ምዕራፍ 6
1፤ ንጉሡ ዖዝያን በሞተበት ዓመት እግዚአብሔርን በረጅምና ከፍ ባለ ዙፋን ላይ ተቀምጦ አየሁት፥ የልብሱም ዘርፍ መቅደሱን ሞልቶት ነበር።
2፤ ሱራፌልም ከእርሱ በላይ ቆመው ነበር፥ ለእያንዳንዱም ስድስት ክንፍ ነበረው፤ በሁለት ክንፍ ፊቱን ይሸፍን ነበር፥ በሁለቱም ክንፍ እግሮቹን ይሸፍን ነበር፥ በሁለቱም ክንፍ ይበር ነበር።
3፤ አንዱም ለአንዱ። ቅዱስ፥ ቅዱስ፥ ቅዱስ፥ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር፤ ምድር ሁሉ ከክብሩ ተሞልታለች እያለ ይጮኽ ነበር።
4፤ የመድረኩም መሠረት ከጭዋኺው ድምፅ የተነሣ ተናወጠ፥ ቤቱንም ጢስ ሞላበት።
5፤ እኔም። ከንፈሮቼ የረከሱብኝ ሰው በመሆኔ፥ ከንፈሮቻቸውም በረከሱባቸው ሕዝብ መካከል በመቀመጤ ዓይኖቼ የሠራዊትን ጌታ ንጉሡን እግዚአብሔርን ስለ አዩ ጠፍቻለሁና ወዮልኝ! አልሁ።
6፤ ከሱራፌልም አንዱ እየበረረ ወደ እኔ መጣ፥ በእጁም ከመሠዊያው በጕጠት የወሰደው ፍም ነበረ።
7፤ አፌንም ዳሰሰበትና። እነሆ፥ ይህ ከንፈሮችህን ነክቶአል፤ በደልህም ከአንተ ተወገደ፥ ኃጢአትህም ተሰረየልህ አለኝ።
8፤ የጌታንም ድምፅ። ማንን እልካለሁ? ማንስ ይሄድልናል? ሲል ሰማሁ። እኔም። እነሆኝ፥ እኔን ላከኝ አልሁ።
9፤ እርሱም። ሂድ፥ ይህን ሕዝብ። መስማትን ትሰማላችሁ አታስተውሉምም፤ ማየትንም ታያላችሁ አትመለከቱምም በላቸው።
10፤ በዓይናቸው እንዳያዩ፥ በጆሮአቸውም እንዳይሰሙ፥ በልባቸውም እንዳያስተውሉ፥ ተመልሰውም እንዳይፈወሱ፥ የዚህን ሕዝብ ልብ አደንድን፥ ጆሮአቸውንም አደንቍር፥ ዓይናቸውንም ጨፍን አለኝ።
11፤ እኔም። ጌታ ሆይ፥ እስከ መቼ ድረስ ነው? አልሁ። እርሱም መልሶ እንዲህ አለ። ከተሞች የሚኖርባቸውን አጥተው እስኪፈርሱ ድረስ፥ ቤቶችም ሰው አልቦ እስኪሆኑ ምድርም ፈጽሞ ባድማ ሆና እስክትቀር ድረስ፥
12፤ እግዚአብሔርም ሰዎችን እስኪያርቅ፥ በምድርም መካከል ውድማው መሬት እስኪበዛ ድረስ ነው።
13፤ በእርስዋም ዘንድ አሥረኛ እጅ ቀርቶ እንደ ሆነ እርሱ ደግሞ ይቃጠላል፤ በተቈረጡ ጊዜ ጉቶቻቸው እንደ ቀሩ እንደ ግራርና እንደ ኮምበል ዛፍ ሆኖ፥ ጉቶው የተቀደሰ ዘር ይሆናል።