ምዕራፍ 4
1፤ እንዲህም ሆነ፤ ሕዝቡ ሁሉ ዮርዳኖስን ፈጽመው በተሻገሩ ጊዜ እግዚአብሔርም ኢያሱን።
2፤ ከሕዝቡ ከየነገዱ አንድ አንድ ሰው፥ አሥራ ሁለት ሰዎች ምረጥና።
3፤ በዮርዳኖስ መካከል የካህናት እግር ከቆመበት ስፍራ አሥራ ሁለት ድንጋዮች አንሡ፤ ተሸክማችሁም በዚህ ሌሊት በምታድሩበት ስፍራ አኑሩአቸው ብለህ እዘዛቸው አለው።
4፤ ኢያሱም ከየነገዱ አንድ አንድ ሰው፥ ከእስራኤል ልጆች ያዘጋጃቸውን አሥራ ሁለት ሰዎች ጠራ።
5፤ ኢያሱም አላቸው። በአምላካችሁ በእግዚአብሔር ታቦት ፊት ወደ ዮርዳኖስ መካከል እለፉ፤ ከእናንተም ሰው ሁሉ በእስራኤል ልጆች ነገድ ቍጥር በጫንቃው ላይ አንድ አንድ ድንጋይ ከዚያ ይሸከም።
6፤ ይህም በመካከላችሁ ምልክት ይሆናል፤ ልጆቻችሁም በሚመጣው ዘመን። የእነዚህ ድንጋዮች ነገር ምንድር ነው? ብለው ሲጠይቁአችሁ፥
7፤ እናንተ። በእግዚአብሔር ቃል ኪዳን ታቦት ፊት የዮርዳኖስ ውኃ ስለተቋረጠ ነው፤ ዮርዳኖስን በተሻገረ ጊዜ የዮርዳኖስ ውኃ ተቋረጠ፥ እነዚህም ድንጋዮች ለእስራኤል ልጆች ለዘላለም መታሰቢያ ይሆናሉ ትሉአቸዋላችሁ።
8፤ የእስራኤልም ልጆች ኢያሱ እንዳዘዘ አደረጉ፤ እግዚአብሔርም ኢያሱን እንደ ተናገረው በእስራኤል ነገድ ቍጥር ከዮርኖስ መካከል አሥራ ሁለት ድንጋዮች አንሥተው ወደሚያድሩበት ስፍራ ወሰዱ፥ በዚያም አኖሩአቸው።
9፤ ኢያሱም የቃል ኪዳኑን ታቦት የተሸከሙ ካህናት እግሮች በቆሙበት ስፍራ በዮርዳኖስ መካከል ሌሎችን አሥራ ሁለት ድንጋዮች ተከለ፤ እስከ ዛሬም ድረስ በዚያ አሉ።
10፤ ሙሴም ኢያሱን እንዳዘዘው ሁሉ፥ እግዚአብሔር ኢያሱን ለሕዝቡ እንዲነግር ያዘዘው ነገር ሁሉ እስኪፈጸም ድረስ ታቦቱን የተሸከሙ ካህናት በዮርዳኖስ መካከል ቆመው ነበርና፤ ሕዝቡም ፈጥነው ተሻገሩ።
11፤ ሕዝቡም ሁሉ ፈጽመው በተሻገሩ ጊዜ፥ ሕዝቡ እያዩ የእግዚአብሔር ታቦትና ካህናቱ ተሻገሩ።
12፤ ሙሴም እንዳዘዛቸው የሮቤል ልጆች፥ የጋድም ልጆች፥ የምናሴም ነገድ እኩሌታ ተሰልፈው በእስራኤል ልጆች ፊት ተሻገሩ።
13፤ አርባ ሺህ ያህል ሰዎች ጋሻና ጦራቸውን ይዘው ለሰልፍ በእግዚአብሔር ፊት ወደ ኢያሪኮ ሜዳ ተሻገሩ።
14፤ በዚያም ቀን እግዚአብሔር ኢያሱን በእስራኤል ሁሉ ፊት ከፍ አደረገው፤ ሙሴንም እንደ ፈሩ በዕድሜው ሁሉ ፈሩት።
15፤
16፤ እግዚአብሔርም ኢያሱን። የምስክሩን ታቦት የሚሸከሙትን ካህናት ከዮርዳኖስ እንዲወጡ እዘዝ ብሎ ተናገረው።
17፤ ኢያሱም ካህናትን። ከዮርዳኖስ ውጡ ብሎ አዘዛቸው።
18፤ የእግዚአብሔርንም የቃል ኪዳኑን ታቦት የተሸከሙ ካህናት ከዮርዳኖስ መካከል በወጡ ጊዜ፥ የካህናቱም እግር ጫማ ደረቅ መሬት መርገጥ በጀመረ ጊዜ፥ የዮርዳኖስ ውኃ ወደ ስፍራው ተመለሰ፥ ቀድሞም እንደ ነበረ በዳሩ ሁሉ ላይ ሄደ።
19፤ ሕዝቡም በመጀመሪያው ወር በአሥረኛው ቀን ከዮርዳኖስ ወጡ፥ በኢያሪኮም ዳርቻ በምሥራቅ በኩል በጌልገላ ሰፈሩ።
20፤ ከዮርዳኖስም ውስጥ የወሰዱአቸውን እነዚያን አሥራ ሁለቱን ድንጋዮች ኢያሱ በጌልገላ አቆማቸው።
21፤ ለእስራኤልም ልጆች እንዲህ ብሎ ተናገራቸው። በሚመጣው ዘመን ልጆቻችሁ አባቶቻቸውን። እነዚህ ድንጋዮች ምንድር ናቸው? ብለው ሲጠይቁ፥
22፤ ለልጆቻችሁ እንዲህ ብላችሁ ታስታውቃላችሁ። እስራኤል ይህን ዮርዳኖስን በደረቅ ተሻገረ፤
23፤ እስክንሻገር ድረስ አምላካችሁ የኤርትራን ባሕር ከፊታችን እንዳደረቀ እንዲሁ እስክትሻገሩ ድረስ አምላካችሁ እግዚአብሔር የዮርዳኖስን ውኃ ከፊታችሁ አደረቀ። v
24፤ ይኸውም የእግዚአብሔር እጅ ጠንካራ እንደ ሆነች የምድር አሕዛብ ሁሉ እንዲያውቁ፥ አምላካችሁንም እግዚአብሔርን ለዘላለሙ እንድትፈሩ ነው። a