ትንቢተ ዘካርያስ - Zechariah

ምዕራፍ: 1 2 3 4 5 6 7 8 9 10 11 12 13 14


ምዕራፍ 11

1፤ ሊባኖስ ሆይ፥ ደጆችህን ክፈት፥ እሳትም ዝግባዎችህን ትብላ።
2፤ የጥድ ዛፍ ሆይ፥ ዝግባ ወድቆአልና፥ ከበርቴዎችም ጠፍተዋልና ዋይ በል፤ እናንተም የባሳን ዛፎች ሆይ፥ ጽኑው ጫካ ተቈርጦአልና ዋይ በሉ።
3፤ የእረኞች ክብር ተዋርዶአልና የዋይታቸው ድምፅ ተሰምቶአል፤ የዮርዳኖስ ትዕቢት ተዋርዶአልና የአንበሶች ግሣት ድምፅ ተሰምቶአል።
4፤ አምላኬ እግዚአብሔር እንዲህ ብሎአል። ለእርድ የሚሆኑትን በጎች ጠብቅ።
5፤ የገዙአቸው ያርዱአቸዋል፥ ራሳቸውንም እንደ በደለኞች አድርገው አይቈጥሩም፤ የሸጡአቸውም። ባለ ጠጋ ሆነናልና እግዚአብሔር ይመስገን ይላሉ፤ እረኞቻቸውም አይራሩላቸውም።
6፤ ከእንግዲህ ወዲህ በምድር ላይ ለሚኖሩ አልራራም፥ ይላል እግዚአብሔር፤ እነሆም፥ ሰውን ሁሉ በባልንጀራውና በንጉሡ እጅ አሳልፌ እሰጣለሁ፤ ምድሪቱንም ይመታሉ፥ ከእጃቸውም አላድናቸውም።
7፤ እኔም ለእርድ የሚሆኑትን በጎች፥ የመንጋውን ችግረኞች ጠበቅሁ። ሁለት በትሮችንም ወሰድሁ፤ የአንዲቱን ስም ውበት የሁለተኛይቱንም ስም ማሰሪያ ብዬ ጠራሁ፤ መንጋውንም ጠበቅሁ።
8፤ በአንድ ወርም ሦስቱን እረኞች አጠፋሁ፤ ነፍሴም ተሰቀቀቻቸው፥ ነፍሳቸውም ደግሞ እኔን ጠላች።
9፤ እኔም። እናንተን አልጠብቅም፤ የሚሞተው ይሙት፥ የሚጠፋውም ይጥፋ፤ የቀረውም እያንዳንዱ የባልንጀራውን ሥጋ ይብላ አልሁ።
10፤ እኔም ከሕዝቦች ሁሉ ጋር የገባሁትን ቃል ኪዳኔን አፈርስ ዘንድ ውበት የተባለችውን በትሬን ወስጄ ቈረጥሁ።
11፤ በዚያም ቀን ተሰበረች፤ እንዲሁም እኔን የተመለከቱ የመንጋው ችግረኞች የእግዚአብሔር ቃል እንደ ነበረ አወቁ።
12፤ እኔም። ደስ ብሎአችሁ እንደ ሆነ ዋጋዬን ስጡኝ፤ ያለዚያ ግን ተዉት አልሁ። እነርሱም ለዋጋዬ ሠላሳ ብር መዘኑ።
13፤ እግዚአብሔርም። የተስማሙበትን የከበረውን ዋጋዬን በግምጃ ቤቱ ውስጥ አኑረው አለኝ። እኔም ሠላሳውን ብር ወስጄ በእግዚአብሔር ቤት ባለው በግምጃ ቤቱ ውስጥ አኖርሁት።
14፤ በይሁዳና በእስራኤል መካከል ያለውንም ወንድማማችነት እሰብር ዘንድ ማሰሪያ የተባለችውን ሁለተኛይቱን በትሬን ቈረጥሁ።
15፤ እግዚአብሔርም እንዲህ አለኝ። ዳግመኛም የሰነፍን እረኛ ዕቃ ውሰድ።
16፤ እነሆ፥ በአገሩ ውስጥ እረኛ አስነሣለሁ፤ እርሱም የጠፋውን አያስብም፥ የባዘነውን አይፈልግም፥ የተሰበረውን አይጠግንም፤ የዳነውንም አይቀልብም፥ ነገር ግን የሰባውን ሥጋ ይበላል፥ ሰኰናውንም ይቀለጣጥማል።
17፤ መንጋውን ለሚተው ለምናምንቴ እረኛ ወዮለት! ሰይፍ በክንዱና በቀኝ ዓይኑ ላይ ይሆናል፤ ክንዱም አጥብቃ ትደርቃለች፥ ቀኝ ዓይኑም ፈጽሞ ትጨልማለች።