ትንቢተ ዘካርያስ - Zechariah

ምዕራፍ: 1 2 3 4 5 6 7 8 9 10 11 12 13 14


ምዕራፍ 7

1፤ በንጉሡም በዳርዮስ በአራተኛው ዓመት ካሴሉ በሚባል በዘጠነኛው ወር በአራተኛው ቀን የእግዚአብሔር ቃል ወደ ዘካርያስ መጣ።
2፤ የቤቴልም ሰዎች ሳራሳርንና ሬጌሜሌክን ሰዎቻቸውንም በእግዚአብሔር ፊት ይለምኑ ዘንድ፥
3፤ ለሠራዊት ጌታ ለእግዚአብሔር ቤት ካህናት ለነቢያትም። ባለፉት ዓመታት እንዳደረግሁት በአምስተኛው ወር መለየትና ማልቀስ ይገባኛልን? ብለው ይናገሩ ዘንድ ልኮአቸው ነበር።
4፤ የሠራዊትም ጌታ የእግዚአብሔር ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ።
5፤ ለምድሩ ሕዝብ ሁሉ ለካህናትም እንዲህ ብለህ ተናገራቸው። በዚህ በሰባው ዓመት በአምስተኛውና በሰባተኛው ወር በጾማችሁና ባለቀሳችሁ ጊዜ፥ በውኑ ለእኔ ጾም ጾማችሁልኝ?
6፤ በምትበሉበትና በምትጠጡበትስ ጊዜ፥ ለራሳችሁ የምትበሉና የምትጠጡ አይደላችሁምን?
7፤ ኢየሩሳሌምና በዙሪያዋ ያሉ ከተሞች ገና ሰዎች ባሉባቸው ጊዜ፥ በምቾትም ተቀምጠው ሳሉ፥ ደቡቡና ቈላውም ሰዎች ባሉባቸው ጊዜ፥ እግዚአብሔር በቀደሙት ነቢያት እጅ የተናገረውን ቃል መስማት አይገባችሁምን?
8፤ የእግዚአብሔርም ቃል ወደ ዘካርያስ እንዲህ ሲል መጣ።
9፤ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ብሎ ተናግሮአል። እውነተኛውን ፍርድ ፍረዱ፤ ቸርነትንና ምሕረትን ሁላችሁ ለወንድሞቻችሁ አድርጉ፤
10፤ መበለቲቱንና ድሀ አደጉን፥ መጻተኛውንና ችግረኛውን አትበድሉ፤ ከእናንተም ማንም በወንድሙ ላይ ክፉውን ነገር በልቡ አያስብ።
11፤ እነርሱ ግን ደንደሳቸውን አዞሩ እንጂ መስማትን እምቢ አሉ፤ እንዳይሰሙም ጆሮአቸውን አደነቈሩ።
12፤ የሠራዊትም ጌታ እግዚአብሔር በቀደሙት ነቢያት እጅ በመንፈሱ የላከውን ሕጉንና ቃሉን እንዳይሰሙ ልባቸውን እንደ አልማዝ አጠነከሩ፤ ስለዚህ ከሠራዊት ጌታ ከእግዚአብሔር ዘንድ ታላቅ ቍጣ መጣ።
13፤ እኔ በጠራሁ ጊዜ እነርሱ እንዳልሰሙኝ፥ እንዲሁ እነርሱ በሚጠሩበት ጊዜ እኔ አልሰማም፥ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር፤
14፤ ወደማያውቁአቸውም አሕዛብ ሁሉ በዐውሎ ነፋስ በተንኋቸው። እንዲሁ ከእነርሱ በኋላ ምድሪቱ ባድማ ሆናለች፥ የሚተላለፍባትና የሚመላለስባትም አልነበረም፤ ያማረችውንም ምድር ባድማ አደረጉአት።