ምዕራፍ 9
1፤ የእግዚአብሔር ቃል ሸክም በሴድራክ ምድር ላይ ነው፥ በደማስቆም ላይ ያርፋል፤ የእግዚአብሔር ዓይን ወደ ሰውና ወደ እስራኤል ነገድ ሁሉ ዘንድ ነው፤
2፤ ደግሞም በዳርቻዋ ባለችው በሐማት ላይ፥ እጅግ ጠቢበኞች በሆኑ በጢሮስና በሲዶና ላይ ነው።
3፤ ጢሮስም ምሽግን ለራስዋ ሠርታለች፥ ብሩንም እንደ አፈር ጥሩውንም ወርቅ እንደ መንገድ ጭቃ አከማችታለች።
4፤ እነሆ፥ ጌታ ይገፍፋታል፥ በባሕርም ላይ ያለውን ብርታትዋን ይመታል፤ እርስዋም በእሳት ትበላለች።
5፤ አስቀሎና አይታ ትፈራለች፤ ጋዛ ደግሞ አይታ እጅግ ትታመማለች፤ አቃሮንም እንዲሁ፥ ተስፋዋ ይቈረጣልና፤ ንጉሡም ከጋዛ ይጠፋል፥ በአስቀሎናም የሚቀመጥ አይገኝም።
6፤ የተደባለቀ ወገን በአዛጦን ይቀመጣል፥ የፍልስጥኤማውያንንም ትዕቢት አጠፋለሁ።
7፤ ደሙንም ከአፉ ውስጥ ርኩሱንም ነገር ከጥርሱ መካከል አስወግዳለሁ፤ እርሱም ደግሞ ለአምላካችን ቅሬታ ይሆናል፤ በይሁዳም እንደ አለቃ ይሆናል፥ አቃሮንም እንደ ኢያቡሳዊ ይሆናል።
8፤ እኔም ማንም እንዳይሄድና እንዳይመለስ እንደ ጠባቂ ጦር ሆኖ በቤቴ ዙሪያ ሰፈር አደርጋለሁ፤ አሁንም በዓይኔ አይቻለሁና ከዚህ በኋላ አስጨናቂ አያልፍባቸውም።
9፤ አንቺ የጽዮን ልጅ ሆይ፥ እጅግ ደስ ይበልሽ፤ አንቺ የኢየሩሳሌም ልጅ ሆይ፥ እልል በዪ፤ እነሆ፥ ንጉሥሽ ጻድቅና አዳኝ ነው፤ ትሑትም ሆኖ በአህያም፥ በአህያይቱ ግልገል በውርጫይቱ ላይ ተቀምጦ ወደ አንቺ ይመጣል።
10፤ ሰረገላውንም ከኤፍሬም ፈረሱንም ከኢየሩሳሌም አጠፋለሁ፤ የሰልፉም ቀስት ይሰበራል፥ ለአሕዛብም ሰላምን ይናገራል፤ ግዛቱም ከባሕር እስከ ባሕር፥ ከወንዙም እስከ ምድር ዳርቻ ድርስ ይሆናል።
11፤ ለአንቺም ደግሞ ስለ ቃል ኪዳንሽ ደም፥ እስሮችሽን ውኃ ከሌለበት ጕድጓድ አውጥቻለሁ።
12፤ እናንተ በተስፋ የምትኖሩ እስሮች ሆይ፥ ወደ ጽኑ አምባ ተመለሱ፤ ሁለት እጥፍ አድርጌ እንድመልስልሽ ዛሬ እነግርሻለሁ።
13፤ ይሁዳን ለእኔ ገትሬአለሁ፤ ቀስቱን በኤፍሬም ሞልቼአለሁ፤ ጽዮን ሆይ፥ ልጆችሽን በግሪክ ልጆች ላይ አስነሣለሁ፥ አንቺንም እንደ ኃያል ሰው ሰይፍ አደርግሻለሁ።
14፤ እግዚአብሔርም በእነርሱ ላይ ይገለጣል፥ ፍላጻውም እንደ መብረቅ ይወጣል፤ ጌታ እግዚአብሔርም መለከትን ይነፋል፥ በደቡብም ዐውሎ ነፋስ ይሄዳል።
15፤ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ይጠብቃቸዋል፤ እነርሱም ይበሉአቸዋል፥ የወንጭፉንም ድንጋዮች ይረግጣሉ፤ እንደ ወይን ጠጅም ይጠጡአቸዋል፥ እንደ ጥዋዎችም እንደ መሠዊያም ማዕዘኖች የተሞሉ ይሆናሉ።
16፤ በዚያም ቀን አምላካቸው እግዚአብሔር እንደ ሕዝቡ መንጋ ያድናቸዋል፤ እነርሱም ለአክሊል እንደሚሆኑ እንደ ከበሩ ድንጋዮች ይሆናሉ፥ በምድሩም ላይ ይብለጨለጫሉ።
17፤ በጎነቱ እንዴት ታላቅ ነው! ውበቱስ እንዴት ታላቅ ነው! እህል ጐበዛዝቱን፥ ጉሽ ጠጅም ቈነጃጅቱን ያለመልማል።