀን የምስጋና መዝሙር። 1 እግዚአብሔርን ማመስገን መልካም ነው፥ ልዑል ሆይ፥ ለስምህም ዝማሬ ማቅረብ፤
2 በማለዳ ምሕረትን፥ በሌሊትም እውነትህን ማውራት
3 አሥር አውታር ባለው በበገና፥ ከምስጋና ጋርም በመሰንቆ።
4 አቤቱ፥ በሥራህ ደስ አሰኝተኸኛልና፤ በእጅህም ሥራ ደስ ይለኛልና።
5 አቤቱ፥ ሥራህ እጅግ ትልቅ ነው፥ አሳብህም እጅግ ጥልቅ ነው።
6 ሰነፍ ሰው አያውቅም። ልብ የሌለውም ይህን አያስተውለውም።
7 ኃጢአተኞች እንደ ሣር ሲበቅሉ ዓመፃ የሚያደርጉ ሁሉ ሲለመልሙ፥ ለዘላለም ዓለም እንዲጠፋ ነው።
8 አቤቱ፥ አንተ ግን ለዘላለም ልዑል ነህ፤
9 አቤቱ፥ እነሆ፥ ጠላቶችህ ይጠፋሉና፥ ዓመፃንም የሚሠሩ ሁሉ ይበተናሉና።
10 ቀንዴ አንድ ቀንድ እንዳለው ከፍ ከፍ ይላል፤ ሽምግልናዬም በዘይት ይለመልማል።
11 ዓይኔም በጠላቶቼ ላይ አየች፥ ጆሮዬም በእኔ ላይ በቆሙ በክፉዎች ላይ ሰማች።
12 ጻድቅ እንደ ዘንባባ ያፈራል፥ እንደ ሊባኖስ ዝግባም ያድጋል።
13 በእግዚአብሔር ቤት ውስጥ ተተክለዋል፥ በአምላካችንም አደባባይ ውስጥ ይበቅላሉ።
14 ያን ጊዜ በለመለመ ሽምግልና ያፈራሉ ደስተኞችም ሆነው ይኖራሉ።
15 አምላኬ እግዚአብሔር እውነተኛ እንደ ሆነ ይነግራሉ፥ በእርሱም ዘንድ ዓመፃ የለም።