ምዕራፍ 23
1፤ የሣራም ዕድሜ መቶ ሀያ ሰባት ዓመት ሆነ።
2፤ በቂርያትአርባቅም ሞተች፤ እርስዋም በከነዓን ምድር ያለች ኬብሮን ናት፤ አብርሃምም ለሣራ ሊያዝንላትና ሊያለቅስላት ተነሣ።
3፤ አብርሃምም ከሬሳው አጠገብ ተነሣ፥
4፤ ለኬጢ ልጆችም እንዲህ ሲል ተናገረ። እኔ በእናንተ ዘንድ ስደተኛና መጻተኛ ነኝ፤ በእናንተ ዘንድ የመቃብር ርስት ስጡኝ፥ ሬሳዬንም ከፊቴ ልቅበር።
5፤ የኬጢ ልጆችም ለአብርሃም መለሱ፥ አሉትም።
6፤ ጌታ ሆይ፥ ስማን፤ አንተ በእኛ መካከል ከእግዚአብሔር አለቃ ነህ፤ ከመቃብር ስፍራችን በመልካሙ ቦታ ሬሳህን ቅበር፤ ሬሳህን ትቀብር ዘንድ ከእኛ መቃብሩን የሚከለክልህ የለም።
7፤ አብርሃምም ተነሣ፥ ለምድሩ ሕዝብም፥ ለኬጢ ልጆች፥ ሰገደ።
8፤ እንዲህም አላቸው። ሬሳዬን ከፊቴ እንድቀብር ከወደዳችሁስ ስሙኝ፥ ከሰዓር ልጅ ከኤፍሮንም ለምኑልኝ፤
9፤ በእርሻው ዳር ያለችውን ድርብ ክፍል ያላትን ዋሻውን በሙሉ ዋጋ በመካከላችሁ ይስጠኝ፥ መቃብሩ የእኔ ርስት እንዲሆን።
10፤ ኤፍሮንም በኬጢ ልጆች መካከል ተቀምጦ ነበር፤ የኬጢ ሰው ኤፍሮንም የኬጢ ልጆችና ወደ ከተማ የሚገቡ ሁሉ ሲሰሙ ለአብርሃም እንዲህ ሲል መለሰለት።
11፤ አይደለም፥ ጌታዬ፥ ስማኝ፤ እርሻውን ሰጥቼሃለሁ በእርሱም ዳር ያለውን ዋሻ ሰጥቼሃለሁ፤ በወገኔ ልጆች ፊት ሰጥቼሃለሁ፤ ሬሳህን ቅበር።
12፤ አብርሃምም በአገሩ ሰዎች ፊት ሰገደ፤
13፤ የአገሩ ሰዎችም ሲሰሙ ለኤፍሮን እንዲህ ሲል ተናገረ። ነገሬን ትሰማ ዘንድ እለምንሃለሁ፤ የእርሻውን ዋጋ እሰጥሃለሁ፤ አንተም ከእኔ ዘንድ ውሰድ፥ ሬሳዬንም በዚያ እቀብራለሁ።
14፤ ኤፍሮንም ለአብርሃም እንዲህ ሲል መለሰለት።
15፤ ጌታዬ ሆይ፥ እኔን ስማኝ፤ የአራት መቶ ሰቅል ዋጋ ምድር በእኔና በአንተ መካክለ ምንድር ነው? ሬሳህንም ቅበር።
16፤ አብርሃምም የኤፍሮንን ነገር ሰማ፤ አብርሃምም በኬጢ ልጆች ፊት የነገረውን አራት መቶ ሰቅል መዝኖ ለኤፍሮን ሰጠው፤ ብሩም ለመሸጫ ለመለወጫ የሚተላለፍ ነበረ።
17፤ በመምሬ ፊት ያለው ባለድርብ ክፍል የሆነው የኤፍሮን እርሻ ለአብርሃም ጸና፤
18፤ እርሻው በእርሱም ያለው ዋሻው፥ በእርሻውም ውስጥ በዙሪያውም ያለው እንጨት ሁሉ በኬጢ ልጆችና በከተማይቱ በር በሚገቡ ሁሉ ፊት ለአብርሃም ርስቱ ሆነ።
19፤ ከዚህም በኋላ ኬብሮን በምትባል በመምሬ ፊት በከነዓን ምድር ባለው እርሻ ባለ ድርብ ክፍል በሆነው ዋሻ ውስጥ አብርሃም ሚስቱን ሣራን ቀበረ።
20፤ እርሻውና በእርሱ ያለው ዋሻው በኬጢ ልጆች ዘንድ ለአብርሃም የመቃብር ርስት ሆኖ ጸና።