ምዕራፍ 24
1፤ እነሆ፥ እግዚአብሔር ምድርን ባዶ ያደርጋታል፥ ባድማም ያደርጋታል፥ ይገለብጣትማል፥ በእርስዋም የተቀመጡትን ይበትናል።
2፤ እንደ ሕዝቡም እንዲሁ ካህኑ፥ እንደ ባሪያውም እንዲሁ ጌታው፥ እንደ ባሪያይቱም እንዲሁ እመቤትዋ፥ እንደሚገዛም እንዲሁ የሚሸጠው፥ እንደ አበዳሪውም እንዲሁ ተበዳሪው፥ እንደ ዕዳ አስከፋዩም እንዲሁ ዕዳ ከፋዩ ይሆናል።
3፤ ምድር መፈታትን ትፈታለች፥ ፈጽማም ትበላሻላች፤ እግዚአብሔር ይህን ቃል ተናግሮአልና።
4፤ ምድርም አለቀሰች ረገፈችም፤ ዓለም ደከመች ረገፈችም፤ የምድርም ሕዝብ ታላላቆች ደከሙ።
5፤ ምድርም ከሚቀመጡባት በታች ረክሳለች፥ ሕጉን ተላልፈዋልና፥ ሥርዓቱንም ለውጠዋልና፥ የዘላለሙንም ቃል ኪዳን አፍርሰዋልና።
6፤ ስለዚህ መርገም ምድርን ትበላለች በእርስዋም የተቀመጡ ይቀጣሉ፤ ስለዚህ የምድር ሰዎች ይቃጠላሉ ጥቂት ሰዎችም ይቀራሉ።
7፤ የወይን ጠጅ አለቀሰች፥ የወይን ንግድ ደከመች፥ ልባቸው ደስ ያለው ሁሉ ተከዙ።
8፤ የከበሮው ሐሤት ቀርቶአል፥ የደስተኞች ድምፅ ዝም ብሎአል፥ የመሰንቆ ደስታ ቀርቶአል።
9፤ እየዘፈኑም የወይን ጠጅን አይጠጡትም፥ የሚያሰክርም መጠጥ ለሚጠጡት መራራ ይሆናል።
10፤ ባድማ የሆነችው ከተማ ፈረሰች፤ ቤት ሁሉ ማንም እንዳይገባበት ተዘጋ።
11፤ ስለ ወይኑም ጠጅ በአደባባይ ጩኸት ይሆናል፤ ደስታ ሁሉ ጨልሞአል፥ የምድርም ሐሤት ፈርሶአል።
12፤ ከተማይቱም ባድማ ሆናለች፥ በርዋም በጥፋት ተመትቶአል።
13፤ የወይራን ዛፍ እንደ መምታት፥ ከወይንም መከር በኋላ ቃርሚያውን እንደ መልቀም፥ እንዲሁ በምድር መካከል በአሕዛብም መካከል ይሆናል።
14፤ እነዚህ ድምፃቸውን ያነሣሉ፥ እልልም ይላሉ፥ ስለ እግዚአብሔር ክብርም ከባሕር ይጣራሉ።
15፤ ስለዚህ እግዚአብሔርን በምሥራቅ፥ የእስራኤልንም አምላክ የእግዚአብሔርንም ስም በባሕር ደሴቶች አክብሩ።
16፤ ለጻድቁ ክብር ይሁን የሚለውን ዝማሬ ከምድር ዳርቻ ሰምተናል። እኔ ግን። ከሳሁ፥ ከሳሁ፥ ወዮልኝ! ወንጀለኞች ወንጅለዋል፤ ወንጀለኞች እጅግ ወንጅለዋል አልሁ።
17፤ በምድር ላይ የምትኖር ሆይ፥ ፍርሃትና ገደል ወጥመድም በአንተ ላይ አሉ።
18፤ የሰማይ መስኮቶች ተከፍተዋልና፥ የምድርም መሠረት ተናውጣለችና ከፍርሃት ድምፅ የሸሸ በገደል ይወድቃል፥ ከገደልም የወጣ በወጥመድ ይያዛል።
19፤ ምድር ተሰባበረች፥ ምድር ፈጽማ ደቀቀች፥ ምድር ተነዋወጠች።
20፤ ምድር እንደ ሰካር ሰው ትንገዳገዳለች፥ እንደ ዳስም ትወዛወዛለች፤ መተላለፍዋ ይከብድባታል፥ ትወድቅማለች ደግማም አትነሣም።
21፤ በዚያም ቀን እንደዚህ ይሆናል፤ እግዚአብሔር በከፍታ ያለውን ሠራዊት በከፍታ ላይ፥ በምድርም ያሉትን ነገሥታት በምድር ላይ ይቀጣቸዋል።
22፤ ግዞተኞች በጕድጓድ እንደሚከማቹ በአንድነት ይከማቻሉ፥ በግዞት ቤትም ውስጥ ተዘግተው ይኖራሉ፥ ከብዙ ቀንም በኋላ ይጐበኛሉ።
23፤ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔርም በጽዮን ተራራና በኢየሩሳሌም ላይ ይነግሣልና፥ በሽማግሌዎቹም ፊት ክብር ይሆናልና ጨረቃ ይታወካል ፀሐይም ያፍራል።