ምዕራፍ 22
1 መልካም ስም ከብዙ ባለጠግነት ይሻላል፥ መልካምም ሞገስ ከብርና ከወርቅ ይበልጣል።
2 ባለጠና ድሀ ተገናኙ፤ እግዚአብሔር የሁላቸው ፈጣሪ ነው።
3 ብልህ ሰው ክፉን አይቶ ይሸሸጋል፤ አላዋቂዎች ግን አልፈው ይጐዳሉ።
4 ትሕትናና እግዚአብሔርን መፍራት ባለጠግነት ክብር ሕይወትም ነው።
5 እሾህና ወጥመድ በጠማማ ሰው መንገድ ናቸው፤ ነፍሱን ግን የሚጠብቅ ከእነርሱ ይርቃል።
6 ልጅን በሚሄድበት መንገድ ምራው፥ በሸመገለም ጊዜ ከእርሱ ፈቀቅ አይልም።
7 ባለጠጋ ድሆችን ይገዛል፥ ተበዳሪም የአበዳሪ ባሪያ ነው።
8 ኃጢአትን የሚዘራ መከራን ያጭዳል፥ የቍጣውም በትር ይጠፋል።
9 ርኅሩህ የተባረከ ይሆናል፥ ከእንጀራው ለድሀ ሰጥቶአልና።
10 ፌዘኛን ብታወጣ ክርክር ይወጣል፥ ጠብና ስድብም ያልቃል።
11 የልብን ንጽሕና የሚወድድና ሞገስ በከንፈሩ ያለች፥ ንጉሥ ወዳጁ ይሆናል።
12 የእግዚአብሔር ዓይኖች እውቀትን ይጠብቃሉ፤ እርሱ ግን የወስላታውን ቃል ይገለብጣል።
13 ታካች ሰው። አንበሳ በሜዳ ነው፤ በመንገዱ ላይ እሞታለሁ ይላል።
14 የጋለሞታ ሴት አፍ የጠለቀ ጕድጓድ ነው፤ እግዚአብሔር የተቈጣው በእርስዋ ይወድቃል።
15 ስንፍና በሕፃን ልብ ታስሮአል፤ የተግሣጽ በትር ግን ከእርሱ ያርቃታል።
16 ለራሱ ጥቅም ለመጨመር ሲል ድሀን የሚጐዳ፥ ለባለጠጋም የሚሰጥ፥ እርሱ ወደ ድህነት ይወድቃል።
17 ጆሮህን አዘንብለህ የጠቢባንን ቃላት ስማ፥ ልብህንም ወደ እውቀቴ አድርግ፤
18 እነርሱን በውስጥህ ብትጠብቅ፥ በከንፈሮችህም ላይ የተዘጋጁ ቢሆኑ፥ የተወደደ ነገር ይሆንልሃልና።
19 እምነትህ በእግዚአብሔር ይሆን ዘንድ ለአንተ ዛሬ እነሆ አስታወቅሁህ።
20-
21 የእውነትን ቃል እርግጥነት አስታውቅህ ዘንድ፥ ለሚጠይቅህም እውነትን ቃል መመለስ ይቻልህ ዘንድ፥ በምክርና በእውቀት የከበረን ነገር አልጻፍሁልህምን?
22 ድሀን በግድ አትበለው ድሀ ነውና፤ ችግረኛውንም በበር አትግፋው፤
23 እግዚአብሔር የእነርሱን ፍርድ ይፋረድላቸዋልና፥ የቀሙአቸውንም ሰዎች ሕይወት ይቀማልና።
24 ከቍጡ ሰው ጋር ባልንጀራ አትሁን፥ ከወፈፍተኛም ጋት አትሂድ፥
25 መንገዱን እንዳትማር ለነፍስህም ወጥመድ እንዳታገኝህ።
26 እጃቸውን አጋና እንደሚማቱ፥ ለባለ ዕዳዎች እንደሚዋሱ አትሁን፤
27 የምትከፍለው ባይኖርህ፥ ምንጣፍህን ከበታችህ ስለ ምን ይወስዳል?
28 አባቶችህ የሠሩትን የቀድሞውን የድንበር ምልክት አታፍልስ።
29 በሥራው የቀጠፈ ሰውን አይተሃልን? በነገሥታት ፊት ይቆማል፤ በተዋረዱም ሰዎች ፊት አይቆምም።