ምዕራፍ 5
1 ልጄ ሆይ፥ ወደ ጥበቤ አድምጥ፤ ጆሮህን ወደ ትምህርቴ መልስ፥
2 ጥንቃቄን ትጠብቅ ዘንድ ከንፈሮችህም እውቀትን እንዲጠብቁ።
3 ከጋለሞታ ሴት ከንፈር ማር ይንጠባጠባልና፥ አፍዋም ከቅቤ የለሰለሰ ነውና፤
4 ፍጻሜዋ ግን እንደ እሬት የመረረ ነው፥ ሁለት አፍ እንዳለው ሰይፍም የተሳለ ነው።
5 እግሮችዋ ወደ ሞት ይወርዳሉ፥ አረማመድዋም ወደ ሲኦል ነው፤
6 የቀና የሕይወትን መንገድ አታገኝም፤ በአካሄድዋ የተቅበዘበዘች ናት፥ የሚታወቅም አይደለም።
7 አሁንም ልጆቼ ሆይ፥ ስሙኝ፥ ከአፌም ቃል አትራቁ።
8 መንገድህን ከእርስዋ አርቅ፥ ወደ ቤትዋም ደጅ አትቅረብ፥
9 ክብርህ ለሌላ እንዳትሰጥ፥ ዕድሜህም ለጨካኝ፤
10 ሌሎች ከሀብትህ እንዳይጠግቡ፥ ድካምህም በባዕድ ሰው ቤት እንዳይሆን።
11 በመጨረሻም ሥጋህና ሰውነትህ በጠፋ ጊዜ ታለቅሳለህ፥
12 ትላለህም። እንዴት ትምህርትን ጠላሁ፥ ልቤም ዘለፋን ናቀ!
13 የአስተማሪዎቼንም ቃል አልሰማሁም፥ ጆሮቼንም ወደ አስተማሪዎቼ አላዘነበልሁም።
14 በማኅበርና በጉባኤ መካከል ወደ ክፉ ሁሉ ለመድረስ ጥቂት ቀረኝ።
15 ከጕድጓድህ ውኃ፥ ከምንጭህም የሚፈልቀውን ውኃ ጠጣ።
16 ምንጮችህ ወደ ሜዳ፥ ወንዞችህ ወደ አደባባይ፥ ይፈስሳሉን?
17 ለአንተ ብቻ ይሁኑ፥ ከአንተ ጋር ላሉ እንግዶችም አይሁኑ።
18 ምንጭህ ቡሩክ ይሁን፤ ከጕብዝናህም ሚስት ጋር ደስ ይበልህ።
19 እንደ ተወደደች ዋላ እንደ ተዋበችም ሚዳቋ፥ ጡትዋ ሁልጊዜ ታርካህ፥ በፍቅርዋም ሁልጊዜ ጥገብ።
20 ልጄ ሆይ፥ ስለ ምን ጋለሞታ ሴት ትወድዳለህ? የሌላይቱንስ ብብት ለምን ታቅፋለህ?
21 የሰው መንገድ በእግዚአብሔር ፊት ነውና፥ አካሄዱንም ሁሉ እርሱ ይመለከታልና።
22 ኃጥኣንን ኃጢአቱ ታጠምደዋለች፥ በኃጢአቱም ገመድ ይታሰራል።
23 አልተቀጣምና እርሱ ይሞታል፤ በስንፍናውም ብዛት ይስታል።