ምዕራፍ 39
1፤ የበረሃ ፍየል የምትወልድበትን ጊዜ ታውቃለህን? ዋላይቱስ የምታምጥበትን ጊዜ ትመለከታለህን?
2፤ እርስዋ የምትፈጽመውንስ ወራት ትቈጥራለህን? የምትወልድበትንስ ጊዜ ታውቃለህን?
3፤ ይንበረከካሉ፥ ልጆቻቸውንም ይወልዳሉ፥ ከምጣቸውም ያርፋሉ።
4፤ ልጆቻቸው ይጠነክራሉ፥ በሜዳም ያድጋሉ፤ ይወጣሉ፥ ወደ እነርሱም አይመለሱም።
5፤ የሜዳውስ አህያ አርነት ማን አወጣው? የበረሃውንስ አህያ ከእስራቱ ማን ፈታው?
6፤ በረሃውን ለእርሱ ቤት አድርጌ ሰጠሁት፤ መኖሪያውም በጨው ምድር ነው።
7፤ በከተማ ውካታ ይዘብታል፤ የነጂውን ጩኸት አይሰማም።
8፤ ተራራውን እንደ መሰምርያው ይመለከተዋል፥ ለምለሙንም ሁሉ ይፈልጋል።
9፤ ጐሽ ያገለግልህ ዘንድ ይታዘዛልን? ወይስ በግርግምህ አጠገብ ያድራልን?
10፤ ጐሽ ይተልምልህ ዘንድ ትጠምደዋለህን? ወይስ ከአንተ በኋላ በእርሻ ላይ ይጐለጕላልን?
11፤ ጕልበቱስ ብርቱ ስለ ሆነ ትታመነዋለህን? ተግባርህንስ ለእርሱ ትተዋለህን?
12፤ ዘርህንስ ይመልስልህ ዘንድ፥ በአውድማህስ ያከማችልህ ዘንድ ትታመነዋለህን?
13፤ የሰጐን ክንፍ በደስታ ይንቀሳቀሳል፤ ነገር ግን ክንፉና ላባው ጭምተኛ ነውን?
14፤ እንቍላልዋን በመሬት ላይ ትተዋለች፥ በአፈርም ውስጥ ታሞቀዋለች፤
15፤ እግር ይሰብረው ዘንድ፥ የምድረ በዳም አውሬ ይረግጠው ዘንድ ትረሳለች።
16፤ የእርስዋ እንዳልሆኑ በልጆችዋ ትጨክናለች። በከንቱም ብትሠራ አትፈራም፤
17፤ እግዚአብሔር ጥበብን ከእርስዋ ከልክሎአልና፥ ማስተዋልንም አልሰጣትምና።
18፤ ወደ ላይ ከፍ ከፍ ስትል በፈረስና በፈረሰኛው ትሳለቃለች።
19፤ ለፈረስ ጕልበቱን ሰጥተኸዋልን? አንገቱንስ ጋማ አልብሰኸዋልን?
20፤ እንደ አንበጣስ አፈናጠርኸውን? የማንኰራፋቱ ክብር የሚያስፈራ ነው።
21፤ በኮቴው በሸለቆው ውስጥ ይጐደፍራል፥ በጉልበቱም ደስ ይለዋል፤ ሰይፍም የታጠቁትን ለመገናኘት ይወጣል።
22፤ በፍርሃት ላይ ይስቃል፥ እርሱም አይደነግጥም፤ ከሰይፍም ፊት አይመለስም።
23፤ በእርሱ ላይ የፍላጻ ኮረጆና ብልጭልጭ የሚል ጦር ሰላጢንም ያንኳኳሉ።
24፤ በጭካኔና በቍጣ መሬትን ይውጣል፤ የመለከትም ድምፅ ቢሰማ አይቆምም።
25፤ የመለከትም ድምፅ ሲሰማ። እሰይ! ይላል፤ ከሩቅ ሆኖ ሰልፍንና የአለቆቹን ጩኸት፥ የሠራዊቱንም ውካታ ያሸታል።
26፤ በውኑ ከጥበብህ የተነሣ ጭልፊት ያንዣብባልን? ወይስ ክንፎቹን ወደ ደቡብ ይዘረጋልን?
27፤ በአፍህ ትእዛዝ ንስር ከፍ ከፍ ይላልን? ቤቱንስ በአርያም ላይ ያደርጋልን?
28፤ በገደል ላይ ይኖራል፤ በገደሉ ገመገምና በጥጉ ያድራል።
29፤ በዚያም ሆኖ የሚነጥቀውን ይጐበኛል፤ ዓይኑም በሩቅ ትመለከታለች።
30፤ ጫጩቶቹም ደም ይጠጣሉ፤ በድን ባለባትም ስፍራ እርሱ በዚያ አለ።