ምዕራፍ 27

1፤ ይስሐቅ ሸምግሎ ዓይኖቹ ከማየት በፈዘዙ ጊዜ ታላቁን ልጁን ዔሳውን ጠርቶ። ልጄ ሆይ አለው፤ እርሱም። እነሆ አለሁ አለው።
2፤ እርሱም አለው። እነሆ እኔ አረጀሁ፥ የምሞትበትን ቀን አላውቅም።
3፤ አሁንም ማደኛህን የፍላጻህን አፎትና ቀስትህን ውሰድ፥ ወደ ምድረ በዳም ውጣ፥ አደንም አድንልኝ፤
4፤ ሳልሞትም ነፍሴ እንድትባርክህ የጣፈጠ መብል እኔ እንደምወደው አዘጋጅተህ እበላ ዘንድ አምጣልኝ።
5፤ ርብቃም ይስሐቅ ለልጁ ለዔሳው ሲነግር ትሰማ ነበር። ዔሳውም አደን አድኖ ሊያመጣ ወደ ምድረ በዳ ሄደ።
6፤ ርብቃም ልጅዋን ያዕቆብን እንዲህ አለችው። እነሆ፥ አባትህ ለወንድምህ ለዔሳው።
7፤ አደን አድነህ አምጣልኝ፥ ሳልሞትም በልቼ በእግዚአብሔር ፊት እንድባርክህ የጣፈጠ መብል አድርግልኝ ብሎ ሲነግረው ሰማሁ።
8፤ አሁንም፥ ልጄ ሆይ፥ እኔ በማዝዝህ ነገር ስማኝ፤
9፤ ወደ መንጋ ሄደህ ሁለት መልካካም ጠቦቶች አምጣልኝ፤ እነርሱንም ጣፋጭ መብል ለአባትህ እንደሚወደው አደርጋለሁ፤
10፤ ለአባትህም፥ ሳይሞት እንዲባርክህ፥ ይበላ ዘንድ ታገባለታለህ።
11፤ ያዕቆብም ርብቃን እናቱን አላት። እነሆ ዔሳው ወንድሜ ጠጕራም ሰው ነው፥ እኔ ግን ለስላሳ ነኝ፤
12፤ ምናልባት አባቴ ቢዳስሰኝ በፊቱ እንደሚዘብት እሆናለሁ፤ መርገምንም በላዬ አመጣለሁ፥ በረከትን አይደለም።
13፤ እናቱም አለችው። ልጄ ሆይ፥ መርገምህ በእኔ ላይ ይሁን፤ ቃሌን ብቻ ስማኝ፤ ሂድና አምጣልኝ።
14፤ ሄዶም አመጣ፥ ለእናቱም ሰጣት፤ እናቱም የጣፈጠውን መብል አባቱ እንደሚወደው አደረገች።
15፤ ርብቃም ከእርስዋ ዘንድ በቤት የነበረችውን የታላቁን ልጅዋን የዔሳውን መልካሙን ልብስ አመጣች፥ ታናሹን ልጅዋን ያዕቆብንም አለበሰችው፤
16፤ የጠቦቶችንም ለምድ በእጆቹና በለስላሳው አንገቱ ላይ አደረገች፤
17፤ የሠራችውን ጣፋጭ መብልና እንጀራውን ለልጅዋ ለያዕቆብ በእጁ ሰጠችው።
18፤ ወደ አባቱም ገብቶ። አባቴ ሆይ አለው እርሱም። እነሆኝ፤ ልጄ ሆይ፥ አንተ ማን ነህ? አለ።
19፤ ያዕቆብም አባቱን አለው። የበኵር ልጅህ እኔ ዔሳው ነኝ፤ እንዳዘዝኽኝ አደረግሁ፤ ነፍስህ ትባርከኝ ዘንድ ቀና በልና ተቀመጥ፥ ካደንሁትም ብላ።
20፤ ይስሐቅም ልጁን። ልጄ ሆይ፥ እንዴት ፈጥነህ አገኘኸው? አለው። እርሱም። እግዚአብሔር አምላክህ ወደ እኔ ስለ አቀረበው ነው አለ።
21፤ ይስሐቅም ያዕቆብን። ልጄ ሆይ፥ አንተ ልጄ ዔሳው እንደ ሆንህ ወይም እንዳልሆንህ እዳስስህ ዘንድ ቅረበኝ አለው።
22፤ ያዕቆብም ወደ አባቱ ወደ ይስሐቅ ቀረበ፤ ዳሰሰውም፥ እንዲህም። ይህ ድምፅ የያዕቆብም ድምፅ ነው፥ እጆች ግን የዔሳው እጆች ናቸው አለው።
23፤ እርሱም አላወቀውም ነበር፤ እጆቹ እንደ ወንድሙ እንደ ዔሳው እጆች ጠጕራም ነበሩና፤ ስለዚህም ባረከው።
24፤ አለውም። አንተ ልጄ ዔሳው ነህን? እርሱም። እኔ ነኝ አለ።
25፤ እርሱም። ከልጄ አደን እንድበላና ነፍሴ እንድትባርክህ አቅርብልኝ አለ። አቀረበለትም፥ በላም፤ የወይን ጠጅ አመጣለት፥ እርሱም ጠጣ።
26፤ አባቱ ይስሐቅም። ልጄ ሆይ፥ ወደ እኔ ቅረብ ሳመኝም አለው።
27፤ ወደ እርሱም ቀረበ፥ ሳመውም፤ የልብሱንም ሽታ አሸተተ፥ ባረከውም፥ እንዲህም አለ። የልጄ ሽታ እግዚአብሔር እንደ ባረከው እርሻ ሽታ ነው፤
28፤ እግዚአብሔርም ከሰማይ ጠል ከምድርም ስብ የእህልንም የወይንንም ብዛት ይስጥህ፤
29፤ አሕዛብ ይገዙልህ ሕዝብም ይስገዱልህ፤ ለወንድሞችህ ጌታ ሁን፥ የእናትህም ልጆች ይስገዱልህ፤ የሚረግምህ እርሱ ርጉም ይሁን የሚባርክህም ቡሩክ ይሁን።
30፤ ይስሐቅም ያዕቆብን ባርኮ ከፈጸመ በኋላ፥ ያዕቆብም ከአባቱ ከይስሐቅ ፊት ከወጣ በኋላ፥ ወዲያው በዚያው ጊዜ ዔሳው ከአደኑ መጥቶ ገባ።
31፤ እርሱም ደግሞ ጣፋጭ መብል አዘጋጀ፥ ለአባቱም አገባ፤ አባቱንም። አባቴ ይነሣ፥ ነፍስህም ትባርከኝ ዘንድ ከልጁ አደን ይብላ አለው።
32፤ አባቱ ይስሐቅም። አንተ ማን ነህ? አለው፤ እርሱም። እኔ የበኵር ልጅህ ዔሳው ነኝ አለው።
33፤ ይስሐቅም እጅግ ደነገጠ እንዲህም አለ። ያደነውን አደን ወደ እኔ ያመጣ ማን ነው? አንተ ሳትመጣም ከሁሉ በላሁ ባረክሁትም፤ እርሱም የተባረከ ሆኖ ይኖራል።
34፤ ዔሳውም የአባቱን ቃል በሰማ ጊዜ ታላቅ እጅግም መራራ ጩኸት ጮኸ፥ አባቱንም። አባቴ ሆይ፥ እኔንም ደግሞ ባርከኝ አለው።
35፤ እርሱም። ወንድምህ በተንኮል ገብቶ በረከትህን ወሰደብህ አለ።
36፤ እርሱም አለ። በእውነት ስሙ ያዕቆብ ተባለ፥ ሁለት ጊዜ አሰናክሎኛልና፤ ብኵርናዬን ወሰደ፥ አሁንም እነሆ በረከቴን ወሰደ። ደግሞም። ለእኔ በረከትን አላስቀረህልኝምን? አለ።
37፤ ይስሐቅም መለሰ ዔሳውንም አለው። እነሆ፥ ጌታህ አደረግሁት፥ ወንድሞቹንም ሁሉ ለእርሱ ተገዦች ይሆኑ ዘንድ ሰጠሁት፥ በእህልም በወይንም አበረታሁት፤ ለአንተ ግን፥ ልጄ ሆይ፥ ምን ላድርግ?
38፤ ዔሳውም አባቱን አለው። አባቴ ሆይ፥ በረከትህ አንዲት ብቻ ናትን? አባቴ ሆይ፥ እኔንም ደግሞ ባርከኝ። ዔሳውም ቃሉን አንሥቶ አለቀሰ።
39፤ አባቱ ይስሐቅም መለሰ አለውም። እነሆ፥ መኖሪያህ ከምድር ስብ ከላይ ከሚገኝ ከሰማይም ጠል ይሆናል፤
40፤ በሰይፍህም ትኖራለህ፥ ለወንድምህም ትገዛለህ፤ ነገር ግን በተቃወምኸው ጊዜ ቀንበሩን ከአንገትህ ትጥላለህ።
41፤ ዔሳውም አባቱ ስለ ባረከው በያዕቆብ ቂም ያዘበት፤ ዔሳውም በልቡ አለ። ለአባቴ የልቅሶ ቀን ቀርቦአል፥ ከዚያም በኋላ ወንድሜን ያዕቆብን እገድለዋለሁ።
42፤ ለርብቃም ይህ የታላቁ ልጅዋ የዔሳው ቃል ደረሰላት፤ ታናሹን ልጅዋን ያዕቆብንም አስጠርታ አስመጣችው፥ አለችውም። እነሆ፥ ወንድምህ ዔሳው ሊገድልህ ይፈቅዳል።
43፤ አሁንም ልጄ ሆይ ቃሌን ስማ፤ ተነሣና ወደ ካራን ምድር ወደ ወንድሜ ወደ ላባ ሂድ፤
44፤ በእርሱም ዘንድ ጥቂት ቀን ተቀመጥ፥ የወንድምህ ቍጣ እስኪበርድ ድረስ፤
45፤ የወንድምህ ቍጣ ከአንተ እስኪመለስ ድረስ፥ ያደረግህበትንም እስኪረሳው ድረስ፤ ከዚያም ልኬ አስመጣሃለሁ፤ በአንድ ቀን ሁለታችሁን ለምን አጣለሁ?
46፤ ርብቃም ይስሐቅን አለችው። ከኬጢ ሴቶች ልጆች የተነሣ ሕይወቴን ጠላሁት፤ ያዕቆብ ከዚህ አገር ሴቶች ልጆች ሚስትን የሚያገባ ከሆነ በሕይወት መኖር ለምኔ ነው?