ምዕራፍ 4
1፤ ከእኔም ጋር ይነጋገር የነበረው መልአክ ተመልሶ ከእንቅልፉ እንደሚነቃ ሰው አነቃኝ።
2፤ እርሱም። የምታየው ምንድር ነው? አለኝ። እኔም። እነሆ፥ ሁለንተናው ወርቅ የሆነውን መቅረዝ አየሁ፤ የዘይትም ማሰሮ በራሱ ላይ ነበረ፥ ሰባትም መብራቶች ነበሩበት፤ በራሱም ላይ ለነበሩት መብራቶች ሰባት ቧንቧዎች ነበሩአቸው።
3፤ ሁለት የወይራ ዛፎች፥ አንዱ በማሰሮው በስተ ቀኝ አንዱም በስተ ግራው ሆነው፥ በአጠገቡ ነበሩ አልሁ።
4፤ ከእኔ ጋር ይነጋገር ለነበረውም መልአክ መልሼ። ጌታዬ ሆይ፥ እነዚህ ምንድር ናቸው? አልሁት።
5፤ ከእኔ ጋር ይነጋገር የነበረውም መልአክ መልሶ። እነዚህ ምን እንደ ሆኑ አታውቅምን? አለኝ። እኔም። ጌታዬ ሆይ፥ አላውቅም አልሁ።
6፤ መልሶም። ለዘሩባቤል የተባለው የእግዚአብሔር ቃል ይህ ነው። በመንፈሴ እንጂ በኃይልና በብርታት አይደለም፥ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር።
7፤ ታላቅ ተራራ ሆይ፥ አንተ ምንድር ነህ? በዘሩባቤል ፊት ደልዳላ ሜዳ ትሆናለህ፤ ሰዎችም። ሞገስ፥ ሞገስ ይሁንለት ብለው እየጮኹ እርሱ መደምደሚያውን ድንጋይ ያወጣል ብሎ ተናገረኝ።
8፤ የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ።
9፤ የዘሩባቤል እጆች ይህን ቤት መሠረቱ፥ የእርሱም እጆች ይፈጽሙታል፤ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔርም ወደ እናንተ እንደ ላከኝ ታውቃላችሁ።
10፤ የጥቂቱን ነገር ቀን የናቀ ማን ነው? እነዚህ ሰባቱ ደስ ብሎአቸው በዘሩባቤል እጅ ቱንቢውን ያያሉ፤ እነዚህም በምድር ሁሉ የሚዘዋወሩ የእግዚአብሔር ዓይኖች ናቸው።
11፤ እኔም መልሼ። በመቅረዙ በስተ ቀኝና በስተ ግራ ያሉ እነዚህ ሁለት የወይራ ዛፎች ምንድር ናቸው? አልሁት።
12፤ ሁለተኛም መልሼ። በሁለቱ የወርቅ ቧንቧዎች አጠገብ ሆነው የወርቁን ዘይት የሚያፈስሱ እነዚህ ሁለት የወይራ ቅርንጫፎች ምንድር ናቸው? አልሁት።
13፤ እርሱም መልሶ። እነዚህ ምን እንደ ሆኑ አታውቅምን? አለኝ። እኔም ። ጌታዬ ሆይ፥ አላውቅም አልሁት።
14፤ እርሱም። በምድር ሁሉ ጌታ አጠገብ የቆሙት ሁለቱ የተቀቡት እነዚህ ናቸው አለኝ።