ምዕራፍ 28
1 በዚያም ዓመት በይሁዳ ንጉሥ በሴዴቅያስ መንግሥት መጀመሪያ በአራተኛው ዓመት በአምስተኛው ወር ነቢዩ የገባዖን ሰው የዓዙር ልጅ ሐናንያ በእግዚአብሔር ቤት በካህናትና በሕዝብ ሁሉ ፊት እንዲህ ብሎ ተናገረኝ።
2 የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ብሎ ይናገራል። የባቢሎንን ንጉሥ ቀንበር ሰብሬአለሁ።
3 የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር ከዚህች ስፍራ ወደ ባቢሎን የወሰዳትን የእግዚአብሔርን ቤት ዕቃ ሁሉ በሁለት ዓመት ውስጥ ወደዚህች ስፍራ እመልሳታለሁ፤
4 ወደ ባቢሎንም የሄዱትን የይሁዳን ንጉሥ የኢዮአቄምን ልጅ ኢኮንያንንና የይሁዳን ምርኮ ሁሉ ወደዚህች ስፍራ እመልሳቸዋለሁ፤ የባቢሎንን ንጉሥ ቀንበር እሰብራለሁና።
5 ነቢዩ ኤርምያስም በካህናቱና በእግዚአብሔር ቤት በቆሙት ሕዝብ ሁሉ ፊት ለነቢዩ ለሐናንያ ተናገረ።
6 ነቢዩም ኤርምያስ እንዲህ አለ። አሜን፥ እግዚአብሔር እንዲህ ያድርግ፤ የእግዚአብሔርን ቤት ዕቃ ምርኮውንም ሁሉ ከባቢሎን ወደዚህ ስፍራ በመመለስ እግዚአብሔር የተናገርኸውን ትንቢት ይፈጽም።
7 ነገር ግን በጆሮህና በሕዝብ ሁሉ ጆሮ የምናገረውን ይህን ቃል ስማ፤
8 ከጥንት ከእኔና ከአንተ በፊት የነበሩ ነቢያት በብዙ አገርና በታላላቅ መንግሥታት ላይ ስለ ሰልፍና ስለ ክፉ ነገር ስለ ቸነፈርም ትንቢት ተናገሩ።
9 ስለ ሰላም የተናገረ ነቢይ፥ የነቢዩ ቃል በሆነ ጊዜ፥ እግዚአብሔር በእውነት የሰደደው ነቢይ እንደ ሆነ ይታወቃል።
10 ነቢዩም ሐናንያ ቀንበሩን ከነቢዩ ከኤርምያስ አንገት ወስዶ ሰበረው።
11 ሐናንያም በሕዝብ ሁሉ ፊት። እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። እንዲሁ በሁለት ዓመት ውስጥ የባቢሎንን ንጉሥ የናቡከደነፆርን ቀንበር ከአሕዛብ ሁሉ አንገት እሰብራለሁ አለ። ነቢዩም ኤርምያስ መንገዱን ሄደ።
12 ነቢዩም ሐናንያ ቀንበሩን ከነቢዩ ከኤርምያስ አንገት ከሰበረ በኋላ፥ የእግዚአብሔር ቃል ወደ ኤርምያስ እንዲህ ሲል መጣ።
13 ሂድ፥ ለሐናንያ እንዲህ ብለህ ንገረው። እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። አንተ የእንጨትን ቀንበር ሰብረሃል፥ እኔ ግን በእርሱ ፋንታ የብረትን ቀንበር እሠራለሁ።
14 የእስራኤልም አምላክ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና። ለባቢሎን ንጉሥ ለናቡከደነፆር ይገዙለት ዘንድ የብረትን ቀንበር በእነዚህ አሕዛብ ሁሉ አንገት ላይ አድርጌአለሁ፤ እነርሱም ይገዙለታል፥ የምድረ በዳ አራዊት ደግሞ ሰጥቼዋለሁ።
15 ነቢዩም ኤርምያስ ነቢዩን ሐናንያን። ሐናንያ ሆይ፥ ስማ፤ ይህ ሕዝብ በሐሰት እንዲታመን አድርገሃል እንጂ እግዚአብሔር አልላከህም።
16 ስለዚህ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። እነሆ፥ ከምድር ላይ እሰድድሃለሁ፤ በእግዚአብሔር ላይ ዓመፅን ተናግረሃልና በዚህ ዓመት ትሞታለህ አለው።
17 ነቢዩም ሐናንያ በዚያው ዓመት በሰባተኛው ወር ሞተ።