ምዕራፍ 40

1 ወደ ባቢሎን በተማረኩት በኢየሩሳሌምና በይሁዳ ምርኮኞች መካከል የዘበኞቹ አለቃ ናቡዘረዳን በሰንሰለት አስሮ በወሰደው ጊዜ ከራማ ከለቀቀው በኋላ ከእግዚአብሔር ዘንድ ወደ ኤርምያስ የመጣ ቃል ይህ ነው።
2 የዘበኞቹም አለቃ ኤርምያስን ወሰደው እንዲህም አለው። አምላክህ እግዚአብሔር ይህን ክፉ ነገር በዚህ ስፍራ ላይ ተናገረ፤
3 እግዚአብሔርም አመጣው እንደ ተናገረውም አደረገ፤ በእግዚአብሔርም ላይ ኃጢአት ሠርታችኋልና፥ ቃሉንም አልሰማችሁምና ይህ ነገር ሆነባችሁ።
4 አሁንም፥ እነሆ፥ በእጅህ ካለችው ሰንሰለት ዛሬ ፈታሁህ። ከእኔ ጋር ወደ ባቢሎን መምጣት መልካም መስሎ ቢታይህ፥ ና፥ እኔም በመልካም አይሃለሁ፤ ከእኔ ጋር ወደ ባቢሎን መምጣት መልካም መስሎ ባይታይህ ግን፥ ተቀመጥ፤ እነሆ፥ አገሪቱ ሁሉ በፊትህ ናት፤ ትሄድ ዘንድ መልካም መስሎ ወደሚታይህ ደስ ወደሚያሰኝህም ስፍራ ሂድ።
5 እርሱም ገና ሳይመለስ። የባቢሎን ንጉሥ በይሁዳ ከተሞች ላይ ወደ ሾመው ወደ ሳፋን ልጅ ወደ አኪቃም ልጅ ወደ ጎዶልያስ ተመለስ፥ ከእርሱም ጋር በሕዝቡ መካከል ተቀመጥ፤ ወይም ትሄድ ዘንድ ደስ ወደሚያሰኝህ ስፍራ ሂድ አለው። የዘበኞቹም አለቃ ስንቅና ስጦታ ሰጥቶ አሰናበተው።
6 ኤርምያስም የአኪቃም ልጅ ጎዶልያስ ወዳለበት ወደ ምጽጳ ሄደ፥ ከእርሱም ጋር በአገሩ ውስጥ በቀሩት ሕዝብ መካከል ተቀመጠ።
7 በየሜዳውም የነበሩት የጭፍራ አለቆችና ሰዎቻቸው ሁሉ የባቢሎን ንጉሥ የአኪቃምን ልጅ ጎዶልያስን በምድር ላይ እንደ ሾመ፥ ወንዶችንና ሴቶችን ልጆችንም፥ ወደ ባቢሎን ያልተማረኩትን የምድርን ድሆች፥ እንዳስጠበቀ በሰሙ ጊዜ የናታንያ ልጅ እስማኤል፥
8 የቃሬያም ልጅ ዮሐናንና ዮናታን፥ የተንሑሜትም ልጅ ሠራያ፥ የነጦፋዊውም የዮፌ ልጆች የማዕካታዊውም ልጅ ያእዛንያ ከሰዎቻቸው ጋር ወደ ጎዶልያስ ወደ ምጽጳ መጡ።
9 የሳፋንም ልጅ የአኪቃም ልጅ ጎዶልያስ ለእነርሱና ለሰዎቻቸው እንዲህ ብሎ ማለ። ለከለዳውያን ትገዙ ዘንድ አትፍሩ፤ በምድር ተቀመጡ ለባቢሎንም ንጉሥ ተገዙ፥ መልካምም ይሆንላችኋል።
10 እኔም፥ እነሆ፥ ወደ እኛ በሚመጡት ከለዳውያን ፊት እቆም ዘንድ በምጽጳ እኖራለሁ፤ እናንተ ግን ወይንንና የበጋ ፍሬ ዘይትንም አከማቹ፥ በየዕቃችሁም ውስጥ ክተቱ፥ በያዛችኋቸውም ከተሞቻችሁ ተቀመጡ።
11 በሞዓብም በአሞንም ልጆች መካከል በኤዶምያስም በምድርም ሁሉ ላይ የነበሩ አይሁድ ሁሉ የባቢሎን ንጉሥ የይሁዳን ቅሬታ እንዳስቀረ፥ የሳፋንንም ልጅ የአኪቃምን ልጅ ጎዶልያስን በላያቸው እንደ ሾመው በሰሙ ጊዜ፥
12 አይሁድ ሁሉ ከተሰደዱበት ስፍራ ሁሉ ተመለሱ፥ ወደ ይሁዳም አገር ጎዶልያስ ወዳለበት ወደ ምጽጳ መጡ፥ ወይንና የበጋንም ፍሬ እጅግ ብዙ አከማቹ።
13 የቃሬያም ልጅ ዮሐናን በየሜዳውም የነበሩ የጭፍራ አለቆች ሁሉ ወደ ጎዶልያስ ወደ ምጽጳ መጥተው።
14 የአሞን ልጆች ንጉሥ በኣሊስ ይገድልህ ዘንድ የናታንያን ልጅ እስማኤልን እንደ ሰደደ ታውቃለህን? አሉት። የአኪቃም ልጅ ጎዶልያስ ግን አላመናቸውም።
15 የቃሬያም ልጅ ዮሐናን። እባክህ፥ ልሂድ፤ ማንም ሳያውቅ የናታንያን ልጅ እስማኤልን ልግደለው፤ ወደ አንተ የተሰበሰቡ አይሁድ ሁሉ እንዲበተኑ የይሁዳም ቅሬታ እንዲጠፋ ነፍስህን ስለ ምን ይገድላል? ብሎ በምጽጳ በቆይታ ለጎዶልያስ ተናገረ።
16 የአኪቃም ልጅ ጎዶልያስ ግን የቃሬያን ልጅ ዮሐናንን። በእስማኤል ላይ ሐሰት ተናግረሃልና ይህን ነገር አታድርግ አለው።