ምዕራፍ 22
1፤ ዳዊትም እግዚአብሔር ከሳኦል እጅና ከጠላቶቹ እጅ ሁሉ ባዳነው ቀን የዚህን ቅኔ ቃል ለእግዚአብሔር ተናገረ።
2፤ እንዲህም አለ። እግዚአብሔር ዓለቴ አምባዬ መድኃኒቴ ነው፤
3፤ እግዚአብሔር ጠባቂዬ ነው፥ በእርሱም እታመናለሁ፤ ጋሻዬና የረድኤቴ ቀንድ፥ መጠጊያዬና መሸሸጊያዬ፥ መድኃኒቴ ሆይ፥ ከግፍ ሥራ ታድነኛለህ።
4፤ ምስጋና የሚገባውን እግዚአብሔርን እጠራለሁ፤ ከጠላቶቼም እድናለሁ።
5፤ የሞት ጣር ያዘኝ፤ የዓመፅ ፈሳሽም አስፈራኝ፤
6፤ የሲኦል ጣር ከበበኝ፤ የሞት ወጥመድ ደረሰብኝ።
7፤ በጨነቀኝ ጊዜ እግዚአብሔርን ጠራሁት፥ ወደ አምላኬም ጮኽሁ፤ ከመቅደሱም ቃሌን ሰማኝ፥ ጩኸቴም በፊቱ ወደ ጆሮው ገባ።
8፤ ምድርም ተንቀጠቀጠች፥ ተናወጠችም፥ የሰማዮችም መሠረቶች ተነቃነቁ፤ እግዚአብሔርም ተቈጥቶአልና ተንቀጠቀጡ።
9፤ ከቍጣው ጢስ ወጣ፥ ከአፉም የሚበላ እሳት ነደደ፤ ፍምም ከእርሱ በራ።
10፤ ሰማዮችን ዝቅ ዝቅ አደረገ፥ ወረደም፤ ጨለማም ከእግሩ በታች ነበረ።
11፤ በኪሩብም ላይ ተቀምጦ በረረ፤ በነፋስም ክንፍ ሆኖ ታየ፤
12፤ መሰወርያውን ጨለማ፥ በዙሪያውም የነበረውን ድንኳን፥ በደመና ውስጥ የነበረ የጨለማ ውኃ አደረገ።
13፤ በፊቱም ካለው ብርሃን የተነሣ ፍም ተቃጠለ።
14፤ እግዚአብሔርም ከሰማያት አንጐደጐደ፥ ልዑልም ቃሉን ሰጠ፤
15፤ ፍላጻውን ላከ፥ በተናቸውም መብረቆችን ላከ፥ አወካቸውም።
16፤ ከእግዚአብሔር ዘለፋ፥ ከመዓቱም መንፈስ እስትንፋስ የተነሣ፥ የባሕር ፈሳሾች ታዩ፥ የዓለም መሠረቶችም ተገለጡ።
17፤ ከላይ ሰደደ፥ ወሰደኝም፤ ከብዙ ውኆችም አወጣኝ።
18፤ ከብርቱዎች ጠላቶቼ፥ ከሚጠሉኝም አዳነኝ፤ በርትተውብኝ ነበርና።
19፤ በመከራዬ ቀን ደረሱብኝ፤ እግዚአብሔር ግን ደገፋዬ ሆነ።
20፤ ወደ ሰፊ ስፍራም አወጣኝ፤ ወድዶኛልና አዳነኝ።
21፤ እግዚአብሔር እንደ ጽድቄ ይከፍለኛል፤ እንደ እጄ ንጽሕና ይመልስልኛል፤
22፤ የእግዚአብሔርን መንገድ ጠብቄአለሁና፥ በአምላኬም አላመፅሁምና።
23፤ ፍርዱ ሁሉ በፊቴ ነበረና፤ ከሥርዓቱም አልራቅሁምና።
24፤ በእርሱ ዘንድ ቅን ነበርሁ፥ ከኃጢአቴም ተጠበቅሁ።
25፤ እግዚአብሔርም እንደ ጽድቄ፥ እንደ እጄም ንጽሕና በዓይኖቹ ፊት መለሰልኝ።
26፤ ከቸር ሰው ጋር ቸር ሆነህ ትገኛለህ፤ ከቅን ሰው ጋር ቅን ሆነህ ትገኛለህ፤
27፤ ከንጹሕ ጋር ንጹሕ ሆነህ ትገኛለህ፤ ከጠማማም ጋር ጠማማ ሆነህ ትገኛለህ።
28፤ አንተ የተጠቃውን ሕዝብ ታድናለህና፤ የትዕቢተኞችን ዓይን ግን ታዋርዳለህ።
29፤ አቤቱ፥ አንተ መብራቴ ነህና፤ እግዚአብሔርም ጨለማዬን ያበራል።
30፤ በአንተ ኃይል በጭፍራ ላይ እሮጣለሁና፤ በአምላኬም ቅጥሩን እዘልላለሁና።
31፤ የአምላክ መንገድ ፍጹም ነው፤ የእግዚአብሔር ቃል የነጠረ ነው፤ በእርሱ ለሚታመኑት ሁሉ ጋሻ ነው።
32፤ ከእግዚአብሔር በቀር አምላክ ማን ነው? ከአምላካችንስ በቀር አምባ ማን ነው?
33፤ ኃይልን የሚያስታጥቀኝ፥ መንገዴንም የሚያቃና፥
34፤ እግሮቼን እንደ ብሆር እግሮች የሚያበረታ፥ በኮረብቶችም የሚያቆመኝ እግዚአብሔር ነው።
35፤ እጆቼን ሰልፍ ያስተምራል፤ በክንዴም የናስ ቀስት እገትራለሁ።
36፤ የማዳንህንም ጋሻ ሰጠኸኝ፤ ተግሣጽህም አሳደገኝ።
37፤ አረማመዴን በበታቼ አሰፋህ፥ እግሮቼም አልተንሸራተቱም።
38፤ ጠላቶቼን አሳድዳቸዋለሁ፥ አጠፋቸውማለሁ፤ እስካጠፋቸውም ድረስ አልመለስም።
39፤ አስጨንቃቸዋለሁ መቆምም አይችሉም፥ ከእግሬም በታች ይወድቃሉ።
40፤ ለሰልፍም ኃይልን ታስታጥቀኛለህ፤ በላዬ የቆሙትን በበታቼ ታስገዛቸዋለህ።
41፤ የጠላቶቼን ጀርባ ሰጠኸኝ፥ የሚጠሉኝንም አጠፋሃቸው።
42፤ ጮኹ፥ የሚረዳቸውም አልነበረም፤ ወደ እግዚአብሔር ጮኹ፥ አልሰማቸውምም።
43፤ እንደ ምድር ትቢያ ፈጨኋቸው፤ እንደ አደባባይም ጭቃ ረገጥኋቸው፥ ደቀደቅኋቸውም።
44፤ ከሕዝብ ክርክር ታድነኛለህ፤ የአሕዛብም ራስ አድርገህ ትሾመኛለህ፤ የማላውቀው ሕዝብም ይገዛልኛል።
45፤ የባዕድ ልጆች ደለሉኝ፤ በጆሮ ሰምተው ተገዙልኝ።
46፤ የባዕድ ልጆች እየጠፉ ይሄዳሉ፤ ከተዘጉ ስፍሮች እየተንቀጠቀጡ ይወጣሉ።
47፤ እግዚአብሔር ሕያው ነው፥ ጠባቂዬም ቡሩክ ነው፤ የመድኃኒቴ ጠባቂ አምላኬ ከፍ ከፍ ይበል፤
48፤ በቀሌን የሚመልስልኝ አምላክ፥ አሕዛብን በበታቼ የሚያስገዛ፥
49፤ ከጠላቶቼ የሚያወጣኝ እርሱ ነው፤ በእኔም ላይ ከቆሙ ከፍ ከፍ ታደርገኛለህ፤ ከግፈኛ ሰው ታድነኛለህ።
50፤ አቤቱ፥ ስለዚህ በአሕዛብ ዘንድ አመሰግንሃለሁ፥ ለስምህም እዘምራለሁ።
51፤ የንጉሡን መድኃኒት ታላቅ ያደርጋል፤ ቸርነቱንም ለቀባው፥ ለዳዊትና ለዘሩ፥ ለዘላለም ይሰጣል።