ምዕራፍ 20

1 ለመዘምራን አለቃ፤ የዳዊት መዝሙር። 1 በመከራ ቀን እግዚአብሔር ይስማህ፤ የያዕቆብ አምላክ ስም ያቁምህ።
2 ከመቅደሱ ረድኤትን ይላክልህ፥ ከጽዮንም ያጥናህ።
3 ቍርባንህን ሁሉ ያስብልህ፤ የሚቃጠል መሥዋዕትህን ያለምልምልህ።
4 እንደ ልብህ ይስጥህ ፈቃድህንም ሁሉ ይፈጽምልህ።
5 በማዳንህ ደስ ይለናል፤ በአምላካችን ስም ከፍ ከፍ እንላለን፤ ልመናህን ሁሉ እግዚአብሔር ይፈጽምልህ።
6 እግዚአብሔር የቀባውን እንዳዳነው ዛሬ አወቅሁ፤ ከሰማይ መቅደሱ ይመልስለታል፤ በቀኙ ብርታት ማዳን።
7 እነዚያ በሰረገላ እነዚያም በፈረስ ይታመናሉ፤ እኛ ግን በአምላካችን በእግዚአብሔር ስም ከፍ ከፍ እንላለን።
8 እነርሱ ተሰነካክለው ወደቁ፤ እኛ ግን ተነሣን፥ ጸንተንም ቆምን።
9 አቤቱ፥ ንጉሥን አድነው፥ በጠራንህም ቀን ስማን።