ምዕራፍ 23
1፤ የእግዚአብሔር ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ።
2፤ የሰው ልጅ ሆይ፥ የአንዲት እናት ልጆች የሆኑ ሁለት ሴቶች ነበሩ።
3፤ በግብጽም አመነዘሩ፥ በኰረዳነታቸው አመነዘሩ፤ በዚያ ጡቶቻቸው ምዋሸሹ በዚያም የድንግልናቸውን ጡቶች ዳበሱ።
4፤ ስማቸውም የታላቂቱ ኦሖላ የእኅትዋም ኦሖሊባ ነበረ፥ ለእኔም ሆኑ ወንዶችና ሴቶች ልጆችንም ወለዱ። ስማቸውም ኦሖላ ሰማርያ ናት፤ ኦሖሊባ ደግሞ ኢየሩሳሌም ናት።
5፤ ኦሖላም ገለሞተችብኝ፥ ውሽሞችዋንም ጎረቤቶችዋን አሦራውያንን በፍቅር ተከተለቻቸው።
6፤ እነርሱም ሰማያዊ ሐር የለበሱ አለቆችና ሹማምቶች፥ መልከ መልካሞች ጐበዛዝት፥ በፈረስ ላይ የሚቀመጡ ፈረሰኞች ነበሩ።
7፤ ግልሙትናዋንም ከተመረጡ ከአሦር ሰዎች ሁሉ ጋር አደረገች፥ በፍቅር በተከተለቻቸውም ጣዖቶቻቸው ሁሉ ረከሰች።
8፤ በግብጽም የነበረውን ግልሙትናዋን አልተወችም፤ በዚያ በኰረዳነትዋ ጊዜ ከእርስዋ ጋር ተኝተው ነበር፥ የድንግልናዋንም ጡቶች ዳብሰው ነበር፥ ግልሙትናቸውንም አፍስሰውባት ነበር።
9፤ ስለዚህ በፍቅር በተከተለቻቸው በውሽሞችዋ በአሦራውያን እጅ አሳልፌ ሰጠኋት።
10፤ እነርሱም ኅፍረተ ሥጋዋን ገለጡ፤ ወንዶችና ሴቶች ልጆችዋንም ማርከው ወሰዱ፥ እርስዋንም በሰይፍ ገደሉ፤ ፍርድንም ስላደረጉባት በሴቶች መካከል መተረቻ ሆነች።
11፤ እኅትዋም ኦሖሊባ ይህን አየች፤ ሆኖም ከእርስዋ ይልቅ በፍቅር በመከተልዋ ረከሰች፥ ግልሙትናዋም ከእኅትዋ ግልሙትና ይልቅ በዛ።
12፤ አለቆችንና ሹማምቶችን ጎረቤቶችዋን ጌጠኛ ልብስ የለበሱትን በፈረሶች ላይ የሚቀመጡትን ፈረሰኞች፥ ሁሉም መልከ መልካሞችን ጐበዛዝት አሦራውያንን በፍቅር ተከተለቻቸው።
13፤ የረከሰችም እንደ ሆነች አየሁ፥ ሁለቱም አንድ መንገድ ሄደዋል።
14፤ ግልሙትናዋንም አበዛች፤ በቀይ ቀለምም የተሳለችውን የከለዳውያንን ስዕል፥ በናስ ላይ የተሳሉትን ሰዎች አየች።
15፤ በወገባቸው ዝናር የታጠቁ ራሳቸውንም በቀለማዊ መጠምጠሚያ የጠመጠሙ ነበሩ፤ ሁሉም ከተወለዱባት አገር የሆኑትን የከለዳውያንን ልጆች መስለው መሳፍንትን ይመስሉ ነበር።
16፤ ባየቻቸውም ጊዜ በፍቅር ተከተለቻቸው፥ ወደ ከላውዴዎን ምድር ወደ እነርሱ መልእክተኞችን ላከች።
17፤ የባቢሎንም ሰዎች ወደ እርስዋ ፍቅር ወዳለበት መኝታ መጡ በግልሙትናቸውም አረከሱአት፤ እርስዋም ከእነርሱ ጋር ረከሰች ነፍስዋም ከእነርሱ ተለየች።
18፤ ግልሙትናዋንም ገለጠች ኅፍረተ ሥጋዋንም አሳየች፤ ነፍሴም ከእኅትዋ እንደ ተለየች እንዲሁ ነፍሴ ከእርስዋ ተለየች።
19፤ ነገር ግን በግብጽ ምድር የገለሞተችበትን የኰረዳነትዋን ዘመን አስባ ግልሙትናዋን አበዛች።
20፤ ሥጋቸውም እንደ አህዮች ሥጋ ዘራቸውም እንደ ፈረሶች ዘር የሆነውን እነዚያን ምልምሎች በፍቅር ተከተለቻቸው።
21፤ ስለ ኰረዳነትሽ ምክንያት ግብጻውያን ጡቶችሽን በዳበሱ ጊዜ የኰረዳነትሽን ሴሰኝነት አሰብሽ።
22፤ ስለዚህ፥ ኦሖሊባ ሆይ፥ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ነፍስሽ ከእነርሱ የተለየች ውሽሞችሽን አስነሣብሻለሁ፥ በዙሪያሽም በአንቺ ላይ አመጣቸዋለሁ።
23፤ እነርሱም የባቢሎን ሰዎች ከለዳውያንም ሁሉ፥ ፋቁድ፥ ሱሔ፥ ቆዓ፥ ከእነርሱም ጋር አሦራውያን ሁሉ፥ መልከ መልካሞች ጐበዛዝት፥ አለቆችና ሹማምቶች ሁሉ፥ መሳፍንቶችና አማካሪዎች ሁሉ፥ በፈረስ ላይ የተቀመጡ ናቸው።
24፤ በመሣሪያና በሰረገላ በመንኰራኵርም በአሕዛብም ጉባኤ ይመጡብሻል፤ ጋሻና አላባሽ ጋሻ ራስ ቍርም ይዘው በዙሪያሽ ይዘጋጁብሻል፤ ፍርድንም እሰጣቸዋለሁ፥ እንደ ፍርዳቸውም ይፈርዱብሻል።
25፤ ቅንዓቴንም በአንቺ ላይ አደርጋለሁ በመዓትም ያደርጉብሻል፤ አፍንጫሽንና ጆሮሽንም ከአንቺ ይቈርጣሉ፥ ከአንቺም የቀረ በሰይፍ ይወድቃል፤ ወንዶችና ሴቶች ልጆችሽንም ማርከው ይወስዳሉ፥ ከአንቺም የቀረውን እሳት ትበላቸዋለች።
26፤ ልብስሽንም ይገፍፉሻል የክብርሽንም ጌጥ ይወስዳሉ።
27፤ ሴሰኝነትሽንም፥ ከግብጽ ምድር ያወጣሽውን ግልሙትናሽንም ከአንቺ አስቀራለሁ፤ ዓይንሽንም ወደ እነርሱ አታነሺም ግብጽንም ከዚያ ወዲያ አታስቢም።
28፤ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና። እነሆ፥ በጠላሻቸው እጅ፥ ነፍስሽ በተለየቻቸው እጅ አሳልፌ እሰጥሻለሁ፤
29፤ እነርሱም በጥል ያደርጉብሻል፥ የደከምሽበትንም ሁሉ ይወስዳሉ፥ ዕራቁትሽንና ዕርቃንሽን አድርገውም ይተዉሻል፤ የግልሙትናሽም ነውር፥ ሴሰኝነትሽና ግልሙትናሽም ሁሉ ይገለጣል።
30፤ ከአሕዛብ ጋር ስላመነዘርሽ በጣዖቶቻቸውም ስለ ረከስሽ ይህን ያደረጉብሻል።
31፤ በእኅትሽ መንገድ ሄደሻል፤ ስለዚህ ጽዋዋን በእጅሽ እሰጥሻለሁ።
32፤ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። የጠለቀውንና የሰፋውን ብዙም የሚይዘውን የእኅትሽን ጽዋ ትጠጪአለሽ፤ መሳቂያና መሳለቂያም ትሆኛለሽ።
33፤ በእኅትሽ በሰማርያ ጽዋ፥ በድንጋጤና በጥፋት ጽዋ፥ በስካርና በውርደት ትሞልያለሽ።
34፤ ትጠጪዋለሽ ትጨልጪውማለሽ ገሉንም ታኝኪዋለሽ ጡትሽንም ትሸነትሪዋለሽ፤ እኔ ተናግሬአለሁና፥ ይላል እግዚአብሔር።
35፤ ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ዘንግተሽኛልና፥ ወደ ኋላሽም ጥለሽኛልና አንቺ ደግሞ ሴሰኝነትሽንና ግልሙትናሽን ተሸከሚ።
36፤ እግዚአብሔርም እንዲህ አለኝ። የሰው ልጅ ሆይ፥ በኦሖላና በኦሖሊባ ትፈርዳለህን? ኃጢአታቸውንም ታስታውቃቸዋለህ?
37፤ አመንዝረዋልና፥ ደምም በእጃቸው አለና፥ ከጣዖቶቻቸውም ጋር አመንዝረዋልና፥ ለእኔም የወለዱአቸውን ልጆቻቸውን መብል እንዲሆኑላቸው በእሳት አሳልፈዋቸዋልና።
38፤ ይህን ደግሞ አድርገውብኛል፤ በዚያ ቀን መቅደሴን አርክሰዋል ሰንበታቴንም ሽረዋል።
39፤ ልጆቻቸውንም ለጣዖቶቻቸው በሠዉ ጊዜ፥ በዚያው ቀን ያረክሱት ዘንድ ወደ መቅደሴ ገቡ፤ እነሆም፥ በቤቴ ውስጥ እንደዚህ አደረጉ።
40፤ ደግሞ መልእክተኛ ወደ ተላከባቸው ከሩቅም ወደሚመጡ ሰዎች ልካችኋል፤ እነሆም መጡ፥ አንቺም ታጠብሽላቸው ዓይኖችሽንም ተኳልሽ ጌጥም አጌጥሽ፤
41፤ በክብር አልጋ ላይ ተቀመጥሽ፥ በፊት ለፊትዋም ማዕድ ተዘጋጅታ ነበር፥ ዕጣኔንና ዘይቴንም አኖርሽባት።
42፤ የደስተኞችም ድምፅ በእርስዋ ዘንድ ነበረ፤ ከብዙም ሰዎች ጉባኤ ጋር ሰካራሞቹ ከምድረ በዳ መጡ፤ በእጃቸው አንበር በራሳቸውም የተዋበ አክሊል አደረጉ።
43፤ እኔም በምንዝር ላረጀችው። አሁን ከእርስዋ ጋር ያመነዝራሉ እርስዋም ከእነርሱ ጋር ታመነዝራለች አልሁ።
44፤ ወደ ጋለሞታም እንደሚገቡ ወደ እርስዋ ገቡ፤ እንዲሁ ይሰስኑ ዘንድ ወደ ኦሖላና ወደ ኦሖሊባ ገቡ።
45፤ ሴቶቹ አመንዝሮች ናቸውና፥ በእጃቸውም ደም አለና ጻጽቃን ሰዎች በአመንዝሮቹና በደም አፍሳሾቹ ሴቶች ላይ በሚፈረደው ፍርድ ይፈርዱባቸዋል።
46፤ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ጉባኤን አመጣባቸዋለሁ፥ ለመበተንና ለመበዝበዝም አሳልፌ አሰጣቸዋለሁ።
47፤ ጉባኤውም በድንጋይ ይወግሩአቸዋል በሰይፋቸውም ይቈርጡአቸዋል፥ ወንዶችና ሴቶች ልጆቻቸውንም ይገድላሉ፥ ቤቶቻቸውንም በእሳት ያቃጥላሉ።
48፤ ሴቶችም ሁሉ እንደ ሴሰኝነታችሁ እንዳይሠሩ ይማሩ ዘንድ ሴሰኝነትን ከምድር ላይ አጠፋለሁ።
49፤ ሴሰኝነታችሁንም በላያችሁ ላይ ይመልሳሉ፥ እናንተም የጣዖቶቻችሁን ኃጢአት ትሸከማላችሁ፤ እኔም ጌታ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቃላችሁ።