መጽሐፈ አስቴር። - Esther

ምዕራፍ: 1 2 3 4 5 6 7 8 9 10


ምዕራፍ 2

1፤ ከዚህም ነገር በኋላ የንጉሡ የአርጤክስስ ቍጣ በበረደ ጊዜ አስጢንና ያደረገችውን የፈረደባትንም ነገር አሰበ።
2፤ ንጉሡንም የሚያገለግሉ ብላቴኖች እንዲህ አሉት። መልከ መልካም የሆኑ ደናግል ለንጉሡ ይፈለጉለት፤
3፤ ሴቶችን ከሚጠብቅ ከንጉሡ ጃንደረባ ከሄጌ እጅ በታች እንዲያደርጓቸው መልከ መልካሞቹን ደናግል ሁሉ ወደ ሱሳ ግንብ ወደ ሴቶች ቤት ይሰበስቡአቸው ዘንድ ንጉሡ በመንግሥቱ አገሮች ሁሉ ሹማምቶችን ያኑር፤ ቅባትና የሚያስፈልጋቸውም ይሰጣቸው፤
4፤ ንጉሡንም ደስ የምታሰኝ ቆንጆ በአስጢን ስፍራ ትንገሥ። ይህም ነገር ንጉሡን ደስ አሰኘው፥ እንዲሁም አደረገ።
5፤ አንድ አይሁዳዊ የቂስ ልጅ የሰሜኢ ልጅ የኢያዕር ልጅ መርዶክዮስ የሚባል ብንያማዊ በሱሳ ግንብ ነበረ።
6፤ እርሱም የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር ከማረካቸው ከይሁዳ ንጉሥ ከኢኮንያን ጋር ከተማረኩት ምርኮኞች ጋር ከኢየሩሳሌም የተማረከ ነበረ።
7፤ አባትና እናትም አልነበራትምና የአጎቱ ልጅ ሀደሳ የተባለችውን አስቴርን አሳድጎ ነበር፤ ቆንጆይቱም የተዋበችና መልከ መልካም ነበረች፤ አባትዋና እናትዋም ከሞቱ በኋላ መርዶክዮስ እንደ ልጁ አድርጎ ወስዶአት ነበር።
8፤ የንጉሡም ትእዛዝና አዋጅ በተሰማ ጊዜ፥ ብዙም ቈነጃጅት ወደ ሱሳ ግንብ ወደ ሄጌ እጅ በተሰበሰቡ ጊዜ፥ አስቴር ወደ ንጉሡ ቤት ወደ ሴቶች ጠባቂው ወደ ሄጌ ተወሰደች።
9፤ ቆንጆይቱም ደስ አሰኘችው፥ በእርሱም ዘንድ ሞገስ አገኘች፤ ቅባትዋንም ድርሻዋንም ከንጉሡም ቤት ልታገኝ የሚገባትን ሰባት ደንገጥሮች ፈጥኖ ሰጣት፤ እርስዋንና ደንገጥሮችዋንም በሴቶች ቤት በተመረጠ ስፍራ አኖረ።
10፤ ይህንም እንዳትናገር መርዶክዮስ አዝዞአት ነበርና አስቴር ሕዝብዋንና ወገንዋን አልተናገረችም።
11፤ መርዶክዮስም የአስቴርን ደኅንነትና የሚሆንላትን ያውቅ ዘንድ ዕለት ዕለት በሴቶች ቤት ወለል ትይዩ ይመላለስ ነበር።
12፤ የመንጻታቸውም ወራት ስድስት ወር ያህል በከርቤ ዘይት፥ ስድስት ወርም በጣፋጭ ሽቱና በልዩ ልዩም በሚያነጻ ነገር ይፈጸም ነበርና እንደ ሴቶች ወግ አሥራ ሁለት ወር እንዲሁ ከተደረገላት በኋላ ወደ ንጉሡ ወደ አርጤክስስ ለመግባት የአንዳንዲቱ ቆንጆ ተራ በደረሰ ጊዜ፥
13፤ በዚህ ወግ ቆንጆይቱ ወደ ንጉሡ ትገባ ነበር፤ ከሴቶች ቤት ወደ ንጉሡ ቤት ለመውሰድ የምትሻውን ሁሉ ይሰጡአት ነበር።
14፤ ማታም ትገባ ነበር፥ ሲነጋም ተመልሳ ወደ ሁለተኛው ሴቶች ቤት ቁባቶችን ወደሚጠብቅ ወደ ንጉሡ ጃንደረባ ወደ ጋይ ትመጣ ነበር፤ ንጉሡም ያልፈለጋት እንደ ሆነ፥ በስምዋም ያልተጠራች እንደሆነ፥ ከዚያ ወዲያ ወደ ንጉሡ አትገባም ነበር።
15፤ ወደ ንጉሡም ትገባ ዘንድ የመርዶክዮስ አጎት የአቢካኢል ልጅ የአስቴር ተራ በደረሰ ጊዜ የሴቶች ጠባቂው የንጉሡ ጃንደረባ ሄጌ ከሚለው በቀር ምንም አልፈለገችም ነበር፤ አስቴርም በሚያዩአት ሁሉ ዓይን ሞገስ አግኝታ ነበርና።
16፤ አርጤክስስም በነገሠ በሰባተኛው ዓመት አዳር በሚባለው በአሥራ ሁለተኛው ወር አስቴር ወደ ንጉሡ ቤት ተወሰደች።
17፤ ንጉሡም ከሴቶች ሁሉ ይልቅ አስቴርን ወደደ፥ በዓይኑም ከደናግል ሁሉ ይልቅ ሞገስንና መወደድን አገኘች፤ የመንግሥቱንም ዘውድ በራስዋ ላይ አደረገ፥ በአስጢንም ፋንታ አነገሣት።
18፤ ንጉሡም ስለ አስቴር ለባለምዋሎቹና ለአገልጋዮቹ ሁሉ ሰባት ቀን ያህል ትልቅ ግብዣ አደረገ፤ ለአገሮቹም ሁሉ ይቅርታ አደረገ፥ እንደ ንጉሡም ለጋስነት መጠን ስጦታ ሰጠ።
19፤ ደናግሉም ዳግመኛ በተሰበሰቡ ጊዜ መርዶክዮስ በንጉሡ በር ይቀመጥ ነበር።
20፤ አስቴርም ከእርሱ ጋር እንዳደገችበት ጊዜ የመርዶክዮስን ትእዛዝ ታደርግ ነበርና መርዶክዮስ እንዳዘዛት አስቴር ወገንዋንና ሕዝብዋን አልተናገረችም።
21፤ በዚያም ወራት መርዶክዮስ በንጉሡ በር ተቀምጦ ሳለ ደጁን ከሚጠብቁት ከንጉሡ ጃንደረቦች ሁለቱ ገበታና ታራ ተቈጡ፥ እጃቸውንም በንጉሡ በአርጤክስስ ላይ ያነሡ ዘንድ ፈለጉ።
22፤ ነገሩም ለመርዶክዮስ ተገለጠ፥ እርሱም ለንግሥቲቱ ለአስቴር ነገራት፤ አስቴርም በመርዶክዮስ ስም ለንጉሡ ነገረች።
23፤ ነገሩም ተመረመረ፥ እንዲህም ሆኖ ተገኘ፥ ሁለቱም በዛፍ ላይ ተሰቀሉ፤ ያም በንጉሡ ፊት በታሪክ መጽሐፍ ተጻፈ።