ምዕራፍ 18
1፤ የምድያምም ካህን የሙሴ አማት ዮቶር እግዚአብሔር ለሙሴና ለሕዝቡ ለእስራኤል ያደረገውን ሁሉ፥ እግዚአብሔርም እስራኤልን ከግብፅ እንዳወጣ ሰማ።
2፤ በዚያን ጊዜ የሙሴ አማት ዮቶር መልሶአት የነበረውን የሙሴን ሚስት ሲፓራን ሁለቱንም ልጆቿን ወሰደ።
3፤ ከእነርሱ የአንደኛው ስም ጌርሳም ነበረ፤ አባቱ። በሌላ አገር ስደተኛ ነበርሁ ብሎአልና፤
4፤ የሁለተኛውም ስም አልዓዛር ነበረ። የአባቴ አምላክ ረዳኝ፥ ከፈርዖንም ሰይፍ አዳነኝ ብሎአልና።
5፤ የሙሴ አማት ዮቶርም ከልጆቹና ከሚስቱ ጋር በእግዚአብሔር ተራራ አጠገብ በምድረ በዳ ወደ ሰፈረ ወደ ሙሴ መጣ።
6፤ ሙሴንም። እኔ አማትህ ዮቶር፥ ሚስትህም፥ ከእርስዋም ጋር ሁለቱ ልጆችዋ መጥተንልሃል አለው።
7፤ ሙሴም አማቱን ሊገናኝ ወጣ፥ ሰገደም፥ ሳመውም፤ እርስ በርሳቸውም ደኅንነታቸውን ተጠያየቁ፥ ወደ ድንኳኑም ገቡ።
8፤ ሙሴም እግዚአብሔር በፈርዖንና በግብፃውያን ላይ ስለ እስራኤል ያደረገውን ሁሉ፥ በመንገድም ያገኛቸውን ድካም ሁሉ፥ እግዚአብሔርም እንዳዳናቸው ለአማቱ ነገረው።
9፤ ዮቶርም እግዚአብሔር ለእስራኤል ስላደረገው ቸርነት ሁሉ፥ ከግብፃውያንም እጅ ስላዳናቸው ደስ አለው።
10፤ ዮቶርም። ከግብፃውያንና ከፈርዖን እጅ ያዳናችሁ፥ ከግብፃውያንም እጅ ሕዝቡን ያዳነ እግዚአብሔር ይባረክ።
11፤ ትዕቢት ባደረጉባቸው ነገር እግዚአብሔር ከአማልክት ሁሉ እንዲበልጥ አሁን አወቅሁ አለ።
12፤ የሙሴ አማት ዮቶርም የሚቃጠል መሥዋዕትንና ሌላ መሥዋዕትን ለእግዚአብሔር ወሰደ፤ በእግዚአብሔርም ፊት ከሙሴ አማት ጋር እንጀራ ሊበሉ አሮን የእስራኤልም ሽማግሌዎች ሁሉ መጡ።
13፤ እንዲህም ሆነ፤ በነጋው ሙሴ በሕዝቡ ሊፈርድ ተቀመጠ፤ ሕዝቡም በሙሴ ፊት ከጥዋት እስከ ማታ ድረስ ቆመው ነበር።
14፤ የሙሴም አማት በሕዝቡ ያደረገውን ሁሉ ባየ ጊዜ። ይህ በሕዝቡ የምታደርገው ምንድር ነው? ሕዝቡ ሁሉ ከጥዋት ጀምሮ እስከ ማታ ድረስ በዙሪያህ ቆመው ሳሉ አንተ ብቻህን ስለ ምን ተቀምጠሃል? አለው።
15፤ ሙሴም አማቱን። ሕዝቡ እግዚአብሔርን ለመጠየቅ ወደ እኔ ይመጣሉ፤
16፤ ነገርም ቢኖራቸው ወደ እኔ ይመጣሉ፥ በዚህና በዚያ ሰውም መካከል እፈርዳለሁ፥ የእግዚአብሔርንም ሥርዓትና ሕግ አስታውቃቸዋለሁ አለው።
17፤ የሙሴም አማት አለው። አንተ የምታደርገው ይህ ነገር መልካም አይደለም።
18፤ ይህ ነገር ይከብድብሃልና አንተ ከአንተም ጋር ያለው ሕዝብ ትደክማላችሁ፤ አንተ ብቻህን ልታደርገው አትችልም።
19፤ አሁንም እመክርሃለሁና ቃሌን ስማ፥ እግዚአብሔርም ከአንተ ጋር ይሆናል፤ አንተ በእግዚአብሔር ፊት ለሕዝቡ ሁን፥ ነገራቸውንም ወደ እግዚአብሔር አድርስ፤
20፤ ሥርዓቱንም ሕጉንም አስተምራቸው፥ የሚሄዱበትን መንገድ የሚያደርጉትንም ሥራ ሁሉ አሳያቸው።
21፤ አንተም ከሕዝቡ ሁሉ አዋቂዎችን፥ እግዚአብሔርን የሚፈሩትን፥ የታመኑ፥ የግፍንም ረብ የሚጠሉትን ሰዎች ምረጥ፤ ከእነርሱም የሺህ አለቆችን፥ የመቶ አለቆችን፥ የአምሳ አለቆችን፥ የአሥርም አለቆችን ሹምላቸው።
22፤ በሕዝቡ ላይ ሁልጊዜ ይፍረዱ፤ አውራውን ነገር ሁሉ ወደ አንተ ያምጡት፥ ታናሹንም ነገር ሁሉ እነርሱ ይፍረዱ፤ እነርሱም ከአንተ ጋር ሸክሙን ይሸከማሉ፥ ለአንተም ይቀልልልሃል።
23፤ ይህንም ብታደርግ፥ እግዚአብሔር እንዲሁ ቢያዝዝህ፥ መቆም ይቻልሃል፥ ደግሞም ይህ ሕዝብ ሁሉ በሰላም ወደ ስፍራው ይደርሳል።
24፤ ሙሴም የአማቱን ቃል ሰማ፥ ያለውንም ሁሉ አደረገ።
25፤ ሙሴም ከእስራኤል ሁሉ አዋቂዎችን መረጠ፥ በሕዝቡም ላይ የሺህ አለቆች፥ የመቶም አለቆች፥ የአምሳም አለቆች፥ የአሥርም አለቆች አድርጎ ሾማቸው።
26፤ በሕዝቡም ላይ ሁልጊዜ ፈረዱ፤ የከበደባቸውንም ነገር ወደ ሙሴ አመጡ፥ ታናሹን ነገር ሁሉ ግን እነርሱ ፈረዱ።
27፤ ሙሴም አማቱን ሰደደው፤ እርሱም ወደ አገሩ ተመለሰ።