ምዕራፍ 15
1፤ ከዚህም በኋላ አቤሴሎም ሰረገላና ፈረሶች፥ በፊቱም የሚሮጡ አምሳ ሰዎች አዘጋጀ።
2፤ አቤሴሎምም በማለዳ ተነሥቶ በበሩ አደበባይ ይቆም ነበር፤ አቤሴሎምም ከንጉሥ ለማስፈረድ ጉዳይ የነበረውን ሁሉ ወደ እርሱ እየጠራ። አንተ ከወዴት ከተማ ነህ? ብሎ ይጠይቅ ነበር። እርሱም። እኔ ባሪያህ ከእስራኤል ነገድ ከአንዲቱ ነኝ ብሎ ይመልስ ነበር።
3፤ አቤሴሎምም። ነገርህ እውነትና ቅን ነው፤ ነገር ግን ከንጉሥ ታዝዞ የሚሰማህ የለም ይለው ነበር።
4፤ አቤሴሎምም። ነገርና ክርክር ያለው ሁሉ ወደ እኔ ይመጣ ዘንድ ቅንም ፍርድ እፈርድለት ዘንድ በአገር ላይ ፈራጅ አድርጎ ማን በሾመኝ? ይል ነበር።
5፤ ሰውም እጅ ሊነሣው ወደ እርሱ በቀረበ ጊዜ እጁን ዘርግቶ ይይዝና ይስመው ነበር።
6፤ እንዲሁም አቤሴሎም ከንጉሥ ፍርድ ሊሰማ ከእስራኤል ዘንድ በሚመጣ ሁሉ ያደርግ ነበር፤ አቤሴሎምም የእስራኤልን ሰዎች ልብ ሰረቀ።
7፤ እንዲህም ሆነ፤ ከአራት ዓመት በኋላ አቤሴሎም ንጉሡን። ለእግዚአብሔር የተሳልሁትን ስእለት ለመስጠት ወደ ኬብሮን፥ እባክህ፥ ልሂድ።
8፤ እኔ ባሪያህ በሶርያ ጌሹር ሳለሁ። እግዚአብሔር ወደ ኢየሩሳሌም ቢመልሰኝ ለእግዚአብሔር መሥዋዕት አቀርባለሁ ብዬ ስእለት ተስዬ ነበር አለው።
9፤ ንጉሡም። በደኅና ሂድ አለው፤ ተነሥቶም ወደ ኬብሮን ሄደ።
10፤ አቤሴሎምም በእስራኤል ነገድ ሁሉ። የቀንደ መለከት ድምፅ በሰማችሁ ጊዜ። አቤሴሎም በኬብሮን ነገሠ በሉ የሚሉ ጕበኞች ላከ።
11፤ የተጠሩትም ሁለት መቶ ሰዎች ከአቤሴሎም ጋር በየዋህነት ከኢየሩሳሌም ሄዱ፤ የሚሆነውንም ነገር ከቶ አያውቁም ነበር።
12፤ አቤሴሎምም የዳዊት መካር የነበረውን የጊሎ ሰው አኪጦፌልን ከከተማው ከጊሎ መሥዋዕት በሚያቀርብበት ጊዜ አስጠራው። ሴራውም ጽኑ ሆነ፤ ከአቤሴሎምም ጋር ያለ ሕዝብ እየበዛ ሄደ።
13፤ ለዳዊትም። የእስራኤል ሰዎች ልብ ከአቤሴሎም ጋር ሆኖአል የሚል ወሬኛ መጣለት።
14፤ ዳዊትም ከእርሱ ጋር በኢየሩሳሌም ያሉትን ባሪያዎቹን ሁሉ። ተነሡ፥ እንሽሽ ያለዚያ ከአቤሴሎም እጅ የሚድን ከእኛ የለምና፤ መጥቶም እንዳይዘን፥ ክፉም እንዳያመጣብን ከተማይቱንም በሰይፍ ስለት እንዳይመታ ፈጥናችሁ እንሂድ አላቸው።
15፤ የንጉሡም ባሪያዎች ንጉሡን። እነሆ፥ ጌታችን ንጉሡ የመረጠውን ሁሉ እኛ ባሪያዎችህ እሺ ብለን እናደርጋለን አሉት።
16፤ ንጉሡም ከእርሱም በኋላ ቤተ ሰቡ ሁሉ ወጡ፤ ንጉሡም አሥሩን ሴቶች ቁባቶቹን ቤቱን ይጠብቁ ዘንድ ተወ።
17፤ ንጉሡም ከእርሱም በኋላ ሕዝቡ ሁሉ ወጡ፥ በቤትሜርሐቅም ቆሙ።
18፤ ባሪያዎቹም ሁሉ በፊቱ አለፉ፤ ከሊታውያንና ፈሊታውያንም ሁሉ፥ ከእርሱም በኋላ ከጌት የመጡት ስድስት መቶው ጌትያውን ሁሉ በንጉሡ ፊት አለፉ።
19፤ ንጉሡም የጌት ሰው ኢታይን። ከእኛ ጋር ለምን መጣህ? አንተ ከስፍራህ የመጣህ እንግዳና ስደተኛ ነህና ተመለስ፥ ከንጉሡም ጋር ተቀመጥ።
20፤ የመጣኸው ትናንት ነው፤ ዛሬ ከእኛ ጋር ላዙርህን? እኔ ወደምሄድበት እሄዳለሁ፤ አንተ ግን ተመለስ፥ ወንድሞችህንም ከአንተ ጋር ውሰድ፥ እግዚአብሔርም ምሕረቱንና እውነቱን ያድርግልህ አለው።
21፤ ኢታይም ለንጉሡ መልሶ። ሕያው እግዚአብሔርን! በጌታዬም በንጉሡ ሕይወት እምላለሁ! በእውነት ጌታዬ ባለበት ስፍራ ሁሉ፥ በሞትም ቢሆን በሕይወትም፥ በዚያ ደግሞ እኔ ባሪያህ እሆናለሁ አለው።
22፤ ዳዊትም ኢታይን። ሂድ ተሻገር አለው፤ የጌት ሰው ኢታይና ሰዎቹም ሁሉ፥ ከእርሱም ጋር የነበሩት ሕፃናት ሁሉ ተሻገሩ።
23፤ በአገርም የነበሩት ሁሉ በታላቅ ድምፅ አለቀሱ፤ ሕዝቡም ሁሉ ተሻገሩ፥ ንጉሡም ደግሞ የቄድሮንን ፈፋ ተሻገረ፤ ሕዝቡም ሁሉ ወደ ምድረ በዳ መንገድ ተሻገሩ።
24፤ እነሆም፥ ደግሞ ሳዶቅ ከእርሱም ጋር ሌዋውያን ሁሉ የእግዚአብሔርን ቃል ኪዳን ታቦት ተሸክመው መጡ፤ የእግዚአብሔርንም ታቦት አስቀመጡ፥ ሕዝቡም ሁሉ ከከተማይቱ ፈጽሞ እስኪያልፍ ድረስ አብያታር ወጣ።
25፤ ንጉሡም ሳዶቅን። የእግዚአብሔርን ታቦት ወደ ከተማ መልስ፤ በእግዚአብሔር ዓይን ሞገስ አግኝቼ እንደ ሆንሁ፥ መልሶ እርሱንና ማደሪያውን ያሳየኛል፤
26፤ ነገር ግን። አልወድድህም ቢለኝ፥ እነሆኝ፥ ደስ የሚያሰኘውን ያድርግብኝ አለው።
27፤ ንጉሡም ደግሞ ካህኑን ሳዶቅን። እነሆ፥ አንተና ልጅህ አኪማአስ የአብያታርም ልጅ ዮናታን ሁለቱ ልጆቻችሁ በደኅና ወደ ከተማ ተመለሱ።
28፤ እኔም፥ እነሆ፥ ከእናንተ ዘንድ ወሬ እስኪመጣልኝ ድረስ በምድረ በዳው መሻገርያ እቆያለሁ አለው።
29፤ ሳዶቅም አብያታርም የእግዚአብሔርን ታቦት ወደ ኢየሩሳሌም መለሱት፥ በዚያም ተቀመጡ።
30፤ ዳዊትም ተከናንቦ ያለ ጫማ እያለቀሰ ወደ ደብረ ዘይት ዐቀበት ወጣ፤ ከእርሱም ጋር የነበሩት ሕዝብ ሁሉ ተከናንበው እያለቀሱ ወጡ።
31፤ አኪጦፌል ከአቤሴሎም ጋር በሴራ አንድ ነው ብለው ለዳዊት ነገሩት፤ ዳዊትም። አቤቱ፥ የአኪጦፌልን ምክር ስንፍና አድርገህ እንድትለውጥ እለምንሃለሁ አለ።
32፤ ዳዊትም ለእግዚአብሔር ወደ ሰገደበት ወደ ተራራው ራስ በመጣ ጊዜ፥ አርካዊው ኩሲ ልብሱን ቀድዶ በራሱም ላይ ትቢያ ነስንሶ ሊገናኘው መጣ።
33፤ ዳዊትም አለው። ከእኔ ጋር ብትመጣ ትከብደኛለህ፤
34፤ ወደ ከተማ ግን ተመልሰህ ለአቤሴሎም። ንጉሥ ሆይ፥ ባሪያ እሆንሃለሁ፤ አስቀድሞ ለአባትህ ባሪያ እንደ ነበርሁ እንዲሁ አሁን ለአንተ ባሪያ እሆንሃለሁ ብትለው የአኪጦፌልን ምክር ከንቱ ታደርግልኛለህ።
35፤ ካህናቱ ሳዶቅና አብያታርም በዚያ ከአንተ ጋር አይደሉምን? ከንጉሡ ቤትም የምትሰማውን ነገር ሁሉ ለካህናቱ ለሳዶቅና ለአብያታር ንገራቸው።
36፤ እነሆ፥ የሳዶቅ ልጅ አኪማአስና የአብያታር ልጅ ዮናታን ልጆቻቸው በዚያ ከእነርሱ ጋር አሉ፤ የምትሰሙትን ሁሉ በእነርሱ እጅ ላኩልኝ።
37፤ የዳዊትም ወዳጅ ኩሲ ወደ ከተማ መጣ፤ አቤሴሎምም ደግሞ ወደ ኢየሩሳሌም ገባ።