ምዕራፍ 24
1፤ ሙሴንም። አንተ አሮንም ናዳብም አብዩድም ከእስራኤልም ሰባ ሽማግሌዎች ወደ እግዚአብሔር ውጡ፥ በሩቁም ስገዱ፤
2፤ ሙሴም ብቻውን ወደ እግዚአብሔር ይቅረብ፥ እነርሱ ግን አይቅረቡ፤ ሕዝቡም ከእርሱ ጋር አይውጡ አለው።
3፤ ሙሴም መጣ ለሕዝቡም የእግዚአብሔርን ቃሎች ሁሉ ሥርዓቱንም ሁሉ ነገረ፤ ሕዝቡም ሁሉ በአንድ ድምፅ። እግዚአብሔር የተናገራቸውን ቃሎች ሁሉ እናደርጋለን ብለው መለሱ።
4፤ ሙሴም የእግዚአብሔርን ቃሎች ጻፈ፤ ማለዳም ተነሣ፥ ከተራራውም በታች መሠዊያን፥ አሥራ ሁለትም ሐውልቶች ለአሥራ ሁለቱ የእስራኤል ነገድ ሠራ።
5፤ የሚቃጠል መሥዋዕት እንዲያቀርቡ፥ ለእግዚአብሔርም ስለ ደኅንነት መሥዋዕት በሬዎችን እንዲሠዉ የእስራኤልን ልጆች ጐበዛዝት ሰደደ።
6፤ ሙሴም የደሙን እኵሌታ ወስዶ በቆሬ ውስጥ አደረገው፤ የደሙንም እኵሌታ በመሠዊያው ረጨው።
7፤ የቃል ኪዳኑንም መጽሐፍ ወስዶ ለሕዝቡ አነበበላቸው፤ እነርሱም። እግዚአብሔር ያለውን ሁሉ እናደርጋለን እንታዘዛለንም አሉ።
8፤ ሙሴም ደሙን ውስዶ በሕዝቡ ላይ ረጨው። በዚህ ቃል ሁሉ እግዚአብሔር ከእናንተ ጋር ያደረገው የቃል ኪዳኑ ደም እነሆ አለ።
9፤ ሙሴም አሮንም ናዳብም አብዩድም ከእስራኤልም ሰባ ሽማግሌዎች ወጡ፤
10፤ የእስራኤልንም አምላክ አዩ፤ ከእግሩም በታች እንደ ሰማይ መልክ የሚያበራ እንደ ብሩህ ሰንፔር ድንጋይ የሚመስል ወለል ነበረ።
11፤ እጁንም በእስራኤል አዛውንቶች ላይ አልዘረጋም፤ እነርሱም እግዚአብሔርን አዩ፥ በሉም ጠጡም።
12፤ እግዚአብሔርም ሙሴን። ወደ እኔ ወደ ተራራው ውጣ፥ በዚያም ሁን፤ እነርሱን ታስተምር ዘንድ እኔ የጻፍሁትን ሕግና ትእዛዝ የድንጋይም ጽላት እሰጥሃለሁ አለው።
13፤ ሙሴና ሎሌው ኢያሱ ተነሡ፤ ሙሴም ወደ እግዚአብሔር ተራራ ወጣ።
14፤ ሽማግሌዎችንም። ወደ እናንተ እስክንመለስ ድረስ በዚህ ቆዩን፤ አሮንና ሖርም እነሆ ከእናንተ ጋር ናቸው፥ ነገረተኛም ቢኖር ወደ እነርሱ ይምጣ አላቸው።
15፤ ሙሴም ወደ ተራራ ወጣ፥ ደመናውም ተራራውን ሸፈነው።
16፤ የእግዚአብሔርም ክብር በሲና ተራራ ላይ ተቀመጠ፥ ደመናውም ስድስት ቀን ሸፈነው፤ በሰባተኛውም ቀን ከደመናው ውስጥ ሙሴን ጠራው።
17፤ በተራራው ራስ ላይ በእስራኤል ልጆች ፊት የእግዚአብሔር ክብር መታየት እንደሚያቃጥል እሳት ነበረ።
18፤ ሙሴም ወደ ደመናው ውስጥ ገባ ወደ ተራራውም ወጣ፤ ሙሴም በተራራው ላይ አርባ ቀን አርባ ሌሊትም ቆየ።