ምዕራፍ 29
1፤ ኢዮብም ምሳሌውን ይመስል ዘንድ ደገመ፥ እንዲህም አለ።
2፤ እግዚአብሔር ይጠብቀኝ እንደ ነበረው ጊዜ፥ እንደ ፊተኛው ወራት ምነው በሆንሁ!
3፤ በራሴ ላይ መብራቱ በበራ ጊዜ፥ እኔም ጨለማውን አልፌ በብርሃኑ በሄድሁ ጊዜ፥
4፤ በሙሉ ሰውነቴ እንደ ነበርሁ ጊዜ፥ እግዚአብሔር ድንኳኔን በጋረደ ጊዜ፥
5፤ ሁሉን የሚችል አምላክ ከእኔ ጋር ገና ሳለ፥ ልጆቼም በዙሪያዬ ሳሉ፥
6፤ መንገዴ በቅቤ ይታጠብ በነበረ ጊዜ፥ ድንጋዩ የዘይት ፈሳሽ ያፈስስልኝ በነበረ ጊዜ።
7፤ ወደ ከተማይቱ በር በወጣሁ ጊዜ፥ በአደባባዩም ወንበሬን ባኖርሁ ጊዜ፥
8፤ ጐበዛዝት እኔን አይተው ተሸሸጉ፥ ሽማግሌዎችም ተነሥተው ቆሙ።
9፤ አለቆቹ ከመናገር ዝም አሉ፥ እጃቸውንም በአፋቸው ላይ ጫኑ።
10፤ የታላላቆቹም ድምፅ አረመመ፤ ምላሳቸውም በትናጋቸው ተጣጋ።
11፤ የሰማችኝ ጆሮ አሞገሰችኝ፥ ያየችኝም ዓይን መሰከረችልኝ፤
12፤ የሚጮኸውን ችግረኛ፥ ድሀ አደጉንና ረጂ የሌለውን አድኜ ነበርሁና።
13፤ ለጥፋት የቀረበው በረከት በላዬ መጣ፤ የባልቴቲቱንም ልብ እልል አሰኘሁ።
14፤ ጽድቅን ለበስሁ እርስዋም ለበሰችኝ፤ ፍርዴም እንደ መጐናጸፊያና እንደ ኵፋር ነበረ።
15፤ ለዕውር ዓይን፥ ለአንካሳ እግር ነበርሁ።
16፤ ለድሀው አባት ነበርሁ፤ የማላውቀውንም ሰው ሙግት መረመርሁ።
17፤ የኃጢአተኛውን መንጋጋ ሰበርሁ፥ የነጠቀውንም ከጥርሱ ውስጥ አስጣልሁ።
18፤ እኔም አልሁ። በልጆቼ መካከል እሞታለሁ፥ ዕድሜዬንም እንደ አሸዋ አበዛለሁ፤
19፤ ሥሬ በውኃ ላይ ተዘርግቶአል፥ ጠልም በቅርንጫፌ ላይ ያድራል፤
20፤ ክብሬ በእኔ ዘንድ ታድሶአል፥ ቀስቴም በእጄ ውስጥ ለምልሞአል።
21፤ ሰዎች እኔን ሰምተው በትዕግሥት ተጠባበቁ፥ ምክሬንም ለማዳመጥ ዝም አሉ።
22፤ ከቃሌ በኋላ አንዳች አልመለሱም፤ ንግግሬም በእርሱ ላይ ተንጠባጠበ።
23፤ ዝናብን እንደሚጠብቁ በትዕግሥት ጠበቁኝ፤ የጥቢን ዝናብ እንደሚሹ አፋቸውን ከፈቱ።
24፤ እነርሱ ባልታመኑ ጊዜ ሳቅሁላቸው፤ የፊቴንም ብርሃን አላወረዱም።
25፤ መንገዳቸውን መረጥሁ፤ እንደ አለቃ ሆኜ ተቀመጥሁ፤ ንጉሥ በሠራዊቱ መካከል እንደሚኖር፥ ኅዘነተኞችን እንደሚያጽናና ኖርሁ።