ምዕራፍ 16

1 የልብ መዘጋጀት ከሰው ነው፤ የምላስ መልስ ግን ከእግዚአብሔር ዘንድ ነው።
2 የሰው መንገድ ሁሉ በዓይኖቹ ፊት ንጹሕ ነው፤ እግዚአብሔር ግን መንፈስን ይመዝናል።
3 ሥራህን ለእግዚአብሔር አደራ ስጥ፥ አሳብህም ትጸናለች።
4 እግዚአብሔር ሁሉን ለእርሱ ለራሱ ፈጠረ፥ ኀጥእን ደግሞ ለክፉ ቀን።
5 በልቡ የታበየ ሁሉ በእግዚአብሔር ዘንድ ርኩስ ነው፥ እጅ በእጅም ሳይቀጣ አይቀርም።
6 በምሕረትና በእውነት ኃጢአት ትሰረያለች፥ እግዚአብሔርንም በመፍራት ሰው ከክፋት ይመለሳል።
7 የሰው አካሄድ እግዚአብሔርን ደስ ያሰኘው እንደ ሆነ፤ በእርሱና በጠላቶቹ መካከል ስንኳ ሰላምን ያደርጋል።
8 በጽድቅ የሚገኝ ጥቂት ነገር በዓመፅ ከሚገኝ ከብዙ ትርፍ ይሻላል።
9 የሰው ልብ መንገዱ ያዘጋጃል፤ እግዚአብሔር ግን አካሄዱን ያቀናለታል።
10 የእግዚአብሔር ብይን በንጉሥ አፍ ነው፥ አፉም በፍርድ አይስትም።
11 እውነተኛ ሚዛንና መመዘኛ የእግዚአብሔር ናቸው፤ የከረጢት መመዘኛዎች ሁሉ የእርሱ ሥራ ናቸው።
12 ግፍን መሥራት በንጉሥ ዘንድ ጸያፍ ነገር ነው፥ ዙፋን በጽድቅ ይጸናልና።
13 የጽድቅ ከንፈር የነገሥታት ደስታ ናት፥ በቅን የሚናገር እርሱንም ይወድዱታል።
14 የንጉሥ ቍጣ እንደ ሞት መልእክተኛ ነው፤ ጠቢብ ሰው ግን ያቈላምጠዋል።
15 በንጉሥ ፊት ብርሃን ዘንድ ሕይወት አለ፥ መልካም ፈቃዱም እንደ በልግ ዝናብ ደመና ነው።
16 ጥበብን ማግኘት ምንኛ ከወርቅ ይሻላል! ማስተዋልንም ማግኘት ከብር ይልቅ የሚመረጥ ነው።
17 የቅኖች መንገድ ከክፋት መራቅ ነው፤ መንገዱን የሚጠብቅ ነፍሱን ይጠብቃታል።
18 ትዕቢት ጥፋትን፥ ኵሩ መንፈስም ውድቀትን ይቀድማል።
19 ከዕቡያን ጋር ምርኮ ከመካፈል ከትሑታን ጋር በተዋረደ መንፈስ መሆን ይሻላል።
20 ቃልን የሚያዳምጥ መልካም ነገርን ያገኛል፤ በእግዚአብሔር የታመነ ምስጉን ነው።
21 ልቡ ጠቢብ የሆነ አስተዋይ ይባላል፥ በከንፈሩም ጣፋጭ የሆነ ትምህርትን ያበዛል።
22 ገንዘብ ላደረገው ሰው እውቀት የሕይወት ምንጭ ነው፤ ስንፍና ግን የሰነፎች ቅጣት ነው።
23 የጠቢብ ልብ አፉን ያስተምራል፥ ለከንፈሩም ትምህርትን ይጨምራል።
24 ያማረ ቃል የማር ወለላ ነው፤ ለነፍስ ጣፋጭ ለአጥንትም ጤና ነው።
25 ለሰው ቅን የምትመስል መንገድ አለች፤ ፍጻሜዋ ግን የሞት መንገድ ነው።
26 የሠራተኛ ራብ ለእርሱ ይሠራል፥ አፉ ይጐተጕተዋልና።
27 ምናምንቴ ሰው ክፋትን ይምሳል፥ በከንፈሩም የሚቃጠል እሳት አለ።
28 ጠማማ ሰው ጥልን ይዘራል፤ ጆሮ ጠቢ ሰው የተማመኑትን ወዳጆች ይለያያል።
29 ግፈኛ ሰው ወዳጁን ያባብላል፥ መልካምም ወዳይደለ መንገድ ይመራዋል።
30 ዓይኑን የሚዘጋ ጠማማ አሳብን ያስባል፤ ከንፈሩን የሚነክስ ክፋትን ይፈጽማል።
31 የሸበተ ጠጕር የክብር ዘውድ ነው፥ እርሱም በጽድቅ መንገድ ይገኛል።
32 ትዕግሥተኛ ሰው ከኃያል ሰው ይሻላል፥ በመንፈሱም ላይ የሚገዛ ከተማ ከሚወስዱ ይበልጣል።
33 ዕጣ በጕያ ይጣላል፤ መደብዋ ሁሉ ግን ከእግዚአብሔር ዘንድ ነው።