መጽሐፈ ነገሥት ካልዕ። - 2 Kings

ምዕራፍ: 1 2 3 4 5 6 7 8 9 10 11 12 13 14 15 16 17 18 19 20 21 22 23 24 25


ምዕራፍ 12

1፤ ኢዮአስም መንገሥ በጀመረ ጊዜ የሰባት ዓመት ልጅ ነበረ።
2፤ በኢዩ በሰባተኛው ዓመት ኢዮአስ መንገሥ ጀመረ፥ በኢየሩሳሌምም አርባ ዓመት ነገሠ፤ እናቱም ሳብያ የተባለች የቤርሳቤህ ሴት ነበረች።
3፤ ካህኑ ዮዳሄም ያስተምረው በነበረ ዘመን ሁሉ ኢዮአስ በእግዚአብሔር ፊት ቅን ነገር አደረገ።
4፤ ነገር ግን በኮረብቶቹ ላይ ያሉት መስገጃዎች አልተወገዱም፤ ሕዝቡም ገና በኮረብቶቹ ላይ ባሉት መስገጃዎች ይሠዋና ያጥን ነበር።
5፤ ኢዮአስም ካህናቱን። ወደ እግዚአብሔር ቤት የሚገባውን የተቀደሰውን ገንዘብ ሁሉ፥ ስለ ነፍሱም ዋጋ የሚቀርበውን ገንዘብ፥ በልባቸውም ፈቃድ ወደ እግዚአብሔር ቤት የሚያመጡትን ገንዘብ ሁሉ፥
6፤ ካህናቱ እያንዳንዱ ሰው ከሚያመጣው ይውሰዱ በመቅደስም ውስጥ የተናዱትን ይጠግኑበት አላቸው።
7፤ ነገር ግን እስከ ንጉሡ እስከ ኢዮአስ እስከ ሀያ ሦስተኛው ዓመት ድረስ በመቅደሱ ውስጥ የተናዱትን ካህናቱ አልጠገኑትም ነበር።
8፤ ኢዮአስም ካህኑን ዮዳሄንና ካህናቱን ጠርቶ። በመቅደሱ ውስጥ የተናዱትን ስፍራዎች ስለ ምን አትጠግኑአቸውም? ከእንግዲህ ወዲያ ገንዘቡ ለቤቱ መጠገኛ ይሰጥ እንጂ ከሚያመጡት ሰዎች አትቀበሉ አላቸው።
9፤ ካህናቱም። ከሕዝቡ ገንዘቡን አንወስድም፥ በቤቱም ውስጥ የተናዱትን አንጠግንም ብለው እሺ አሉ።
10፤ ካህኑ ዮዳሄ ግን ሣጥን ወስዶ መክደኛውን ነደለው፥ በመሠዊያውም አጠገብ ወደ እግዚአብሔር ቤት በሚገቡበት መግቢያ በስተ ቀኝ አኖረው፤ ደጁንም የሚጠብቁ ካህናት ወደ እግዚአብሔር ቤት የሚመጣውን ገንዘብ ሁሉ ያኖሩበት ነበር።
11፤ በሣጥንም ውስጥ ብዙ ገንዘብ መኖሩን ባዩ ጊዜ የንጉሡ ጸሐፊና የካህናቱ አለቃ ይመጡ ነበር፥ በእግዚአብሔርም ቤት የተገኘውን ቈጥረው በከረጢት ውስጥ ያኖሩት ነበር።
12፤ የተመዘነውንም ገንዘብ የእግዚአብሔርን ቤት ለመሥራት በተሾሙት እጅ ይሰጡ ነበር።
13፤ የተናደውን የእግዚአብሔርን ቤት ለመጠገን መክፈል ለሚያሻው ሁሉ ድንጋይና እንጨት ይገዙ ዘንድ የእግዚአብሔርን ቤት ለሚሠሩ አናጢዎችና ሠራተኞች ግንበኞችና ድንጋይ ወቃሪዎች ይሰጡት ነበር።
14፤ ነገር ግን ወደ እግዚአብሔር ቤት ከሚመጣው ገንዘብ ለእግዚአብሔር ቤት የሚሆኑ የብር ጽዋዎችና ጕጠቶች ድስቶችም መለከቶችም የወርቅና የብር ዕቃዎችም አልተሠሩም ነበር።
15፤ ነገር ግን ለሚሠሩት ይሰጡት ነበር፤ የእግዚአብሔርንም ቤት ጠገኑበት።
16፤ ለሠራተኞችም ይከፍሉ ዘንድ ገንዘቡን የሚወስዱትን ሰዎች አይቆጣጠሩአቸውም ነበር፤ በታማኝነት ይሠሩ ነበርና።
17፤ ስለ በደልና ሰለ ኃጢአት መሥዋዕት የቀረበውም ገንዘብ ለካህናት ነበረ እንጂ ወደ እግዚአብሔር ቤት አያገቡትም ነበር።
18፤ በዚያም ወራት የሶርያ ንጉሥ አዛሄል ወጥቶ ጌትን ወጋ፥ ያዘውም፤ አዛሄልም ወደ ኢየሩሳሌም ለመውጣት ፊቱን አቀና።
19፤ የይሁዳም ንጉሥ ኢዮአስ አባቶቹ የይሁዳ ነገሥታት ኢዮሣፍጥና ኢዮራም አካዝያስም የቀደሱትን ቅዱስ ነገር፥ እርሱም የቀደሰውን፥ በእግዚአብሔርም ቤትና በንጉሡ ቤት መዛግብት የተገኘውን ወርቅ ሁሉ ወሰደ፥ ወደ ሶርያም ንጉሥ ወደ አዛሄል ላከው። እርሱም ከኢየሩሳሌም ተመለሰ።
20፤ የቀረውም የኢዮአስ ነገር፥ የሠራውም ሥራ ሁሉ፥ በይሁዳ ነገሥታት ታሪክ መጽሐፍ የተጻፈ አይደለምን?
21፤ ባሪያዎቹም ተነሥተው ዐመፁበት፥ ወደ ሲላ በሚወርደውም መንገድ በሚሎ ቤት ገደሉት። [..]፤ ባሪያዎቹም የሰምዓት ልጅ ዮዘካርና የሾሜር ልጅ ዮዛባት መቱት፥ ሞተም፤ በዳዊትም ከተማ ከአባቶቹ ጋር ቀበሩት፤ ልጁም አሜስያስ በፋንታው ነገሠ።