ምዕራፍ 36
1፤ ኤሊሁም ደግሞ መለሰ እንዲህም አለ።
2፤ ገና ስለ እግዚአብሔር የሚነገር አለኝና ጥቂት ቆየኝ፥ እኔም አስታውቅሃለሁ።
3፤ እውቀቴን ከሩቅ አመጣለሁ፥ ፈጣሪዬንም። ጻድቅ ነው እላለሁ።
4፤ ቃሌ በእውነት ያለ ሐሰት ነው፤ በእውቀትም ፍጹም የሆነ ከአንተ ጋር አለ።
5፤ እነሆ፥ እግዚአብሔር ኃያል ነው፥ ማንንም አይንቅም፤ እርሱም በማስተዋል ብርታት ኃያል ነው።
6፤ እርሱ የበደለኞችን ሕይወት አያድንም፤ ለችግረኞች ግን ፍርዱን ይሰጣል።
7፤ ዓይኑን ከጻድቃን ላይ አያርቅም፤ ለዘላለምም ከነገሥታት ጋር በዙፋን ላይ ያስቀምጣቸዋል፥ እነርሱም ከፍ ከፍ ይላሉ።
8፤ በሰንሰለት ቢታሰሩ፥ ወይም በችግር ገመድ ቢጠመዱ፥
9፤ ሥራቸውንና መተላለፋቸውን በትዕቢትም እንዳደረጉ ይናገራቸዋል።
10፤ ጆሮአቸውን ለተግሣጽ ይከፍተዋል፥ ከኃጢአትም ይመለሱ ዘንድ ያዝዛቸዋል።
11፤ ቢሰሙ ቢያገለግሉትም፥ ዕድሜአቸውን በልማት፥ ዘመናቸውንም በተድላ ይፈጽማሉ።
12፤ ባይሰሙ ግን በሰይፍ ይጠፋሉ፥ ያለ እውቀትም ይሞታሉ።
13፤ ዝንጉዎች ግን ቍጣን ያዘጋጃሉ፤ እርሱም ባሰራቸው ጊዜ አይጮኹም።
14፤ በሕፃንነታቸው ሳሉ ይሞታሉ፥ ሕይወታቸውም በሰዶማውያን መካከል ይጠፋል።
15፤ የተቸገረውን በችግሩ ያድነዋል፤ በመከራም ጆሮአቸውን ይገልጣል።
16፤ እንዲሁም አንተን ከመከራ ችግር ወደሌለበት ወደ ሰፊ ስፍራ በወሰደህ ነበር፥ በማዕድህ ላይ የተዘጋጀውም ስብ በሞላበት ነበር።
17፤ አንተ ግን በበደለኞች ፍርድ የተሞላህ ነህ፤ ስለዚህ ፍርድና ብይን ይይዝሃል።
18፤ ቍጣ ለስድብ አያታልልህ፤ የማማለጃም ብዛት ፈቀቅ አያድርግህ።
19፤ ባለጠግነትህ የኃይልህም ብርታት ሁሉ ያለ ችግር እንድትሆን ሊረዳህ ይችላልን?
20፤ ወገኖች ከስፍራቸው የሚወጡበትን ሌሊት አትመኝ።
21፤ ከመከራ ይልቅ ይህን መርጠሃልና ኃጢአትን እንዳትመለከት ተጠንቀቅ።
22፤ እነሆ፥ እግዚአብሔር በኃይሉ ከፍ ያለውን ነገር ያደርጋል፤ እንደ እርሱስ ያለ አስተማሪ ማን ነው?
23፤ መንገዱን ማን አዘዘለት? ወይስ። ኃጢአትን ሠርተሃል የሚለው ማን ነው?
24፤ ሰዎች የዘመሩትን ሥራውን ታከብር ዘንድ አስብ።
25፤ ሰዎች ሁሉ ተመልክተውታል፤ ሰውም ከሩቅ ያየዋል።
26፤ እነሆ፥ እግዚአብሔር ታላቅ ነው፥ እኛም አናውቀውም። የዘመኑም ቍጥር አይመረመርም።
27፤ የውኃውን ነጠብጣብ ወደ ላይ ይስባል፥ ዝናብም ከጉም ይንጠባጠባል፤
28፤ ደመናት ያዘንባሉ፥ በሰዎችም ላይ በብዙ ያንጠባጥባሉ።
29፤ የደመናውንም መዘርጋት፥ የማደሪያውንም ነጐድጓድ የሚያስተውል ማን ነው?
30፤ እነሆ፥ በዙሪያው ብርሃኑን ይዘረጋል፤ የባሕሩንም ጥልቀት ይከድናል።
31፤ በእነዚህ በአሕዛብ ላይ ይፈርዳል፤ ብዙም ምግብ ይሰጣል።
32፤ እጆቹን በብርሃን ይሰውራል፥ በጠላቱም ላይ ይወጣ ዘንድ ያዝዘዋል፤
33፤ የነጐድጓድ ድምፅ ስለ እርሱ ይናገራል፤ እንስሶችም ደግሞ ስለሚመጣው ውሽንፍር ይጮኻሉ።