ምዕራፍ 60
1፤ ብርሃንሽ መጥቶአልና፥ የእግዚአብሔርም ክብር ወጥቶልሻልና ተነሺ፥ አብሪ።
2፤ እነሆ፥ ጨለማ ምድርን ድቅድቅ ጨለማም አሕዛብን ይሸፍናል፤ ነገር ግን በአንቺ ላይ እግዚአብሔር ይወጣል ክብሩም በአንቺ ላይ ይታያል፤
3፤ አሕዛብም ወደ ብርሃንሽ ነገሥታትም ወደ መውጫሽ ጸዳል ይመጣሉ።
4፤ ዓይኖችሽን አንሥተሽ በዙሪያሽ ተመልከቺ፤ እነዚህ ሁሉ ተሰብስበው ወደ አንቺ ይመጣሉ፤ ወንዶች ልጆችሽ ከሩቅ ይመጣሉ፥ ሴቶች ልጆችሽንም በጫንቃ ላይ ይሸከሙአቸዋል።
5፤ በዚያን ጊዜ የባሕሩ በረከት ወደ አንቺ ስለሚመለስ፥ የአሕዛብም ብልጥግና ወደ አንቺ ስለሚመጣ፥ አይተሽ ደስ ይልሻል፥ ልብሽም ይደነቃል ይሰፋማል።
6፤ የግመሎች ብዛት፥ የምድያምና የጌፌር ግመሎች፥ ይሸፍኑሻል፤ ሁሉ ከሳባ ይመጣሉ፥ ወርቅንና ዕጣንን ያመጣሉ የእግዚአብሔርንም ምስጋና ያወራሉ።
7፤ የቄዳር መንጎች ሁሉ ወደ አንቺ ይሰበሰባሉ የነባዮትም አውራ በጎች ያገለግሉሻል፤ እኔን ደስ ሊያሰኙ በመሠዊያዬ ላይ ይወጣሉ፥ የክብሬንም ቤት አከብራለሁ።
8፤ ርግቦች ወደ ቤታቸው እንደሚበርሩ፥ እነዚህ እንደ ደመና የሚበርሩ እነማን ናቸው?
9፤ እርሱ አክብሮሻልና ለአምላክሽ ለእግዚአብሔር ስምና ለእስራኤል ቅዱስ ልጆችሽን ከሩቅ ከእነርሱ ጋርም ብራቸውንና ወርቃቸውን ያመጡ ዘንድ ደሴቶች የተርሴስ መርከቦችም አስቀድመው ይጠባበቁኛል።
10፤ በቍጣዬ ቀሥፌ በፍቅሬ ምሬሻለሁና መጻተኞች ቅጥርሽን ይሠራሉ፥ ነገሥታቶቻቸውም ያገለግሉሻል።
11፤ በሮችሽም ሁልጊዜ ይከፈታሉ፤ ሰዎች የአሕዛብን ብልጥግና የተማረኩትንም ነገሥታቶቻቸውን ወደ አንቺ ያመጡ ዘንድ ሌሊትና ቀን አይዘጉም።
12፤ ለአንቺም የማይገዛ ሕዝብና መንግሥት ይጠፋል፥ እነዚያ አሕዛብም ፈጽመው ይጠፋሉ።
13፤ የመቅደሴንም ስፍራ ያስጌጡ ዘንድ የሊባኖስ ክብር፥ ጥዱና አስታው ባርሰነቱም፥ ወደ አንቺ ይመጣሉ፥ የእግሬንም ስፍራ አከብራለሁ።
14፤ የአስጨናቂዎችሽም ልጆች አንገታቸውን ደፍተው ወደ አንቺ ይመጣሉ፥ የናቁሽም ሁሉ ወደ እግርሽ ጫማ ይሰግዳሉ፤ የእግዚአብሔርም ከተማ፥ የእስራኤል ቅዱስ የሆንሽ ጽዮን ይሉሻል።
15፤ ከሰውም ማንም እስከማያልፍብሽ ድረስ የተተውሽና የተጠላሽ ነበርሽ፤ ነገር ግን የዘላለም ትምክሕትና የልጅ ልጅ ደስታ አደርግሻለሁ።
16፤ የአሕዛብንም ወተት ትጠጫለሽ የነገሥታትንም ጡት ትጠቢያለሽ፤ እኔም እግዚአብሔር የያዕቆብ ኃይል፥ መድኃኒትሽና ታዳጊሽ እንደ ሆንሁ ታውቂያለሽ።
17፤ በናስ ፋንታ ወርቅን፥ በብረትም ፋንታ ብርን፥ በእንጨትም ፋንታ ናስን፥ በድንጋይም ፋንታ ብረትን አመጣለሁ። አለቆችሽንም ሰላም፥ የበላይ ገዢዎችሽንም ጽድቅ አደርጋለሁ፤
18፤ ከዚያ በኋላ በምድርሽ ውስጥ ግፍ፥ በዳርቻሽም ውስጥ ጕስቍልናና ቅጥቃጤ አይሰማም፤ ቅጥርሽን መዳን በሮችሽንም ምስጋና ብለሽ ትጠሪያለሽ
19፤ ከዚያ በኋላ እግዚአብሔር የዘላለም ብርሃንሽ፥ አምላክሽም ክብርሽ ይሆናልና ፀሐይ በቀን ብርሃን አይሆንልሽም፥ የጨረቃም ብርሃን በሌሊት አይበራልሽም።
20፤ እግዚአብሔር የዘላለም ብርሃንሽ ይሆናልና፥ የልቅሶሽም ወራት ታልቃለችና ፀሐይሽ ከዚያ በኋላ አትጠልቅም ጨረቃሽም አይቋረጥም።
21፤ ሕዝብሽም ሁሉ ጻድቃን ይሆናሉ፤ እኔም እከብር ዘንድ የአታክልቴን ቡቃያ፥ የእጄ ሥራ የምትሆን ምድሪቱንም ለዘላለም ይወርሳሉ።
22፤ ታናሹ ለሺህ የሁሉም ታናሹ ለብርቱ ሕዝብ ይሆናል፤ እኔ እግዚአብሔር በዘመኑ ይህን አፋጥነዋለሁ።