ምዕራፍ 14
1 ወደ ኤርምያስ ስለ ድርቅ የመጣው የእግዚአብሔር ቃል ይህ ነው።
2 ይሁዳ አለቀሰች፥ ደጆችዋም ባዶ ሆኑ በምድርም ላይ ጨለሙ፤ የኢየሩሳሌም ጩኸት ከፍ ከፍ ብሎአል።
3 ታላላቆችም ብላቴኖቻቸውን ወደ ውኃ ሰደዱ፤ ወደ ጕድጓድ መጡ ውኃም አላገኙም፥ ዕቃቸውንም ባዶውን ይዘው ተመለሱ፤ አፈሩም ተዋረዱም ራሳቸውንም ተከናነቡ።
4 በምድር ላይ አልዘነበምና መሬቱ ስንጥቅጥቅ ስለሆነ አራሾች አፈሩ ራሳቸውንም ተከናነቡ።
5 ዋላ ደግሞ በምድረ በዳ ወለደች፥ ሣርም የለምና ግልገልዋን ተወች።
6 የሜዳ አህዮችም በወና ኮረብታ ላይ ቆመዋል፥ እንደ ቀበሮም ወደ ነፋስ አለከለኩ፤ ልምላሜም የለምና ዓይኖቻቸው ጠወለጉ።
7 አቤቱ፥ ኃጢአታችን ብዙ ነውና፥ በአንተም ላይ ኃጢአት ሠርተናልና ኃጢአታችን ይመሰክርብናል ነገር ግን ስለ ስምህ ብለህ አድርግ።
8 አንተ የእስራኤል ተስፋ ሆይ በመከራም ጊዜ የምታድነው፥ በምድር እንደ እንግዳ፥ ወደ ማደሪያ ዘወር እንደሚል መንገደኛ ስለ ምን ትሆናለህ?
9 እንዳንቀላፋ ሰው ሰው፥ ያድንም ዘንድ እንደማይችል ኃያል ስለ ምን ትሆናለህ? አንተ ግን፥ አቤቱ፥ በመካከላችን ነህ እኛም በስምህ ተጠርተናል፤ አትተወን።
10 እግዚአብሔር ለዚህ ሕዝብ እንዲህ ይላል። መቅበዝበዝን ወድደዋል እግራቸውንም አልከለከሉም፤ ስለዚህ እግዚአብሔር በእነርሱ ደስ አይለውም፥ በደላቸውንም አሁን ያስባል ኃጢአታቸውንም ይቀጣል።
11 እግዚአብሔርም። ለዚህ ሕዝብ ስለ መልካም አትጸልይላቸው።
12 በጾሙ ጊዜ ጸሎታቸውን አልሰማም፤ የሚቃጠለውን መሥዋዕትና የእህሉን ቍርባን ባቀረቡ ጊዜ አልቀበላቸውም፤ በሰይፍና በራብ በቸነፈርም አጠፋቸዋለሁ አለኝ።
13 እኔም። ጌታ እግዚአብሔር ሆይ፥ ወዮ! እነሆ፥ ነቢያት። በእውነት ሰላምን በዚህ ስፍራ እሰጣችኋለሁ እንጂ ሰይፍን አታዩም፥ ራብም አያገኛችሁም ይሉአቸዋል አልሁ።
14 እግዚአብሔርም እንዲህ አለኝ። ነቢያቱ ውሸት በስሜ ትንቢት ይናገራሉ፤ አላክኋቸውም፥ አላዘዝኋቸውም፥ አልተናገርኋቸውም፤ የውሸቱን ራእይ ምዋርትንም ከንቱንም ነገር የልባቸውንም ሽንገላ ይሰብኩላችኋል።
15 ስለዚህ እግዚአብሔር በስሜ ትንቢት ስለሚናገሩ ነቢያት። በዚህች አገር ሰይፍና ራብ አይሆንም ስለሚሉ ስላላክኋቸው ነቢያት እንዲህ ይላል። እነዚያ በሰይፍና በራብ ይጠፋሉ።
16 ትንቢት የሚናገሩላቸውም ሰዎች ከራብና ከሰይፍ የተነሣ በኢየሩሳሌም አደባባይ ይበተናሉ፤ ክፋታቸውንም አፈስስባቸዋለሁ እነርሱንና ሚስቶቻቸውን ወንዶችና ሴቶች ልጆቻቸውንም የሚቀብራቸው አይገኝም።
17 እንደዚህም ብለህ ትነግራቸዋለህ። የወገኔ ልጅ ድንግሊቱ በታላቅ ስብራትና እጅግ ክፉ በሆነ ቍስል ተሰብራለችና ዓይኖቼ ሌሊትና ቀን ሳያቋርጡ እንባ ያፈሳሉ።
18 ወደ ሜዳ ብወጣ፥ እነሆ፥ በሰይፍ የሞቱ አሉ፤ ወደ ከተማም ብገባ፥ እነሆ፥ በራብ የከሱ አሉ፤ ነቢዩና ካህኑም ወደማያውቋት አገር ሄደዋልና።
19 በውኑ ይሁዳን ፈጽመህ ጥለኸዋልን? ነፍስህስ ጽዮንን ጠልታታለችን? ስለ ምን መታኸን? ፈውስስ ስለ ምን የለንም? ሰላምን በተስፋ ተጠባበቅን፥ መልካምም አልተገኘም፤ ፈውስን በተስፋ ተጠባበቅን፥ እነሆም፥ ድንጋጤ ሆነ።
20 አቤቱ፥ በአንተ ላይ ኃጢአትን ሠርተናልና ክፋታችንንና የአባቶቻችንን በደል እናውቃለን።
21 ስለ ስምህ ብለህ አትናቀን፥ የክብርህንም ዙፋን አታስነውር፤ ከእኛ ጋርም ያደረግኸውን ቃል ኪዳንህን አስብ እንጂ አታፍርስ።
22 በውኑ በአሕዛብ ጣዖታት መካከል ያዘንብ ዘንድ የሚችል ይገኛልን? ወይስ ሰማይ ዝናብ ማፍሰስ ይችላልን? አቤቱ አምላካችን ሆይ፥ አንተ አይደለህምን? አንተ ይህን ነገር ሁሉ አድርገሃልና ስለዚህ አንተን በተስፋ እንጠባበቃለን።