ምዕራፍ 29
1፤ በአሥረኛው ዓመት በአሥረኛው ወር ከወሩም በአሥራ ሁለተኛው ቀን የእግዚአብሔር ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ።
2፤ የሰው ልጅ ሆይ፥ ፊትህን በግብጽ ንጉሥ በፈርዖን ላይ አድርግ፥ በእርሱና በግብጽ ሁሉ ላይም ትንቢት ተናገር፥
3፤ እንዲህም በል። ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። በወንዞች መካከል የምትተኛና። ወንዙ የእኔ ነው ለራሴም ሠርቼዋለሁ የምትል ታላቅ አዞ፥ የግብጽ ንጉሥ ፈርዖን ሆይ፥ እነሆ፥ በአንተ ላይ ነኝ።
4፤ በመንጋጋህ መቃጥን አገባብሃለሁ፥ የወንዞችህንም ዓሦች ወደ ቅርፊትህ አጣብቃለሁ፤ ከወንዞችህም መካከል አወጣሃለሁ፥ የወንዞችህም ዓሦች ሁሉ ወደ ቅርፊትህ ይጣበቃሉ።
5፤ አንተንና የወንዞችህን ዓሦች ሁሉ ወደ ምድረ በዳ እጥላለሁ፥ በምድርም ፊት ላይ ትወድቃለህ እንጂ አትከማችም አትሰበሰብም መብልም አድርጌ ለምድር አራዊትና ለሰማይ ወፎች ሰጥቼሃለሁ።
6፤ በግብጽም የሚኖሩ ሁሉ ለእስራኤል ቤት የሸንበቆ በትር ሆነዋልና እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ።
7፤ በእጅ በያዙህ ጊዜ ተሰበርህ ጫንቃቸውንም ሁሉ አቈሰልህ፤ በተደገፉብህም ጊዜ ተሰበርህ ወገባቸውንም ሁሉ አንቀጠቀጥህ።
8፤ ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። እነሆ፥ ሰይፍ አመጣብሃለሁ፥ ሰውንና እንስሳንም ከአንተ ዘንድ አጠፋለሁ።
9፤ የግብጽም ምድር ባድማና ውድማ ትሆናለች፥ እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ፤ አንተ። ወንዙ የእኔ ነው የሠራሁትም እኔ ነኝ ብለሃልና።
10፤ ስለዚህ፥ እነሆ፥ በአንተና በወንዞችህ ላይ ነኝ፥ የግብጽንም ምድር ከሚግዶል ጀምሮ እስከ ሴዌኔና እስከ ኢትዮጵያ ዳርቻ ድረስ ውድማና ባድማ አደርጋታለሁ።
11፤ የሰው እግር አያልፍባትም የእንስሳም ኮቴ አያልፍባትም፥ እስከ አርባ ዓመትም ድረስ ማንም አይኖርባትም።
12፤ ባድማም በሆኑ ምድሮች መካከል የግብጽን ምድር ባድማ አደርጋታለሁ፥ በፈረሱትም ከተሞች መካከል ከተሞችዋ አርባ ዓመደ ፈርሰው ይቀመጣሉ፤ ግብጻውያንንም ወደ አሕዛብ እበትናቸዋለሁ በአገሮችም እዘራቸዋለሁ።
13፤ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ከአርባ ዓመት በኋላ ግብጻውያንን ከተበተኑባቸው አሕዛብ ዘንድ እሰበስባለሁ፤
14፤ የግብጽንም ምርኮ እመልሳለሁ፥ ወደ ተወለዱባትም ምድር ወደ ጳትሮስ እመልሳቸዋለሁ፤ በዚያም የተዋረደች መንግሥት ይሆናሉ።
15፤ ከሌሎች መንግሥታት ሁሉ ይልቅ የተዋረደች ትሆናለች፤ ከእንግዲህ ወዲያ በአሕዛብ ላይ ከፍ አትልም፤ በአሕዛብም ላይ እንዳይገዙ አሳንሳቸዋለሁ።
16፤ የእስራኤል ቤት እነርሱን በተከተሉ ጊዜ እርስዋ በደልን ታሳስባለች፥ ከእንግዲህም ወዲያ መታመኛ አትሆንላቸውም፤ እኔም ጌታ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ።
17፤ እንዲህም ሆነ፤ በሀያ ሰባተኛው ዓመት በመጀመሪያው ወር ከወሩም በመጀመሪያው ቀን የእግዚአብሔር ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ።
18፤ የሰው ልጅ ሆይ፥ የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር ሠራዊቱን በጢሮስ ላይ ጽኑ አገልግሎት አስገለገለ፤ ራስ ሁሉ የተላጨ ጫንቃም ሁሉ የተላጠ ሆኖአል፤ ነገር ግን በላይዋ ስላገለገለው አገልግሎት እርሱና ሠራዊቱ ደመወዝ ከጢሮስ አልተቀበሉም።
19፤ ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። እነሆ፥ የግብጽን ምድር ለባቢሎን ንጉሥ ለናቡከደነፆር እሰጠዋለሁ፥ ብዛትዋንም ይወስዳል ምርኮዋንም ይማርካል ብዝበዛዋንም ይበዘብዛል፤ ይህም ለሠራዊቱ ደመወዝ ይሆናል።
20፤ ስለ እኔ ሠርተዋልና ስለ አገልግሎቱ ደመወዝ የግብጽን ምድር ሰጥቼዋለሁ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።
21፤ በዚያ ቀን ለእስራኤል ቤት ቀንድን አበቅላለሁ፥ በመካከላቸውም ለአንተ የተከፈተ አፍን እሰጣለሁ፤ እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ።