ምዕራፍ 5
1፤ አሁን ስለ ወዳጄና ስለ ወይን ቦታው ለወዳጄ ቅኔ እቀኛለሁ። ለወዳጄ በፍሬያማው ኮረብታ ላይ የወይን ቦታ ነበረው።
2፤ በዙሪያው ቈፈረ፥ ድንጋዮችንም ለቅሞ አወጣ፥ ምርጥ የሆነውንም አረግ ተከለበት፥ በመካከሉም ግንብ ሠራ፥ ደግሞም የመጥመቂያ ጕድጓድ ማሰበት፤ ወይንንም ያፈራ ዘንድ ተማመነ፥ ዳሩ ግን ሆምጣጣ ፍሬ አፈራ።
3፤ አሁንም እናንተ በኢየሩሳሌም የምትኖሩ የይሁዳ ሰዎች ሆይ፥ በእኔና በወይኑ ቦታዬ መካከል እስኪ ፍረዱ።
4፤ ለወይኔ ያላደረግሁለት፥ ከዚህ ሌላ አደርግለት ዘንድ የሚገባኝ ምንድር ነው? ወይንን ያፈራል ብዬ ስትማመን ስለ ምን ሆምጣጣ ፍሬ አፈራ?
5፤ አሁንም በወይኔ ላይ የማደርገውን እነግራችኋለሁ፤ አጥሩን እነቅላለሁ፥ ለማሰማርያም ይሆናል፤ ቅጥሩንም አፈርሳለሁ፥ ለመራገጫም ይሆናል።
6፤ ባድማ አደርገዋለሁ፤ አይቈረጥም፥ አይኰተኰትም፤ ኵርንችትና እሾህ ይበቅልበታል፤ ዝናብንም እንዳያዘንቡበት ዳመናዎችን አዝዛለሁ።
7፤ የሠራዊት ጌታ የእግዚአብሔር ወይን ቦታ እርሱ የእስራኤል ቤት ነው፥ የደስታውም አትክልት የይሁዳ ሰዎች ናቸው፤ ፍርድን ተስፋ ያደርግ ነበር፥ እነሆም ደም ማፍሰስ ሆነ፤ ጽድቅንም ይተማመን ነበር፥ እነሆም፥ ጩኸት ሆነ።
8፤ ስፍራ እስከማይቀር ድረስ እናንተም በምድር ላይ ብቻችሁን እስክትቀመጡ ድረስ፥ ቤትን ከቤት ጋር ለሚያያይዙ እርሻንም ከእርሻ ጋር ለሚያቀራርቡ ወዮላቸው!
9፤ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር በጆሮዬ እንዲህ አለ። በእውነት ብዙ ታላቅና መልካም ቤት ባድማ ይሆናል፥ የሚቀመጥበትም አይገኝም።
10፤ ከወይኑ ቦታ አሥር ጥማድ በሬ ካረሰው አንድ የባዶስ መስፈሪያ ብቻ ይወጣል፤ አንድ የቆሮስ መስፈሪያ ዘር አንድ የኢፍ መስፈሪያ ብቻ ይሰጣል።
11፤ ስካርን ለመከተል በጥዋት ለሚማልዱ፥ የወይን ጠጅም እስኪያቃጥላቸው እስከ ሌሊት ድረስ ለሚዘገዩ ወዮላቸው!
12፤ መሰንቆና በገና ከበሮና እምቢልታም የወይን ጠጅም በግብዣቸው አለ፤ የእግዚአብሔርን ሥራ ግን አልተመለከቱም፥ እጁም ያደረገችውን አላስተዋሉም።
13፤ ስለዚህ ሕዝቤ ወደ ምርኮ ሄዱ፥ ጌታን አላወቁትምና፤ ከበርቴዎቻቸውም ተራቡ፥ ሕዝባቸውም ተጠሙ።
14፤ ሲኦልም ሆድዋን አስፍታለች፥ አፍዋንም ያለ ልክ ከፍታለች፤ ከበርቴዎቻቸውና አዛውንቶቻቸው ባለጠጎቻቸውም ደስተኞቻቸውም ወደ እርስዋ ይወርዳሉ።
15፤ ሰውም ይጐሰቍላል፥ ሰውም ይዋረዳል፥ የትዕቢተኞችም ዓይን ትዋረዳለች፤
16፤ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ግን በፍርድ ከፍ ከፍ ብሎአል፥ ቅዱሱም አምላክ በጽድቅ ተቀድሶአል።
17፤ የበግ ጠቦቶች በማሰማርያቸው ውስጥ ይሰማራሉ፥ እንግዶችም የሰቡትን ባድማ ይበላሉ።
18፤ በደልን በምናምንቴ ገመድ፥ ኃጢአትንም በሰረገላ ማሰሪያ ወደ ራሳቸው ለሚስቡ። እናይ ዘንድ ይቸኵል፥
19፤ ሥራውንም ያፋጥን፤ እናውቃትም ዘንድ የእስራኤል ቅዱስ ምክር ትቅረብ፥ ትምጣ ለሚሉ ወዮላቸው!
20፤ ክፉውን መልካም መልካሙን ክፉ ለሚሉ፥ ጨለማውን ብርሃን ብርሃኑንም ጨለማ ለሚያደርጉ፥ ጣፋጩን መራራ መራራውንም ጣፋጭ ለሚያደርጉ ወዮላቸው!
21፤ በዓይናቸው ጥበበኞች በነፍሳቸውም አስተዋዮች ለሆኑ ወዮላቸው!
22፤ የወይን ጠጅ ለመጠጣት ኃያላን የሚያሰክረውንም ለማደባለቅ ጨካኞች ለሆኑ፤
23፤ በደለኛውን ስለ ጉቦ ጻድቅ ለሚያደርጉ፥ የጻድቁንም ጽድቅ ለሚያስወግዱበት ወዮላቸው!
24፤ ስለዚህ የእሳት ወላፈን ቃርሚያን እንደሚበላ፥ እብቅም በነበልባል ውስጥ እንደሚጠፋ፥ እንዲሁ የእነርሱ ሥር የበሰበሰ ይሆናል ቡቃያቸውም እንደ ትቢያ ይበንናል፤ የሠራዊት ጌታ የእግዚአብሔርን ሕግ ጥለዋልና፥ የእስራኤልም ቅዱስ የተናገረውን ቃል አቃልለዋልና።
25፤ ስለዚህ የእግዚአብሔር ቍጣ በሕዝቡ ላይ ነድዶአል እጁንም በላያቸው ዘርግቶ መትቶአቸዋል፤ ተራሮችም ተንቀጠቀጡ፥ ሬሳቸውም በአደባባይ መካከል እንደ ጕድፍ ሆኖአል። በዚህም ሁሉ እንኳ ቍጣው አልተመለሰችም፥ ነገር ግን እጁ ገና ተዘርግታ ትኖራለች።
26 ለአሕዛብም በሩቅ ምልክትን ያቆማል፥ ከምድርም ዳርቻ በፉጨት ይጠራቸዋል፤ እነሆም፥ እየተጣደፉ ፈጥነው ይመጣሉ።
27 ደካማና ስንኵል የለባቸውም፥ የሚያንቀላፋና የሚተኛም የለም፤ የወገባቸውም መቀነት አይፈታም፥ የጫማቸውም ማዘቢያ አይበጠስም።
28 ፍላጾቻቸው ተስለዋል፥ ቀስቶቻቸውም ሁሉ ተለጥጠዋል፤ የፈረሶቻቸውም ኮቴ እንደ ቡላድ የሰረገሎቻቸውም መንኰራኵር እንደ ዐውሎ ነፋስ ይቈጠራል።
29 ጩኸታቸው እንደ አንበሳ ነው፥ እንደ አንበሳ ደቦሎችም ያገሣሉ፤ ንጥቂያንም ይዘው ያገሣሉ፥ ይወስዱትማል፥ የሚያድንም የለም።
30 በዚያም ቀን እንደ ባሕር መትመም ይተምሙባቸዋል፤ ወደ ምድርም ቢመለከቱ፥ እነሆ፥ ጨለማና መከራ አለ፤ ብርሃንም በደመናዎችዋ ውስጥ ጨልሞአል።