ምዕራፍ 6
1 እናንተ የብንያም ልጆች፥ ክፉ ነገር ታላቅም ጥፋት ከሰሜን ይጐበኛልና ከኢየሩሳሌም ውስጥ ሽሹ፥ በቴቁሔ መለከቱን ንፉ፥ በቤትሐካሪም ላይ ምልክት አንሡ።
2 የተዋበችውንና የተሰባቀለችውን የጽዮንን ልጅ አጐሰቍላለሁ።
3 እረኞችና መንጐቻቸው ወደ እርስዋ ይመጣሉ፥ በዙሪያዋም ድንኳኖቻቸውን ይተክሉባታል፥ እያንዳንዱም በስፍራው መንጋውን ያሰማራል።
4 በእርስዋ ላይ ሰልፍ አዘጋጁ ተነሡ፥ በቀትርም እንውጣ። ቀኑ መሽቶአልና፥ የማታውም ጥላ ረዝሞአልና ወዮልን።
5 ተነሡ በሌሊትም እንውጣ፥ አዳራሾችዋንም እናፍርስ።
6 የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና። ዛፎችዋን ቍረጡ፥ በኢየሩሳሌምም ላይ አፈርን ደልድሉ፤ ይህች ከተማ የምትቀሠፍ ናት፤ መካከልዋ ሁሉ ግፍ ብቻ ነው።
7 በጕድጓድ ውኃ እንደሚፈልቅ፥ እንዲሁ ክፋትዋ ከእርስዋ ዘንድ ይፈልቃል፤ ግፍና ቅሚያ በእርስዋ ዘንድ ይሰማል፥ ደዌና ቍስልም ሁልጊዜ በፊቴ አለ።
8 ኢየሩሳሌም ሆይ፥ ነፍሴ ከአንቺ እንዳትለይ፥ አንቺንም ባድማና ወና እንዳላደርግሽ፥ ተግሣጽን ተቀበዪ።
9 እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ሰው ወይኑን እንደሚቃርም፥ እንዲሁ ከእስራኤል የቀሩትን ፈጽሞ ይቃርሙአቸዋል፤ እጅህንም እንደ ለቃሚ ወደ እንቅብ ዘርጋ።
10 ይሰሙኝስ ዘንድ ለማን እናገራለሁ? ለማንስ አስጠነቅቃለሁ? እነሆ፥ ጆሮአቸው ያልተገረዘች ናት ለመስማትም አይችሉም፤ እነሆ፥ የእግዚአብሔር ቃል ለስድብ ሆኖባቸዋል፥ ደስም አያሰኛቸውም።
11 ስለዚህ በእግዚአብሔር ቍጣ ተሞልቻለሁ፤ ከመታገሥ ደክሜአለሁ፤ በሜዳ በሕፃናት ላይ በጕልማሶችም ጉባዔ ላይ በአንድነት አፍስሰው፤ ባል ከሚስቱ ጋር ሽማግሌውም ከጎበዙ ጋር ይያያዛልና።
12 እጄን በምድር በሚኖሩ ላይ እዘረጋለሁና ቤቶቻቸው እርሻዎቻቸውም ሴቶቻቸውም በአንድነት ለሌሎች ይሆናሉ፥ ይላል እግዚአብሔር።
13 ከታናሹ ጀምሮ እስከ ታላቁ ድረስ ሁሉ ስስትን ያስባሉና፥ ከነቢዩም ጀምሮ እስከ ካህኑ ድረስ ሁሉ በተንኰል ያደርጋሉና።
14 የሕዝቤንም ስብራት በጥቂቱ ይፈውሳሉ፤ ሰላም ሳይሆን። ሰላም ሰላም ይላሉ።
15 ርኩስን ነገር ስለ ሠሩ አፍረዋልን? ምንም አላፈሩም፥ እፍረትንም አላወቁም፤ ስለዚህ ከሚወድቁ ጋር ይወድቃሉ፤ በጐበኘኋቸው ጊዜ ይዋረዳሉ፥ ይላል እግዚአብሔር።
16 እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። በመንገድ ላይ ቁሙ ተመልከቱም፥ የቀደመችውንም መንገድ ጠይቁ፤ መልካሚቱ መንገድ ወዴት እንደ ሆነች እወቁ፥ በእርስዋም ላይ ሂዱ፥ ለነፍሳችሁም ዕረፍት ታገኛላችሁ፤ እነርሱ ግን። አንሄድባትም አሉ።
17 እኔም። የመለከቱን ድምፅ አድምጡ ብዬ ጠባቆችን ሾምሁባችሁ፤ እነርሱ ግን። አናደምጥም አሉ።
18 አሕዛብ ሆይ፥ ስለዚህ ስሙ፤ ማኅበር ሆይ፥ እነዚያ የሚያገኛቸውን እወቁ።
19 ምድር ሆይ፥ ስሚ፤ እነሆ፥ ቃሌን ስላልሰሙ ሕጌንም ስለ ጣሉ በዚህ ሕዝብ ላይ የአሳባቸውን ፍሬ ክፉን ነገር አመጣባቸዋለሁ።
20 ስለ ምንስ ከሳባ ዕጣንን፥ ከሩቅም አገር ቀረፋን ታቀርቡልኛላችሁ? የሚቃጠለውን መሥዋዕታችሁን አልቀበለውም ሌላ መሥዋዕታችሁም ደስ አያሰኘኝም።
21 ስለዚህ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። እነሆ፥ ከዚህ ሕዝብ ፊት ዕንቅፋቶችን አደርጋለሁ፤ አባቶችና ልጆች በአንድነት ይሰናከሉባቸዋል፥ ጎረቤትና ባልንጀራም ይጠፋሉ።
22 እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። እነሆ፥ ሕዝብ ከሰሜን አገር ይመጣል፥ ታላቅ ሕዝብም ከምድር ዳርቻ ይነሣል።
23 ቀስትንና ጦርን ይይዛሉ፤ ጨካኞች ናቸው፥ ምሕረትንም አያደርጉም፤ ድምፃቸው እንደ ባሕር ይተምማል፥ በፈረሶችም ላይ ይቀመጣሉ፤ የጽዮን ሴት ልጅ ሆይ፥ ለሰልፍ እንደ ተዘጋጀ ሰው እያንዳንዳቸው በአንቺ ላይ ተሰለፉ።
24 ወሬውን ሰምተናል፥ እጃችን ደክማለች፤ ምጥ ወላድን ሴት እንደሚይዛት ጭንቀት ይዞናል።
25 የጠላት ሰይፍና ድንጋጤ ከብበዋችኋልና ወደ ሜዳ አትውጡ በምንገድም ላይ አትሂዱ።
26 የሕዝቤ ልጅ ሆይ፥ ማቅ ልበሺ በአመድም ውስጥ ተንከባለዪ፤ አጥፊ በላያችን በድንገት ይመጣብናልና ለአንድያ ልጅ እንደሚደረግ ልቅሶ፥ መራራ ልቅሶ አልቅሺ።
27 መንገዳቸውን እንድታውቅና እንድትፈትን በሕዝቤ መካከል ፈታኝ አድርጌሃለሁ።
28 እነርሱ ሁሉ እጅግ ዓመፀኞች ናቸው፤ በጠማማነት ይሄዳሉ፤ ናስና ብረት ናቸው፤ ሁሉ ርኵሰትን ያደርጋሉ።
29 ወናፍ አናፋ እርሳሱም በእሳት ቀለጠ፤ አንጥረኛውም መልሶ በከንቱ ያቀልጠዋል፤ ኃጢአተኞች አልተወገዱም።
30 እግዚአብሔር ጥሎአቸዋልና የተጣለ ብር ብለው ይጠሩአቸዋል።