ምዕራፍ 19

1 እግዚአብሔርም እንዲህ አለኝ። ሂድ፥ ከሸክላ ሠሪ ገምቦ ግዛ፥ ከሕዝቡም ሽማግሌዎችና ከካህናት ሽማግሌዎች ከአንተ ጋር ውሰድ፤
2 በካርሲት በር መግቢያ አጠገብ ወዳለው ወደ ሄኖም ልጅ ሸለቆ ሂድ፥ በዚያም የምነግርህን ቃል ተናገር፥
3 እንዲህም በል። የይሁዳ ነገሥታትና በኢየሩሳሌም የምትኖሩ ሆይ፥ የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ፤ የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። የሰማውን ሰው ጆሮ ጭው የሚያደርግ ክፉ ነገር፥ እነሆ፥ በዚህ ስፍራ አመጣለሁ።
4 ትተውኛልና፥ ይህንም ስፍራ እንግዳ አድርገውታልና፥ እነርሱና አባቶቻቸውም ለማያውቋቸው ለሌሎች አማልክት ዐጥነዋልና የይሁዳም ነገሥታት ይህን ስፍራ በንጹህ ደም ሞልተዋልና፥
5 እኔም ያላዘዝሁትን ያልተናገርሁትንም ወደ ልቤም ያልገባውን፥ የሚቃጠለውን መሥዋዕት አድርገው ለበኣል ልጆቻቸውን በእሳት ያቃጥሉ ዘንድ የበኣልን የኮረብታውን መስገጃዎች ሠርተዋልና ስለዚህ፥
6 እነሆ፥ ይህ ስፍራ የእርድ ሸለቆ ይባላል እንጂ ቶፌት ወይም የሄኖም ልጅ ሸለቆ ዳግመኛ የማይባልበት ዘመን ይመጣል፥ ይላል እግዚአብሔር።
7 በዚህም ስፍራ የይሁዳንና የኢየሩሳሌምን ምክር አፈርሳለሁ፥ በጠላቶቻቸውም ፊት በሰይፍና ነፍሳቸውን በሚሹት እጅ እጥላቸዋለሁ፥ ሬሳቸውንም ለሰማይ ወፎችና ለምድር አራዊት መብል አድርጌ እሰጣለሁ።
8 ይህችንም ከተማ ለመደነቂያና ለማፍዋጫ አደርጋታለሁ፤ የሚያልፍባትም ሁሉ ስለ ተደረገባት መቅሠፍት ሁሉ ይደነቃል ከንፈሩንም ይመጥጣል።
9 የወንዶችና የሴቶች ልጆቻቸውንም ሥጋ አበላቸዋለሁ፥ ሁሉም ጠላቶቻቸውንና ነፍሳቸውን የሚሹት በሚያስጨንቋቸው ጭንቀትና መከበብ የባልንጀሮቻቸውን ሥጋ ይበላሉ።
10 ገምቦውንም ከአንተ ጋር በሚሄዱ ሰዎች ፊት ትሰብራለህ፥
11 እንዲህም ትላቸዋለህ። የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። የሸክላ ሠሪው ዕቃ እንደሚሰባበር ደግሞም ይጠገን ዘንድ እንደማይቻል፥ እንዲሁ ይህን ሕዝብና ይህችን ከተማ እሰብራለሁ፤ የሚቀብሩበትም ስፍራ ሌላ የለምና በቶፌት ይቀበራሉ።
12 እንዲሁ በዚህ ስፍራና በሚኖሩበት ላይ አደርጋለሁ፥ ይላል እግዚአብሔር፥ ይህችንም ከተማ እንደ ቶፌት አደርጋለሁ።
13 የረከሱትም የኢየሩሳሌም ቤቶችና የይሁዳ ነገሥታት ቤቶች፥ እነዚያ በሰገነታቸው ላይ ለሰማይ ሠራዊት ሁሉ ያጠኑባቸው ለሌሎችም አማልክት የመጠጥን ቍርባን ያፈሰሱባቸው ቤቶች ሁሉ፥ እንደ ቶፌት ስፍራ ይሆናሉ።
14 ኤርምያስም እግዚአብሔር ትንቢት ሊናገር ወደዚያ ልኮት ከነበረው ስፍራ ከቶፌት መጣ፥ በእግዚአብሔርም ቤት አደባባይ ቆሞ ለሕዝብ ሁሉ።
15 የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ቃሌን እንዳይሰሙ አንገታቸውን አደንድነዋልና እነሆ፥ በዚህች ከተማና በመንደሮችዋ ሁሉ ላይ የተናገርሁባትን ክፉ ነገር ሁሉ አመጣለሁ።