ምዕራፍ 5
1፤ የአዳም የትውልዱ መጽሐፍ ይህ ነው። እግዚአብሔር አዳምን በፈጠረ ቀን በእግዚአብሔር ምሳሌ አደረገው፤
2፤ ወንድና ሴት አድርጎ ፈጠራቸው፥ ባረካቸውም። ስማቸውንም በፈጠረበት ቀን አዳም ብሎ ጠራቸው።
3፤ አዳምም ሁለት መቶ ሠላሳ ዓመት ኖረ፥ ልጅንም በምሳሌው እንደ መልኩ ወለደ፤ ስሙንም ሴት ብሎ ጠራው።
4፤ አዳምም ሴትን ከወለደ በኋላ የኖረው ሰባት መቶ ዓመት ሆነ፤ ወንዶችንም ሴቶችንም ወለደ።
5፤ አዳምም የኖረበት ዘመን ሁሉ ዘጠኝ መቶ ሠላሳ ዓመት ሆነ፤ ሞተም።
6፤ ሴትም ሁለት መቶ አምስት ዓመት ኖረ፥ ሄኖስንም ወለደ፤
7፤ ሴትም ሄኖስን ከወለደ በኋላ የኖረው ሰባት መቶ ሰባት ዓመት ሆነ፤ ወንዶችንም ሴቶችንም ወለደ።
8፤ ሴትም የኖረበት ዘመን ሁሉ ዘጠኝ መቶ አሥራ ሁለት ዓመት ሆነ፤ ሞተም።
9፤ ሄኖስም መቶ ዘጠና ዓመት ኖረ፥ ቃይናንንም ወለደ፤
10፤ ሄኖስም ቃይናንን ከወለደ በኋላ የኖረው ሰባት መቶ አሥራ አምስት ዓመት ሆነ፤ ወንዶችንም ሴቶችንም ወለደ።
11፤ ሄኖስም የኖረበት ዘመን ሁሉ ዘጠኝ መቶ አምስት ዓመት ሆነ ሞተም።
12፤ ቃይናንም መቶ ሰባ ዓመት ኖረ፥ መላልኤልንም ወለደ፤
13፤ ቃይናንም መላልኤልን ከወለደ በኋላ የኖረው ሰባት መቶ አርባ ዓመት ሆነ፤ ወንዶችንም ሴቶችንም ወለደ።
14፤ ቃይናንም የኖረበት ዘመን ሁሉ ዘጠኝ መቶ አሥር ዓመት ሆነ፤ ሞተም።
15፤ መላልኤልም መቶ ስድሳ አምስት ዓመት ኖረ፥ ያሬድንም ወለደ፤
16፤ መላልኤልም ያሬድን ከወለደ በኋላ የኖረው ሰባት መቶ ሠላሳ ዓመት ሆነ፤ ወንዶችንም ሴቶችንም ወለደ።
17፤ መላልኤልም የኖረበት ዘመን ሁሉ ስምንት መቶ ዘጠና አምስት ዓመት ሆነ፤ ሞተም።
18፤ ያሬድም መቶ ስድሳ ሁለት ዓመት ኖረ፥ ሄኖክንም ወለደ
19፤ ያሬድም ሄኖክን ከወለደ በኋላ የኖረው ስምንት መቶ ዓመት ሆነ፤ ወንዶችንም ሴቶችንም ወለደ።
20፤ ያሬድም የኖረበት ዘመን ሁሉ ዘጠኝ መቶ ስድሳ ሁለት ዓመት ሆነ፤ ሞተም።
21፤ ሄኖክም መቶ ስድሳ አምስት ዓመት ኖረ፥ ማቱሳላንም ወለደ፤
22፤ ሄኖክም አካሄዱን ከእግዚአብሔር ጋር አደረገ፤ ማቱሳላንም ከወለደ በኋላ የኖረው ሁለት መቶ ዓመት ሆነ፤ ወንዶችንም ሴቶችንም ወለደ።
23፤ ሄኖክም የኖረበት ዘመን ሁሉ ሦስት መቶ ስድሳ አምስት ዓመት ሆነ።
24፤ ሄኖክም አካሄዱን ከእግዚአብሔር ጋር ስላደረገ አልተገኘም፤ እግዚአብሔር ወስዶታልና።
25፤ ማቱሳላም መቶ ሰማኒያ ሰባት ዓመት ኖረ፥ ላሜሕንም ወለደ፤
26፤ ማቱሳላም ላሜሕን ከወለደ በኋላ የኖረው ሰባት መቶ ሰማንያ ሁለት ዓመት ሆነ፤ ወንዶችንም ሴቶችንም ወለደ።
27፤ ማቱሳላም የኖረበት ዘመን ሁሉ ዘጠኝ መቶ ስድሳ ዘጠኝ ዓመት ሆነ፤ ሞተም።
28፤ ላሜሕም መቶ ሰማንያ ሁለት ዓመት ኖረ፥ ልጅንም ወለደ።
29፤ ስሙንም። እግዚአብሔር በረገማት ምድር ከተግባራችንና ከእጅ ሥራችን ይህ ያሳርፈናል ሲል ኖኅ ብሎ ጠራው።
30፤ ላሜሕም ኖኅን ከወለደ በኋላ የኖረው አምስት መቶ ስድሳ አምስት ዓመት ሆነ፤ ወንዶችንም ሴቶችንም ወለደ።
31፤ ላሜሕ የኖረበት ዘመን ሁሉ ሰባት መቶ አርባ ሰባት ዓመት ሆነ፤ ሞተም።
32፤ ኖኅም የአምስት መቶ ዓመት ሰው ነበረ፤ ኖኅም ሴምን ካምን ያፌትንም ወለደ።