ምዕራፍ 27
1፤ ርዝመቱ አምስት ክንድ፥ ወርዱም አምስት ክንድ መሠዊያ ከግራር እንጨት አድርግ፤ አራት ማዕዘንም ይሁን፤ ከፍታውም ሦስት ክንድ ይሁን።
2፤ በአራቱም ማዕዘን ቀንዶችን ታደርጋለህ፥ ቀንዶቹም ከእርሱ ጋር በአንድ የተሠሩ ይሁኑ፤ በናስም ለብጠው።
3፤ አመድ የሚሆንባቸውን ምንቸቶች፥ መጫሪያዎቹንም፥ ድስቶቹንም፥ ሜንጦቹንም፥ ማንደጃዎቹንም አድርግ፤ ዕቃውንም ሁሉ ከናስ አድርግ።
4፤ እንደ መረብ ሆኖ የተሠራ የናስ መከታ አድርግለት፤ ለመከታውም አራት የናስ ቀለበት በአራት ማዕዘኑ አድርግለት።
5፤ መከታውም እስከ መሠዊያው እኵሌታ ይደርስ ዘንድ በመሰዊያው በሚዞረው በእርከኑ ታች አድርገው።
6፤ ለመሠዊያውም ከግራር እንጨት መሎጊያዎችን ሠርተህ በናስ ለብጣቸው።
7፤ መሎጊያዎቹም በቀለበቶች ውስጥ ይግቡ፤ መሠዊያውንም ስትሸከሙ መሎጊያዎቹ በሁለቱ ወገኖች ይሁኑ።
8፤ ከሳንቆች ሠርተህ ባዶ አድርገው፤ በተራራው እንዳሳየሁህ ምሳሌ እንዲሁ ያድርጉት።
9፤ የማደሪያውንም አደባባይ ሥራ፤ በደቡብ ወገን የጥሩ በፍታ መጋረጆች ይሁኑለት፥ የአንዱም ወገን ርዝመት መቶ ክንድ ይሁን፤
10፤ ከናስ የተሠሩ ሀያ ምሰሶችና ሀያ እግሮች ይሁኑለት፤ የምሰሶቹም ኩላቦችና ዘንጎች የብር ይሁኑ።
11፤ እንዲሁም በሰሜን ወገን መቶ ክንድ ርዝመት ያላቸው መጋረጆች፥ ከናስ የተሠሩ ሀያ ምሶሶች ሀያም እግሮች ይሁኑ፤ ለምሰሶችም የብር ኩላቦችና ዘንጎች ይሁኑ።
12፤ በምዕራብም ወገን ለአደባባዩ ስፋት አምሳ ክንድ ርዝመት ያላቸው መጋረጆች፥ አሥርም ምሰሶች፥ አሥርም እግሮች ይሁኑለት።
13፤ በምሥራቅም ወገን የአደባባዩ ስፋት አምሳ ክንድ ይሁን።
14፤ በአንድ ወገን የመጋረጆቹ ርዝመት አሥራ አምስት ክንድ ይሁን፤ ምሰሶቹም ሦስት፥ እግሮቹም ሦስት ይሁኑ።
15፤ በሌላውም ወገን የመጋረጆች ርዝመት አሥራ አምስት ክንድ ይሆናል፤ ምሰሶቹም ሦስት፥ እግሮቹም ሦስት ይሁኑ።
16፤ ለአደባባዩም ደጅ ከሰማያዊ ከሐምራዊም ከቀይም ግምጃ ከጥሩ በፍታም በጥልፍ አሠራር የተሠራ ሀያ ክንድ መጋረጃ ይሆናል፤ ምሰሶቹም አራት፥ እግሮቹም አራት ይሁኑ።
17፤ በአደባባዩም ዙሪያ ላሉት ምሰሶች ሁሉ የብር ዘንጎች፥ የብርም ኩላቦች፥ የናስም እግሮች ይሁኑላቸው።
18፤ የአደባባዩ ርዝመት መቶ ክንድ ስፋቱም አምሳ ክንድ ይሁን፥ የመጋረጃውም ከፍታ አምስት ክንድ ይሁን፤ መጋረጃውም ከጥሩ በፍታ፥ እግሮቹም ከናስ የተሠሩ ይሁኑ።
19፤ ለማገልገል ሁሉ የማደሪያው ዕቃ ሁሉ፥ ካስማዎቹም ሁሉ የአደባባዩም ካስማዎች ሁሉ፥ የናስ ይሁኑ።
20፤ አንተም መብራቱን ሁልጊዜ ያበሩት ዘንድ ለመብራት ተወቅጦ የተጠለለ ጥሩ የወይራ ዘይት እንዲያመጡልህ የእስራኤልን ልጆች እዘዛቸው።
21፤ በመገናኛው ድንኳን ውስጥ በምስክሩ ታቦት ፊት ባለው መጋረጃ ውጭ አሮንና ልጆቹ ከማታ እስከ ማለዳ ድረስ በእግዚአብሔር ፊት እንዲበራ ያሰናዱት፤ በእስራኤል ልጆች ዘንድ ለልጅ ልጃቸው የዘላለም ሥርዓት ይሁን።