ምዕራፍ 5
1፤ የሶርያ ንጉሥ ሠራዊት አለቃ ንዕማንም እግዚአብሔር በእርሱ እጅ ለሶርያ ደኅንነትን ስለ ሰጠ በጌታው ዘንድ ታላቅ ክቡር ሰው ነበረ፤ ደግሞም ጽኑዕ ኃያል ነበረ፥ ነገር ግን ለምጻም ነበረ።
2፤ ከሶርያውያንም አገር አደጋ ጣዮች ወጥተው ነበር፥ ከእስራኤልም ምድር ታናሽ ብላቴና ሴት ማርከው ነበር፤ የንዕማንንም ሚስት ታገለግል ነበር።
3፤ እመቤትዋንም። ጌታዬ በሰማርያ ካለው ከነቢዩ ፊት ቢደርስ ኖሮ ከለምጹ በፈወሰው ነበር አለቻት።
4፤ ንዕማንም ገብቶ ለጌታው። ከእስራኤል አገር የሆነች አንዲት ብላቴና እንዲህና እንዲህ ብላለች ብሎ ነገረው።
5፤ የሶርያም ንጉሥ ንዕማንን። ሂድ፥ ለእስራኤል ንጉሥ ደብዳቤ እልካለሁ አለው። እርሱም ሄደ፥ አሥርም መክሊት ብር፥ ስድስት ሺህም ወርቅ፥ አሥርም መለውጫ ልብስ በእጁ ወሰደ።
6፤ ለእስራኤልም ንጉሥ። ይህች ደብዳቤ ወደ አንተ ስትደርስ ባሪያዬን ንዕማንን ከለምጹ ትፈውሰው ዘንድ እንደ ሰደድሁልህ እወቅ የሚል ደብዳቤ ወሰደ።
7፤ የእስራኤልም ንጉሥ ደብዳቤውን ባነበበ ጊዜ ልብሱን ቀድዶ። ሰውን ከለምጹ እፈውስ ዘንድ ይህ ሰው ወደ እኔ መስደዱ እኔ በውኑ ለመግደልና ለማዳን የምችል አምላክ ሆኜ ነውን? ተመልከቱ፥ የጠብ ምክንያትም እንደሚፈልግብኝ እዩ አለ።
8፤ የእግዚአብሔርም ሰው ኤልሳዕ የእስራኤል ንጉሥ ልብሱን እንደ ቀደደ በሰማ ጊዜ። ልብስህን ለምን ቀደድህ? ወደ እኔ ይምጣ፥ በእስራኤልም ዘንድ ነቢይ እንዳለ ያውቃል ብሎ ወደ ንጉሡ ላከ።
9፤ ንዕማንም በፈረሱና በሰረገላው መጣ፥ በኤልሳዕም ቤት ደጃፍ ውጭ ቆመ።
10፤ ኤልሳዕም። ሂድ፥ በዮርዳኖስም ሰባት ጊዜ ታጠብ፤ ሥጋህም ይፈወሳል፥ አንተም ንጹሕ ትሆናለህ ብሎ ወደ እርሱ መልእክተኛ ላከ።
11፤ ንዕማን ግን ተቈጥቶ ሄደ፥ እንዲህም አለ። እነሆ፥ ወደ እኔ የሚመጣ፥ ቆሞም የአምላኩን የእግዚአብሔርን ስም የሚጠራ፥ የለምጹንም ስፍራ በእጁ ዳስሶ የሚፈውሰኝ መስሎኝ ነበር።
12፤ የደማስቆ ወንዞች አባናና ፋርፋ ከእስራኤል ውኆች ሁሉ አይሻሉምን? በእነርሱስ ውስጥ መታጠብና መንጻት አይቻለኝም ኖሮአልን? ዘወርም ብሎ ተቈጥቶ ሄደ።
13፤ ባሪያዎቹም ቀርበው። አባት ሆይ፥ ነቢዩ ታላቅ ነገርስ እንኳ ቢነግርህ ኖሮ ባደረግኸው ነበር፤ ይልቁንስ። ታጠብና ንጹሕ ሁን ቢልህ እንዴት ነዋ! ብለው ተናገሩት።
14፤ ወረደም፥ የእግዚአብሔርም ሰው እንደ ተናገረው በዮርዳኖስ ሰባት ጊዜ ብቅ ጥልቅ አለ፤ ሥጋውም እንደ ገና እንደ ትንሽ ብላቴና ሥጋ ሆኖ ተመለሰ፥ ንጹሕም ሆነ።
15፤ እርሱም ከጭፍራው ሁሉ ጋር ወደ እግዚአብሔር ሰው ተመለሰ፥ ወጥቶም በፊቱ ቆመና። እነሆ፥ ከእስራኤል ዘንድ በቀር በምድር ሁሉ አምላክ እንደሌለ አወቅሁ፤ አሁንም ከባሪያህ በረከት ትቀበል ዘንድ እለምንሃለሁ አለ።
16፤ እርሱም። በፊቱ የቆምሁት ሕያው እግዚአብሔርን! አልቀበልም አለ። ይቀበለውም ዘንድ ግድ አለው፤ እርሱ ግን እንቢ አለ።
17፤ ንዕማንም። እኔ ባሪያህ ከእንግዲህ ወዲህ ከእግዚአብሔር በቀር ለሌሎች አማልክት የሚቃጠል መሥዋዕት ወይም ሌላ መሥዋዕት አላቀርብምና ሁለት የበቅሎ ጭነት አፈር እንድወስድ እሺ ትለኝ ዘንድ እለምንሃለሁ።
18፤ እግዚአብሔርም ለእኔ ለባሪያህ በዚህ ነገር ብቻ ይቅር ይበለኝ፤ ጌታዬ በዚያ ይሰግድ ዘንድ እጄን ተደግፎ ወደ ሬሞን ቤት በገባ ጊዜ፥ እኔም በሬሞን ቤት በሰገድሁ ጊዜ፥ እግዚአብሔር በዚህ ነገር ለእኔ ለባሪያህ ይቅር ይበለኝ አለ።
19፤ እርሱም። በደኅና ሂድ አለው። አንድ አግድመትም ያህል ከእርሱ ራቀ።
20፤ የእግዚአብሔርም ሰው ሎሌ ግያዝ። ጌታዬ ሶርያዊውን ይህን ንዕማንን ማረው፥ ካመጣለትም ነገር ምንም አልተቀበለም፤ ሕያው እግዚአብሔርን! በስተ ኋለው እሮጣለሁ፥ ከእርሱም አንዳች እወስዳለሁ አለ።
21፤ ግያዝም ንዕማንን ተከተለው፤ ንዕማንም ወደ እርሱ ሲሮጥ ባየው ጊዜ ሊገናኘው ከሰረገላው ወርዶ። ሁሉ ደኅና ነውን? አለው።
22፤ እርሱም። ደኅና ነው። አሁን ከነቢያት ወገን የሆኑት ሁለት ጕልማሶች ከተራራማው ከኤፍሬም አገር ወደ እኔ መጥተዋል፤ አንድ መክሊት ብርና ሁለት መለወጫ ልብስ ትሰጣቸው ዘንድ እለምንሃለሁ ብሎ ጌታዬ ላከኝ አለ።
23፤ ንዕማንም። ሁለት መክሊት ትወስድ ዘንድ ይፈቀድልህ አለ፤ ግድ አለውም፤ ሁለቱንም መክሊት ብር በሁለት ከረጢት ውስጥ አሰረና ከሁለት መለወጫ ልብስ ጋር ለሁለት ሎሌዎቹ አስያዘ፤ እነርሱም ተሸክመው በፊቱ ሄዱ።
24፤ ወደ ኮረብታውም በመጣ ጊዜ ከእጃቸው ወስዶ በቤቱ ውስጥ አኖራቸው፤ ሰዎቹንም አሰናበተ፥ እነርሱም ሄዱ።
25፤ እርሱ ግን ገብቶ በጌታው ፊት ቆመ፤ ኤልሳዕም። ግያዝ ሆይ፥ ከወዴት መጣህ? አለው። እርሱም። እኔ ባሪያህ ወዴትም አልሄድሁም አለ።
26፤ እርሱም። ያ ሰው ከሰረገላው ወርዶ ሊቀበልህ በተመለሰ ጊዜ ልቤ ከአንተ ጋር አልሄደምን? ብሩንና ልብሱን፥ የወይራውንና የወይኑን ቦታ፥ በጎችንና በሬዎችን፥ ወንዶችንና ሴቶችን ባሪያዎች ትቀበል ዘንድ ይህ ጊዜው ነውን?
27፤ እንግዲህስ የንዕማን ለምጽ በአንተ ላይ፥ ለዘላለምም በዘርህ ላይ ይጣበቃል አለው። እንደ በረዶም ለምጻም ሆኖ ከእርሱ ዘንድ ወጣ።