ምዕራፍ 26
1 በረዶ በበጋ ዝናብም በመከር እንዳይገባ፥ እንዲሁ ለሰነፍ ክብር አይገባውም።
2 እንደሚተላለፍ ድንቢጥ ወዲያና ወዲህም እንደሚበርር ጨረባ፥ እንዲሁ ከንቱ እርግማን በማንም ላይ አይደርስም።
3 አለንጋ ለፈረስ፥ ልጓም ለአህያ፥ በትርም ለሰነፍ ጀርባ ነው።
4 አንተ ደግሞ እርሱን እንዳትመስል ለሰነፍ እንደ ስንፍናው አትመልስለት።
5 ለራሱ ጠቢብ የሆነ እንዳይመስለው ለሰነፍ እንደ ስንፍናው መልስለት።
6 በሰነፍ መልእክተኛ እጅ ነገርን የሚልክ እግሮቹን ይቈርጣል ግፍንም ይጠጣል።
7 እንደሚንጠለጠሉ የአንካሳ እግሮች፥ እንዲሁም ምሳሌ በሰነፎች አፍ ነው።
8 ለሰነፍ ክብርን የሚሰጥ ድንጋይን በወንጭፍ እንደሚያስር ነው።
9 እሾህ በስካር እጅ እንደሚሰካ፥ እንዲሁ ምሳሌ በሰነፎች አፍ ነው።
10 ዋና ሠራተኛ ሁሉን ነገር ይሠራል፤ ሰነፍን የሚቀጥር ግን መንገድ አላፊውን እንደሚቀጥር ነው።
11 ወደ ትፋቱ እንደሚመለስ ውሻ ስንፍናውን የሚደግም ሰው እንዲሁ ነው።
12 ለራሱ ጠቢብ የሆነ የሚምስለውን ሰው አየኽውን? ከእርሱ ይልቅ ለሰነፍ ተስፋ አለው።
13 ታካች ሰው። አንበሳ በመንገድ አለ፤ አንበሳ በጎዳና አለ ይላል።
14 ሣንቃ በማጠፊያው ላይ እንደሚዞር፥ እንዲሁ ታካች ሰው በአልጋው ላይ ይመላለሳል።
15 ታካች ሰው እጁን ወደ ወጭት ያጠልቃል፤ ወደ አፉም ይመልሳት ዘንድ ለእርሱ ድካም ነው።
16 ታካች ሰው በጥበብ ከሚመልሱ ከሰባት ሰዎች ይልቅ ለራሱ ጠቢብ የሆነ ይመስለዋል።
17 አልፎ በሌላው ጥል የሚደባለቅ ውሻን በጅራቱ እንደሚይዝ ነው።
18 ትንታግንና ፍላጻን ሞትንም እንደሚወረውር እንደ ዕብድ ሰው፥
19 ባልንጀራውን የሚያታልል። በጨዋታ አደረግሁት የሚል ሰውም እንዲሁ ነው።
20 እንጨት ባለቀ ጊዜ እሳት ይጠፋል፤ ጆሮ ጠቢ በሌለበትም ዘንድ ጠብ ጸጥ ይላል።
21 ከሰል ፍምን እንጨትም እሳትን እንዲያበዛ፥ እንዲሁ ቍጡ ሰው ጠብን ያበዛል።
22 የጆሮ ጠቢ ቃል እንደ ጣፋጭ መብል ነው፥ እርሱም እስከ ሆድ ጕርጆች ድረስ ይወርዳል።
23 ክፋት በልቡ ሳለ ፍቅርን የሚናገር ከንፈር በብር ዝገት እንደ ተለበጠ የሸክላ ዕቅ ነው።
24 ጠላት በከንፈሩ ተስፋ ይሰጣል፥ በልቡ ግን ተንኰልን ያኖራል።
25 በልቡ ሰባት ርኵሰት አለበትና በቃሉ አሳምሮ ቢናገርህ አትመነው።
26 ጠላትነቱን በተንኰል የሚሸሽግ፥ ክፋቱ በጉባኤ መካከል ይገለጣል።
27 ጕድጓድን የሚምስ ይወድቅበታል፤ ድንጋይንም የሚያንከባልል ይገለበጥበታል።
28 ሐሰተኛ ምላስ ያቈሰላቸውን ሰዎች ይጠላል፤ ልዝብ አፍም ጥፋትን ያመጣል።