ምዕራፍ 54

1፤ አንቺ ያልወለድሽ መካን ሆይ፥ ዘምሪ፤ አንቺ ያላማጥሽ ሆይ፥ እልል በዪ፥ ጩኺም፤ ባል ካላት ይልቅ ፈት የሆነቺቱ ልጆች በዝተዋልና፥ ይላል እግዚአብሔር።
2፤ የድንኳንሽን ስፍራ አስፊ፥ መጋረጃዎችሽንም ይዘርጉ፤ አትቈጥቢ፤ አውታሮችሽን አስረዝሚ ካስሞችሽንም አጽኚ።
3፤ በቀኝና በግራ ትሰፋፊያለሽና፥ ዘርሽም አሕዛብን ይወርሳልና፥ የፈረሱትንም ከተሞች መኖሪያ ያደርጋልና።
4፤ አታፍሪምና አትፍሪ፤ አተዋረጂምና አትደንግጪ፤ የሕፃንነትሽንም እፍረት ትረሺዋለሽ፥ የመበለትነትሽንም ስድብ ከእንግዲህ ወዲህ አታስቢም።
5፤ ፈጣሪሽ ባልሽ ነው፥ ስሙም የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ነው፤ የእስራኤልም ቅዱስ ታዲጊሽ ነው፥ እርሱም የምድር ሁሉ አምላክ ይባላል።
6፤ እግዚአብሔር እንደ ተተወችና እንደ ተበሳጨች በልጅነትዋም እንደ ተጣለች ሚስት ጠርቶሻል፥ ይላል አምላክሽ።
7፤ ጥቂት ጊዜ ተውሁሽ፥ በታላቅም ምሕረት እሰበስብሻለሁ።
8፤ በጥቂት ቍጣ ለቅጽበት ዓይን ፊቴን ከአንቺ ሰወርሁ፥ በዘላለምም ቸርነት እምርሻለሁ፥ ይላል ታዳጊሽ እግዚአብሔር።
9፤ ይህ ለእኔ እንደ ኖኅ ውኃ ነው፤ የኖኅ ውኃ ደግሞ በምድር ላይ እንዳያልፍ እንደ ማልሁ፥ እንዲሁ አንቺን እንዳልቈጣ እንዳልዘልፍሽም ምያለሁ።
10፤ ተራሮች ይፈልሳሉ፥ ኮረብቶችም ይወገዳሉ፤ ቸርነቴ ግን ከአንቺ ዘንድ አይፈልስም የሰላሜም ቃል ኪዳን አይወገድም፥ ይላል መሐሪሽ እግዚአብሔር።
11፤ አንቺ የተቸገርሽ በዐውል ነፋስም የተናወጥሽ ያልተጽናናሽም፥ እነሆ፥ ድንጋዮችሽን ሸላልሜ እገነባለሁ፥ በሰንፔርም እመሠርትሻለሁ።
12፤ የግንብሽንም ጕልላት በቀይ ዕንቍ፥ በሮችሽንም በሚያብረቀርቅ ዕንቍ፥ ዳርቻሽንም ሁሉ በከበሩ ድንጋዮች እሠራለሁ።
13፤ ልጆችሽም ሁሉ ከእግዚአብሔር የተማሩ ይሆናሉ፥ የልጆችሽም ሰላም ብዙ ይሆናል።
14፤ በጽድቅ ትታነጺያለሽ፤ ከግፍ ራቂ፥ አትፈሪምም፥ ድንጋጤም ወደ አንቺ አትቀርብም።
15፤ እነሆ፥ ይሰበሰባሉ፥ ነገር ግን ከእኔ ዘንድ አይሆንም፤ በአንቺም ላይ የሚሰበሰቡ ሁሉ ከአንቺ የተነሣ ይወድቃሉ።
16፤ እነሆ፥ ፍሙን በወናፍ የሚያናፋ ለሥራውም መሣሪያ የሚያወጣ ብረት ሠሪን እኔ ፈጥሬአለሁ፤ የሚያፈርሰውንም እንዲያጠፋ ፈጥሬአለሁ።
17፤ በአንቺ ላይ የተሠራ መሣሪያ ሁሉ አይከናወንም፤ በፍርድም በሚነሣብሽ ምላስ ሁሉ ትፈርጂበታለሽ። የእግዚአብሔር ባሪያዎች ርስት ይህ ነው፥ ጽድቃቸውም ከእኔ ዘንድ ነው፥ ይላል እግዚአብሔር።