መጽሐፈ ዜና መዋዕል ካልዕ። - 2 Chronicles

ምዕራፍ: 1 2 3 4 5 6 7 8 9 10 11 12 13 14 15 16 17 18 19 20 21 22 23 24 25 26 27 28 29 30 31 32 33 34 35 36


ምዕራፍ 3

1፤ ሰሎሞንም እግዚአብሔር ለአባቱ ለዳዊት በተገለጠበት በሞሪያ ተራራ ዳዊት ባዘጋጀው ስፍራ በኢያቡሳዊው በኦርና አውድማ በኢየሩሳሌም የእግዚአብሔርን ቤት መሥራት ጀመረ።
2፤ በነገሠም በአራተኛው ዓመት በሁለተኛው ወር መሥራት ጀመረ።
3፤ ሰሎሞንም የእግዚአብሔርን ቤት ይሠራ ዘንድ የጣለው መሠረት ይህ ነው፤ ርዝመቱም በዱሮው ስፍር ስድሳ ክንድ፥ ወርዱም ሀያ ክንድ ነበረ።
4፤ በቤቱም ፊት የነበረው ወለል ርዝመቱ እንደ ቤቱ ወርድ ሀያ ክንድ፥ ቁመቱም መቶ ሀያ ክንድ ነበረ፤ ውስጡንም በጥሩ ወርቅ ለበጠው።
5፤ ታላቁንም ቤት በጥድ እንጨት ከደነው፥ በጥሩም ወርቅ ለበጠው፤ የዘንባባና የሰንሰለት አምሳል ቀረጸበት።
6፤ ቤቱንም በዕንቍ አስጌጠው፤ ወርቁንም የፈርዋይም ወርቅ ነበረ።
7፤ ቤቱንም ሰረገሎቹንም መድረኮቹንም ግንቦቹንም ደጆቹንም በወርቅ ለበጠ፤ በግንቦቹም ላይ ኪሩቤልን ቀረጸ።
8፤ ቅድስተ ቅዱሳኑንም ሠራ፤ ርዝመቱም እንደ ቤቱ ወርድ ሀያ ክንድ፥ ወርዱም ሀያ ክንድ ነበረ፤ ስድስት መቶ መክሊት በሚያህል በጥሩ ወርቅ ለበጠው።
9፤ የምስማሮቹም ሚዛን አምሳ ሰቅል ወርቅ ነበረ። የደርቡንም ጓዳዎች በወርቅ ለበጠ።
10፤ በቅድስተ ቅዱሳንም ውስጥ ከእንጨት ሥራ ሁለቱ ኪሩቤልን ሠራ፥ በወርቅም ለበጣቸው።
11፤ የኪሩቤልም ክንፎች ሀያ ክንድ ሙሉ ተዘርግተው ነበር፤ የአንዱ ኪሩብ ክንፍ አምስት ክንድ ነበረ፥ የቤቱንም ግንብ ይነካ ነበረ፤ ሁለተኛው ክንፍ አምስት ክንድ ነበረ፥ የሁለተኛውንም ኪሩብ ክንፍ ይነካ ነበር።
12፤ የሁለተኛውም ኪሩብ ክንፍ አምስት ክንድ ነበረ፥ የቤቱንም ግንብ ይነካ ነበር፤ ሁለተኛውም ክንፍ አምስት ክንድ ነበረ፥ የሌላውንም ኪሩብ ክንፍ ይነካ ነበር።
13፤ የእነዚህም ኪሩቤል ክንፎች ሀያ ክንድ ሙሉ ተዘርግተው ነበር፤ በእግራቸውም ቆመው ነበር፥ ፊቶቻቸውም ወደ ቤቱ ይመለከቱ ነበር።
14፤ ከሰማያዊውም ከሐምራዊውም ከቀዩም ሐር ከጥሩም በፍታ መጋረጃውን ሠራ፥ ኪሩቤልንም ጠለፈበት።
15፤ በቤቱም ፊት ቁመታቸው ሠላሳ አምስት ክንድ የነበረውን ሁለቱን ዓምዶች ሠራ፥ በእያንዳንዳቸውም ላይ የነበረው ጕልላት አምስት ክንድ ነበረ።
16፤ እንደ ድሪ ያሉ ሰንሰለቶችንም ሠርቶ በአዕማዱ ራስ ላይ አደረጋቸው፤ መቶም ሮማኖች ሠርቶ በሰንሰለቱ ላይ አደረጋቸው።
17፤ አዕማዶቹንም አንደኛውን በቀኝ፥ ሁለተኛውን በግራ በመቅደሱ ፊት አቆማቸው፤ በቀኝም የነበረውን ስም ያቁም በግራም የነበረውን ስም በለዝ ብሎ ጠራቸው።