ምዕራፍ 32
1 የዳዊት ትምህርት። 1 መተላለፉ የቀረችለት ኃጢአቱም የተከደነችለት ምስጉን ነው።
2 እግዚአብሔር በደልን የማይቈጥርበት በመንፈሱም ሽንገላ የሌለበት ሰው ምስጉን ነው።
3 ሁልጊዜ ከመጮኼ የተነሣ ዝም ባልሁ ጊዜ አጥንቶቼ ተበላሹ፤
4 በቀንና በሌሊት እጅህ ከብዳብኛለችና፥ እርጥበቴም ለበጋ ትኵሳት ተለወጠ።
5 ኃጢአቴን ለአንተ አስታወቅሁ፥ በደሌንም አልሸፈንሁም፤ ለእግዚአብሔር መተላለፌን እነግራለሁ አልሁ፤ አንተም የልቤን ኃጢአት ተውህልኝ።
6 ስለዚህ ቅዱስ ሁሉ በምቹ ጊዜ ወደ አንተ ይለምናል፤ ብዙ የጥፋት ውኃም ወደ እርሱ አይቀርብም።
7 አንተ ለእኔ መሸሸጊያዬ ነህ፥ ከጣርም ትጠብቀኛለህ፤ ከከበቡኝ ታድነኝ ዘንድ ደስታዬ ነህ።
8 አስተምርሃለሁ በምትሄድበትም መንገድ እመራሃለሁ፤ ዓይኖቼን በአንተ ላይ አጠናለሁ።
9 ወደ አንተ እንዳይቀርቡ በልባብና በልጓም ጉንጫቸውን እንደሚለጕሙአቸው፥ ልብ እንደሌላቸው እንደ ፈረስና እንደ በቅሎ አትሁኑ።
10 በኃጢአተኛ ብዙ መቅሠፍት አለበት፤ በእግዚአብሔር የሚታመነውን ግን ምሕረት ይከብበዋል።
11 ጻድቃን ሆይ፥ በእግዚአብሔር ደስ ይበላችሁ ሐሤትም አድርጉ፤ ልባችሁም የቀና ሁላችሁ፥ እልል በሉ።