ምዕራፍ 9
1፤ አዳር በሚባለውም በአሥራ ሁለተኛው ወር ከወሩም በአሥራ ሦስተኛው ቀን፥ የንጉሡ ትእዛዝና አዋጅ ሊፈጸምበት በነበረው ቀን፥ የአይሁድ ጠላቶች ሊሠለጥኑባቸው በነበረው ቀን፥ አይሁድ በጠላቶቻቸው ላይ እንዲሠለጥኑ ነገሩ ተገለበጠ።
2፤ አይሁድም ክፋታቸውን በሚሹት ሰዎች ላይ እጃቸውን ይዘረጉ ዘንድ በንጉሡ በአርጤክስስ አገሮች ሁሉ በነበሩ ከተሞቻቸው ውስጥ ተሰበሰቡ፤ እነርሱንም መፍራት በአሕዛብ ሁሉ ላይ ወድቆ ነበርና እነርሱን የሚቃወም ሰው አልነበረም።
3፤ መርዶክዮስን መፍራት በላያቸው ስለ ወደቀ በየአገሩ የነበሩ አዛውንትና ሹማምቶች አለቆችም፥ የንጉሡንም ሥራ የሚሠሩቱ ሁሉ አይሁድን አገዙ።
4፤ ያ ሰው መርዶክዮስ ከፍ ከፍ እያለ ስለ ሄደ በንጉሡ ቤት ታላቅ ሆኖ ነበርና፥ የመርዶክዮስም ዝና በየአገሩ ሁሉ ተሰምቶ ነበርና።
5፤ አይሁድም ጠላቶቻቸውን ሁሉ በሰይፍ እየመቱ ገደሉአቸው፥ አጠፉአቸውም፤ በሚጠሉአቸውም ላይ እንደ ወደዱ አደረጉባቸው።
6፤ አይሁድም በሱሳ ግንብ አምስት መቶ ያህል ሰዎች ገደሉ አጠፉም።
7፤
8፤ ፈርሰኔስ፥ ደልፎን፥ ፋስጋ፥ ፋረዳታ፥
9፤ በርያ፥ ሰርባካ፥ መርመሲማ፥ ሩፋዮስ፥ አርሳዮስ፥ ዛቡታዮስ የሚባሉትን፥
10፤ የሐመዳቱን ልጅ የአይሁድን ጠላት አሥሩን የሐማን ልጆች ገደሉ፤ ነገር ግን ወደ ብዝበዛው እጃቸውን አልዘረጉም።
11፤ በዚያም ቀን በሱሳ ግንብ የተገደሉት ሰዎች ቍጥር ወደ ንጉሡ መጣ።
12፤ ንጉሡም ንግሥቲቱን አስቴርን። አይሁድ በሱሳ ግንብ አምስት መቶ ሰዎችንና አሥሩን የሐማ ልጆች ገደሉ አጠፉአቸውም፤ በቀሩትስ በንጉሡ አገሮች እንዴት አድርገው ይሆን! አሁንስ ልመናሽ ምንድር ነው? ይሰጥሻል፤ ሌላስ የምትሺው ምንድር ነው? ይደረጋል አላት።
13፤ አስቴርም። ንጉሡን ደስ ቢያሰኘው በሱሳ የሚኖሩ አይሁድ ዛሬ እንደ ተደረገው ትእዛዝ ነገ ደግሞ ያድርጉ፤ አሥሩም የሐማ ልጆች በግንድ ላይ ይሰቀሉ አለች።
14፤ ንጉሡም ይህ ይደረግ ዘንድ አዘዘ፤ አዋጅም በሱሳ ተነገረ፤ አሥሩንም የሐማን ልጆች ሰቀሉ።
15፤ በሱሳም የነበሩ አይሁድ አዳር በሚባለው ወር በአሥራ አራተኛው ቀን ደግሞ ተሰብስበው በሱሳ ሦስት መቶ ያህል ሰዎች ገደሉ፤ ነገር ግን ወደ ብዝበዛው እጃቸውን አልዘረጉም።
16፤ የቀሩትም በንጉሡ አገር ያሉ አይሁድ ተሰብስበው ለሕይወታቸው ቆሙ፥ ከጠላቶቻቸውም ዐረፉ፤ ከሚጠሉአቸውም ሰባ አምስት ሺህ ገደሉ፤ ነገር ግን ወደ ብዝበዛው እጃቸውን አልዘረጉም።
17፤ አዳር በሚባለው ወር በአሥራ ሦስተኛው ቀን ይህ ተደረገ፤ በአሥራ አራተኛውም ቀን ዐረፉ፥ የግብዣና የደስታም ቀን አደረጉ።
18፤ በሱሳ የነበሩት አይሁድ ግን በአሥራ ሦስተኛውና በአሥራ አራተኛው ቀን ተሰበሰቡ፤ በአሥራ አምስተኛውም ቀን ዐረፉ፥ የመጠጥና የደስታም ቀን አደረጉት።
19፤ ስለዚህም በመንደሮችና ባልተመሸጉ ከተሞች የሚኖሩ አይሁድ አዳር በሚባለው ወር አሥራ አራተኛውን ቀን የደስታና የመጠጥ የመልካምም ቀን፥ እርስ በርሳቸውም ስጦታ የሚሰጣጡበት ቀን ያደርጉታል።
20፤ መርዶክዮስም ይህን ነገር ጻፈ፥ በንጉሡም በአርጤክስስ አገሮች ሁሉ በቅርብና በሩቅ ወዳሉት አይሁድ ሁሉ ደብዳቤዎችን ላከ።
21፤ በየዓመቱም አዳር በሚባለው ወር አሥራ አራተኛውና አሥራ አምስተኛው ቀን፥
22፤ አይሁድ ከጠላቶቻቸው ዕረፍትን ያገኙበት ቀን፥ ወሩም ከኀዘን ወደ ደስታ ከልቅሶም ወደ መልካም ቀን የተለወጠበት ወር ሆኖ ይጠብቁት ዘንድ፥ የግብዣና የደስታም ቀን፥ እርስ በርሳቸውም ስጦታ የሚሰጣጡበትና ለድሆች ስጦታ የሚሰጡበት ቀን ያደርጉት ዘንድ አዘዛቸው።
23፤ አይሁድም ለመሥራት የጀመሩትን፥ መርዶክዮስም የጻፈላቸውን ያደርጉ ዘንድ ተቀበሉት፤
24፤ አጋጋዊው የሐመዳቱ ልጅ የአይሁድ ሁሉ ጠላት ሐማ አይሁድን ያጠፋ ዘንድ ተተንኵሎ ነበር፤ ሊደመስሳቸውና ሊያጠፋቸውም ፉር የሚባል ዕጣ ጥሎ ነበር።
25፤ አስቴርም ወደ ንጉሡ ፊት በገባች ጊዜ በአይሁድ ላይ የተተነኰለው ክፉ ተንኰል በራሱ ላይ እንዲመለስ፥ እርሱና ልጆቹም በግንድ ላይ እንዲሰቀሉ በደብዳቤው አዘዘ።
26፤ ስለዚህም እነዚህ ቀኖች እንደ ፉር ስም ፉሪም ተባሉ። በዚህም ደብዳቤ ስለ ተጻፈው ቃል ሁሉ፥ ስላዩትና ስላገኙአቸውም ነገር ሁሉ፥
27፤
28፤ አይሁድ እነዚህን ሁለት ቀኖች እንደ ጽሕፈቱና እንደ ጊዜው በየዓመቱ ይጠብቁ ዘንድ፥ እነዚህም ቀኖች በየትውልዳቸውና በየወገናቸው በየአገራቸውም በየከተማቸውም የታሰቡና የተከበሩ ይሆኑ ዘንድ፥ እነዚህም የፉሪም ቀኖች በአይሁድ ዘንድ እንዳይሻሩ፥ መታሰባቸውም ከዘራቸው እንዳይቈረጥ፥ በራሳቸውና በዘራቸው ወደ እነርሱም በተጠጉት ሁሉ ላይ እንዳይቀር ሥርዓት አድርገው ተቀበሉ።
29፤ የአቢካኢልም ልጅ ንግሥቲቱ አስቴርና አይሁዳዊው መርዶክዮስ ይህችን ስለ ፉሪም የምትናገረውን ሁለተኛይቱን ደብዳቤ በሥልጣናቸው ሁሉ ያጸኑአት ዘንድ ጻፉ።
30፤ ደብዳቤዎቹንም በአርጤክስስ መንግሥት በመቶ ሀያ ሰባቱ አገሮች ወዳሉ አይሁድ ሁሉ በሰላምና በእውነት ቃል ላኩ።
31፤ እነዚህንም የፉሪም ቀኖች፥ አይሁዳዊው መርዶክዮስና ንግሥቲቱ አስቴር እንዳዘዙ፥ ለራሳቸውና ለዘራቸውም የጾማቸውንና የልቅሶአቸውን ነገር ለማክበር እንደ ተቀበሉ፥ በየጊዜያቸው ያጸኑ ዘንድ ጻፉ።
32፤ የአስቴርም ትእዛዝ ይህን የፉሪምን ነገር አጸና፤ በመጽሐፍም ተጻፈ።