መጽሐፈ ሳሙኤል ካል - 2 Samuel

ምዕራፍ: 1 2 3 4 5 6 7 8 9 10 11 12 13 14 15 16 17 18 19 20 21 22 23 24


ምዕራፍ 19

1፤ ኢዮአብም ንጉሡ ስለ አቤሴሎም እንዳለቀሰና ዋይ ዋይ እንዳለ ሰማ።
2፤ በዚያም ቀን። ንጉሡ ስለ ልጁ አዘነ ሲባል ሕዝቡ ሰምቶአልና የዚያ ቀን ድል በሕዝቡ ሁሉ ዘንድ ወደ ኀዘን ተለወጠ።
3፤ ሕዝቡም ከሰልፍ የሸሸ ሕዝብ አፍሮ ወደ ኋላው እንዲል በዚያ ቀን ወደ ከተማ ተሰርቆ ገባ።
4፤ ንጉሡም ፊቱን ሸፈነ፥ ንጉሡም በታላቅ ድምፅ። ልጄ አቤሴሎም ሆይ፥ ልጄ አቤሴሎም፥ ልጄ ሆይ እያለ ይጮኽ ነበር።
5፤ ኢዮአብም ወደ ንጉሡ ወደ ቤት ገብቶ እንዲህ አለ። ዛሬ ነፍስህንና የወንዶችና የሴቶች ልጆችህን ነፍስ የሚስቶችህንና የቁባቶችህን ነፍስ ያዳኑትን የባሪያዎችህን ሁሉ ፊት ዛሬ አሳፍረሃል፤
6፤ አንተ የሚጠሉህን ትወድዳለህ፥ የሚወድዱህንም ትጠላለህ። መሳፍንትህንና ባሪያዎችህን እንዳታስብ ዛሬ ገልጠሃል፤ ዛሬ ሁላችን ሞተን ቢሆን ኖር አቤሴሎምም ድኖ ቢሆን ኖሮ ደስ ያሰኘህ እንደ ነበረ ዛሬ አያለሁ።
7፤ አሁን እንግዲህ ተነሥተህ ውጣ፥ ለባሪያዎችህም የሚያጽናናቸውን ነገር ተናገራቸው፤ ያልወጣህ እንደ ሆነ ግን አንድ ሰው ከአንተ ጋር በዚህች ሌሊት እንዳይቀር በእግዚአብሔር እምላለሁ፤ ይህም ከብላቴናነትህ ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ ካገኘህ ክፉ ነገር ሁሉ ይልቅ ታላቅ መከራ ይሆንብሃል።
8፤ ንጉሡም ተነሥቶ በበሩ ተቀመጠ፤ ሕዝቡም ሁሉ ንጉሡ በበሩ እንደ ተቀመጠ ሰማ፤ ሕዝቡም ሁሉ ወደ ንጉሡ ፊት መጣ። እስራኤልም እያንዳንዱ ወደ ድንኳኑ ሸሽቶ ነበር።
9፤ ሕዝቡም ሁሉ በእስራኤል ነገድ ሁሉ ውስጥ። ንጉሡ ከጠላቶቻችን እጅ ታድጎናል፥ ከፍልስጥኤማውያንም እጅ አድኖናል፤ አሁንም ስለ አቤሴሎም ከአገር ሸሽቶአል።
10፤ በላያችን እንዲሆን የቀባነው አቤሴሎም በሰልፍ ሞቶአል፤ አሁንም እንግዲህ ንጉሡን ለመመለስ ስለምን ዝም ትላላችሁ? እያለ እርስ በርሱ ይከራከር ነበር።
11፤ ንጉሡም ዳዊት ለካህናቱ ለሳዶቅና ለአብያታር ልኮ እንዲህ አላቸው። ለይሁዳ ሽማግሌዎች እንዲህ ብላችሁ ተናገሩአቸው። የእስራኤል ሁሉ ነገር ወደ ንጉሡ ደርሶአልና ንጉሡን ወደ ቤቱ ከመመለስ ስለ ምን ዘገያችሁ?
12፤ እናንተ ወንድሞቼ፥ የአጥንቴ ፍላጭና የሥጋዬ ቍራጭ ናችሁ፤ እናንተ ንጉሡን ከመመለስ ስለ ምን ዘገያችሁ?
13፤ ለአሜሳይም። አንተ የአጥንቴ ፍላጭና የሥጋዬ ቍራጭ አይደለህምን? በዘመንህም ሁሉ በኢዮአብ ፋንታ በፊቴ የሠራዊት አለቃ ሳትሆን ብትቀር እግዚአብሔር ይህን ያድርግብኝ ይህንም ይጨምርብኝ በሉት።
14፤ የይሁዳንም ሰዎች ሁሉ ልብ እንደ አንድ ሰው ልብ አድርጎ አዘነበለ፤ ወደ ንጉሡም ልከው። አንተ ከባሪያዎችህ ሁሉ ጋር ተመለስ አሉት።
15፤ ንጉሡም ተመልሶ እስከ ዮርዳኖስ ድረስ መጣ። የይሁዳ ሰዎች ንጉሡን ሊቀበሉ ንጉሡንም ዮርዳኖስን ሊያሻግሩ ወደ ጌልገላ መጡ።
16፤ ከብራቂምም አገር የነበረው ብንያማዊው የጌራ ልጅ ሳሚ ከይሁዳ ሰዎች ጋር ዳዊትን ሊቀበል ፈጥኖ ወረደ።
17፤ ከእርሱም ጋር ብንያማውያን የሆኑ ሺህ ሰዎች ነበሩ፥ የሳኦልም ቤት ባሪያ ሲባ ከእርሱም ጋር አሥራ አምስቱ ልጆችና ሀያው ባሪያዎች ነበሩ፤ በንጉሡም ፊት ፈጥነው ዮርዳኖስን ተሻገሩ።
18፤ ታንኳውም የንጉሥን ቤተ ሰብ ያሻግር ዘንድ ንጉሡም ደስ ያሰኘውን ያደርግ ዘንድ ይሸጋገር ነበር። ንጉሡም ዮርዳኖስን ከተሻገረ በኋላ የጌራ ልጅ ሳሚ በፊቱ ተደፋ።
19፤ ንጉሡንም። ጌታዬ ሆይ፥ ኃጢአቴን አትቍጠርብኝ፤ ጌታዬ ንጉሡ፥ ከኢየሩሳሌም በወጣህ ቀን ባሪያህ የበደልሁህን አታስብብኝ፥ ንጉሡም በልቡ አያኑረው።
20፤ ባሪያህ በደለኛ እንደ ሆንሁ አውቄአለሁና እነሆ፥ ከዮሴፍ ቤት ሁሉ አስቀድሜ ዛሬ መጣሁ፥ ጌታዬንም ንጉሡን ልቀበል ወረድሁ አለው።
21፤ የጽሩያ ልጅ አቢሳ ግን። ሳሚ እግዚአብሔር የቀባውን ሰድቦአልና ሞት የተገባው አይደለምን? አለ።
22፤ ዳዊትም። እናንተ የጽሩያ ልጆች፥ እኔ ከእናንተ ጋር ምን አለኝ? ዛሬ ስለ ምን ጠላቶች ትሆኑብኛላችሁ? ዛሬስ በእስራኤል ዘንድ ሰው ሊሞት ይገባልን? ዛሬስ በእስራኤል ላይ እንደ ነገሥሁ አላወቅሁምን? አለ።
23፤ ንጉሡም ሳሚን። አትሞትም አለው። ንጉሡም ማለለት።
24፤ የሳኦልም ልጅ ሜምፊቦስቴ ንጉሡን ሊቀበል ወረደ፤ ንጉሡም ከሄደ ጀምሮ በደኅና እስከ ተመለሰበት ቀን ድረስ እግሩን አልጠገነም፥ ጢሙንም አልቈረጠም፥ ልብሱንም አላጠበም ነበር።
25፤ ንጉሡም ሊቀበለው ከኢየሩሳሌም በመጣ ጊዜ ንጉሡ። ሜምፊቦስቴ ሆይ፥ ከእኔ ጋር ስለ ምን አልወጣህም? አለው።
26፤ እርሱም መልሶ አለ። ጌታዬን፥ ንጉሥ ሆይ፥ ባሪያዬ አታለለኝ፤ እኔ ባሪያህ አንካሳ ነኝና። ከንጉሥ ጋር እሄድ ዘንድ የምቀመጥበትን አህያ ልጫን አልሁት።
27፤ እርሱም እኔን ባሪያህን ለጌታዬ ለንጉሡ አማ፤ አንተ ጌታዬ ንጉሥ ግን እንደ እግዚአብሔር መልአክ ነህ፤ ደስም ያሰኘህን አድርግ።
28፤ የአባቴ ቤት ሁሉ በጌታዬ በንጉሡ ዘንድ ሞት የሚገባቸው ነበሩ፤ አንተ ግን እኔን ባሪያህን በገበታህ በሚበሉ መካከል አስቀመጥኸኝ፤ ለንጉሥ ደግሞ ለመናገር ምን መብት አለኝ?
29፤ ንጉሡም። ነገርህን ለምን ታበዛለህ? አንተና ሲባ እርሻውን ትካፈሉ ዘንድ ብያለሁ አለው።
30፤ ሜምፊቦስቴም ንጉሡን። ጌታዬ ንጉሡ በደኅና ወደ ቤቱ ከተመለሰ እርሱ ሁሉን ይውሰደው አለው።
31፤ ገለዓዳዊውም ቤርዜሊ ከሮግሊም ወረደ፤ ሊሸኘውም ከንጉሡ ጋር ዮርዳኖስን ተሻገረ።
32፤ ቤርዜሊም እጅግ ያረጀ የሰማንያ ዓመት ሽማግሌ ነበረ፤ እጅግም ትልቅ ሰው ነበረና ንጉሡ በመሃናይም ሳለ ይቀልበው ነበር።
33፤ ንጉሡም ቤርዜሊን። በኢየሩሳሌም እቀልብህ ዘንድ ከእኔ ጋር እለፍ አለው።
34፤ ቤርዜሊም ንጉሡን አለው። ከንጉሡ ጋር ወደ ኢየሩሳሌም እወጣ ዘንድ ከሕይወቴ ዘመን ምን ያህል ቀረኝ?
35፤ ዛሬ የሰማንያ ዓመት ሽማግሌ ነኝ፤ መልካሙንና ክፉውን መለየት እችላለሁን? እኔ ባሪያህ የምበላውንና የምጠጣውን ጣዕሙን መለየት እችላለሁን? የወንዱንና የሴቲቱን ዘፈን ድምፅ መስማት እችላለሁን? እኔ ባሪያህ በጌታዬ በንጉሡ ላይ ለምን እከብድብሃለሁ?
36፤ እኔ ባሪያህ ዮርዳኖስን ተሻግሬ ከንጉሡ ጋር ጥቂት ልሄድ ነበር፤ ንጉሡ እንዲህ ያለ ወረታ ለምን ይመልስልኛል?
37፤ እኔ ባሪያህ ተመልሼ በከተማዬ በአባቴና በእናቴ መቃብር አጠገብ፥ እባክህ፥ ልሙት። ነገር ግን ባሪያህን ከመዓምን እይ፤ እርሱ ከጌታዬ ከንጉሡ ጋር ይለፍ፥ ደስ የሚያሰኝህንም ለእርሱ አድርግ።
38፤ ንጉሡም። ከመዓም ከእኔ ጋር ይለፍ፥ ደስ የሚያሰኝህንም አደርግለታለሁ፤ አንተም ከእኔ የምትሻውን ሁሉ አደርግልሃለሁ አለው።
39፤ ሕዝቡም ሁሉ ዮርዳኖስን ተሻገረ፥ ንጉሡም ተሻገረ፤ ንጉሡም ቤርዜሊን ሳመው፥ መረቀውም፤ ወደ ስፍራውም ተመለሰ።
40፤ ንጉሡም ወደ ጌልገላ ተሻገረ፥ ከመዓምም ከእርሱ ጋር ሄደ፤ የይሁዳም ሕዝብ ሁሉ ደግሞም የእስራኤል ሕዝብ እኩሌታ ንጉሡን አሻገረው።
41፤ እነሆም፥ የእስራኤል ሰዎች ሁሉ ወደ ንጉሥ መጡ፥ ንጉሡንም። ወንድሞቻችን የይሁዳ ሰዎች ለምን ሰረቁህ? ንጉሡንም ቤተ ሰቡንም ከእርሱም ጋር የዳዊትን ሰዎች ሁሉ ዮርዳኖስን አሻገሩ? አሉት።
42፤ የይሁዳም ሰዎች ሁሉ ለእስራኤል ሰዎች መልሰው። ንጉሡ ለእኛ ቅርባችን ነው፤ ስለ ምን በዚህ ነገር ትቈጣላችሁ? በውኑ ከንጉሡ አንዳች በልተናልን? ወይስ እርሱ በረከት ሰጥቶናልን? አሉ።
43፤ የእስራኤልም ሰዎች ለይሁዳ ሰዎች መልሰው። በንጉሡ ዘንድ ለእኛ አሥር ክፍል አለን፥ በዳዊትም ዘንድ ደግሞ ከእናንተ ይልቅ መብት አለን፤ ስለ ምን ናቃችሁን? ስለ ምንስ ንጉሣችንን ለመመለስ ቀድሞ ምክር አልጠየቃችሁንም? አሉ። የይሁዳም ሰዎች ቃል ከእስራኤል ሰዎች ቃል ይልቅ ጠነከረ።