መጽሐፈ ኢያሱ ወልደ ነዌ - Joshua

ምዕራፍ: 1 2 3 4 5 6 7 8 9 10 11 12 13 14 15 16 17 18 19 20 21 22 23 24


ምዕራፍ 13

1፤ ኢያሱም ሸመገለ በዕድሜም አረጀ፤ እግዚአብሔርም አለው። አንተ ሸመገልህ፥ በዕድሜህም አረጀህ፤ ያልተወረሰች እጅግ ብዙ ምድር ገና ቀርታለች፤
2፤ የቀረችውም ምድር ይህች ናት፥ የፍልስጥኤማውያንና የጌሹራውያን አገር ሁሉ፥
3፤ በግብፅ ፊት ካለው ከሺሖር ወንዝ ጀምሮ በሰሜን በኩል እስካለችው የከነዓናውያን ሆና እስከ ተቈጠረችው እስከ አቃሮን ዳርቻ ድረስ፥ የጋዛ፥ የአዛጦን፥ የአስቀሎና፥ የጌት፥ የአቃሮን፥ አምስቱ የፍልስጥኤማውያን መኳንንት፥
4፤ በደቡብም በኩል የኤዋውያን፥ የከነዓናውያን ምድር ሁሉ፥ ለሲዶናውያንም የምትሆን መዓራ እስከ አሞራውያን ዳርቻ እስከ አፌቅ ድረስ፥
5፤ የጌባላውያውንም ምድር፥ በምሥራቅም በኩል ከአርሞንዔም ተራራ በታች ካለችው በኣልጋድ ጀምሮ እስከ ሐማት መግቢያ ድረስ ያለችው ሊባኖስ ሁሉ፥
6፤ በተራራማውም አገር የሚኖሩትን ሁሉ ከሊባኖስ ጀምሮ እስከ ማሴሮን ድረስ ሲዶናውያን ሁሉ፤ እነዚህን ከእስራኤል ልጆች ፊት አባርራቸዋለሁ፤ እንዳዘዝሁህም ምድራቸውን ለእስራኤል ርስት አድርገህ አካፍላቸው።
7፤ አሁንም ይህን ምድር ለዘጠኙ ነገድ ለምናሴም ነገድ እኩሌታ ርስት አድርገህ ክፈለው።
8፤ የእግዚአብሔር ባሪያ ሙሴ እንደ ሰጣቸው ከእርሱ ከምናሴ ጋር የሮቤልና የጋድ ልጆች በምሥራቅ በኩል በዮርዳኖስ ማዶ ሙሴ የሰጣቸውን ርስታቸውን ተቀበሉ።
9፤ በአርኖን ሸለቆ ዳር ካለችው ከአሮዔር፥ በሸለቆውም መካከል ካለችው ከተማ ጀምሮ የሜድባን ሜዳ ሁሉ እስከ ዲቦን ድረስ፥
10፤ በሐሴቦንም የነገሠ የአሞራውያን ንጉሥ የሴዎን ከተሞች ሁሉ እስከ አሞን ልጆች ዳርቻ ድረስ፥
11፤ ገለዓድንም፥ የጌሹራውያንንና የማዕካታውያንን ዳርቻ ሁሉ፥ የአርሞንዔምንም ተራራ ሁሉ፥
12፤ ባሳንንም ሁሉ እስከ ሰልካ ድረስ፥ በባሳን የነበረውን በአስታሮትና በኤድራይ የነገሠውን የዐግን መንግሥት ሁሉ፤ እርሱም ከራፋይም የቀረ ነበረ፤ እነዚህንም ሙሴ መታቸው አወጣቸውም።
13፤ የእስራኤል ልጆች ግን ጌሹራውያንንና ማዕካታውያንን አላወጡም፤ እስከ ዛሬም ድረስ ጌሹርና ማዕካት በእስራኤል መካከል ይኖራሉ።
14፤ ለሌዊ ነገድ ግን ርስት አልሰጠም፤ ለእስራኤል አምላክ ለእግዚአብሔር የቀረበው በእሳት የተደረገ መሥዋዕት ርስታቸው ነው፥ እርሱ እንደ ተናገራቸው።
15፤ ሙሴም ለሮቤል ልጆች ነገድ በየወገናቸው ርስትን ሰጣቸው።
16፤ ድንበራቸውም በአርኖን ሸለቆ ዳር ካለችው ከአሮዔር ጀምሮ በሸለቆው መካከል ያለችው ከተማ፥ የሜድባ ሜዳ ሁሉ፥
17፤ ሐሴቦንም፥ በሜዳውም ያሉት ከተሞችዋ ሁሉ፥ ዲቦን፥ ባሞትበኣል፥
18፤ ቤትበኣልምዖን፥ ያሀጽ፥ ቅዴሞት፥
19፤ ሜፍዓት፥ ቂርያታይም፥ ሴባማ፥ በሸለቆውም ተራራ ያለችው ጼሬትሻሐር፥
20፤ ቤተ ፌጎር፥ ከፈስጋ ተራራ በታች ያለው ምድር፥ ቤትየሺሞት፥
21፤ የሜዳውም ከተሞች ሁሉ፥ በሐሴቦንም የነገሠው የአሞራውያን ንጉሥ የሴዎን መንግሥት ሁሉ ነበረ፤ ሙሴም እርሱንና በምድሪቱ የተቀመጡትን የሴዎንን መሳፍንት፥ የምድያምን አለቆች ኤዊን፥ ሮቆምን፥ ሱርን፥ ሑርን፥ ሪባን መታቸው።
22፤ ከገደሉአቸውም ሰዎች ጋር የእስራኤል ልጆች ምዋርተኛውን የቢዖርን ልጅ በለዓምን በሰይፍ ገደሉት።
23፤ የሮቤልም ልጆች ድንበር የዮርዳኖስ ወንዝና ዳርቻው ነበረ። የሮቤል ልጆች ርስት ከተሞቻቸውም መንደሮቻቸውም በየወገኖቻቸው ይህ ነበረ።
24፤ ሙሴም ለጋድ ነገድ ለጋድም ልጆች በየወገኖቻቸው ርስት አድርጎ ሰጣቸው።
25፤ ድንበራቸውም ኢያዜርና የገለዓድ ከተሞች ሁሉ፥ የአሞንም ልጆች ምድር እኩሌታ በረባት ፊት እስካለችው እስከ አሮዔር ድረስ፥
26፤ ከሐሴቦን ጀምሮ እስከ ራማት ምጽጴ፥ እስከ ብጦኒም ድረስ፥ ከመሃናይም ጀምሮ እስከ ዳቤር ዳርቻ ድረስ፥
27፤ በሸለቆውም ቤትሀራም፥ ቤትኒምራ፥ ሱኮት፥ ጻፎን፥ የሐሴቦን ንጉሥ የሴዎን መንግሥት ቅሬታ ነበረ። ድንበሩም ዮርዳኖስና በምሥራቅ በኩል ባለው በዮርዳኖስ ማዶ የኪኔሬት ባሕር ወዲያኛው ዳርቻ ነበር።
28፤ የጋድ ልጆች ርስት ከተሞቻቸውም መንደሮቻቸውም በየወገኖቻቸው ይህ ነበረ።
29፤ ሙሴም ለምናሴ ነገድ እኩሌታ ርስት ሰጣቸው፤ ለምናሴም ልጆች ነገድ እኩሌታ በየወገኖቻቸው ይህ ነበረ።
30፤ ድንበራቸውም ከመሃናይም ጀምሮ የባሳን ንጉሥ የዐግ መንግሥት፥ ባሳን ሁሉ፥ በባሳንም ያሉት የኢያዕር መንደሮች ሁሉ ስድሳው ከተሞች፥ የገለዓድም እኩሌታ፥
31፤ በባሳንም ያሉት የዐግ መንግሥት ከተሞች፥ አስታሮትና ኤድራይ ነበረ። እነዚህም ለምናሴ ልጅ ለማኪር ልጆች ሆኑ፤ ለማኪር ልጆች እኩሌታ በየወገኖቻቸው ይህ ነበረ።
32፤ ሙሴ በምሥራቅ በኩል በኢያሪኮ አንጻር በዮርዳኖስ ማዶ በሞዓብ ሜዳ ሳለ የከፈለው ርስት ይህ ነው።
33፤ ለሌዊ ነገድ ግን ሙሴ ርስት አልሰጠም፤ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዳላቸው ርስታቸው እርሱ ነው።