ምዕራፍ 35
1፤ እግዚአብሔርም ሙሴን በዮርዳኖስ አጠገብ በኢያሪኮ አንጻር በሞዓብ ሜዳ እንዲህ ብሎ ተናገረው።
2፤ ሌዋውያን የሚቀመጡባቸውን ከተሞች ከርስታቸው ይሰጡ ዘንድ የእስራኤልን ልጆች እዘዛቸው፤ በከተሞቹም ዙሪያ ያለውን መሰምርያ ለሌዋውያን ስጡ።
3፤ እነርሱም በከተሞቹ ውስጥ ይቀመጣሉ፤ መሰምርያቸውም ለከብቶቻቸው ለእንስሶቻቸውም ለእነርሱም ላለው ሁሉ ይሁን።
4፤ ለሌዋውያንም የምትሰጡት የከተማ መሰምርያ በከተማው ዙሪያ ከቅጥሩ ወደ ውጭ አንድ ሺህ ክንድ ይሁን።
5፤ ከከተማው ውጭ በምሥራቅ በኩል ሁለት ሺህ ክንድ፥ በደቡብ በኩል ሁለት ሺህ ክንድ፥ በምዕራብ በኩል ሁለት ሺህ ክንድ፥ በሰሜንም በኩል ሁለት ሺህ ክንድ ትከነዳላችሁ፥ ከተማውም በመካከል ይሆናል፤ ይህም የከተሞቹ መሰምርያ ይሆንላቸዋል።
6፤ ለሌዋውያንም የምትሰጡአቸው ስድስቱ የመማፀኛ ከተሞች ናቸው፤ እነርሱም ነፍሰ ገዳይ ይሸሽባቸው ዘንድ የምትሰጡአቸው ናቸው፤ ከእነዚህም ሌላ አርባ ሁለት ከተሞች ትሰጣላችሁ።
7፤ ለሌዋውያን የምትሰጡአቸው ከተሞች ሁሉ አርባ ስምንት ከተሞች ይሆናሉ፤ ከመሰምርያቸው ጋር ትሰጡአቸዋላችሁ።
8፤ ከእስራኤል ልጆች ርስት ለሌዋውያን የምትሰጡአቸውን ከተሞች እንዲሁ ስጡ፤ ከብዙዎቹ ብዙ፥ ከጥቂቶቹ ጥቂት ትወስዳላችሁ፤ እያንዳንዱ እንደ ወረሱት እንደ ርስታቸው መጠን ከከተሞቻቸው ለሌዋውያን ይሰጣሉ።
9፤ እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው።
10፤ ለእስራኤል ልጆች እንዲህ ብለህ ንገራቸው። ወደ ከነዓን ምድር ዮርዳኖስን በተሻገራችሁ ጊዜ፥
11፤ በስሕተት ነፍስ የገደለ ወደዚያ ይሸሽ ዘንድ የመማፀኛ ከተሞች እንዲሆኑላችሁ ከተሞችን ለእናንት ለዩ።
12፤ ነፍሰ ገዳዩ በማኅበሩ ፊት ለፍርድ እስኪቆም ድረስ እንዳይሞት፥ ከተሞቹም ከደም ተበቃይ የመማፀኛ ከተሞች ይሁኑላችሁ።
13፤ የምትሰጡአቸውም ስድስቱ ከተሞች የመማፀኛ ከተሞች ይሁኑላችሁ።
14፤ በዮርዳኖስ ማዶ ሦስት ከተሞች ትሰጣላችሁ፥ በከነዓንም ምድር ሦስት ከተሞች ትሰጣላችሁ፤ የመማፀኛ ከተሞች ይሆናሉ።
15፤ በስሕተት ነፍስ የገደለ ይሸሽበት ዘንድ እነዚህ ስድስት ከተሞች ለእስራኤል ልጆች በመካከላቸው ለሚቀመጡ እንግዶችና መጻተኞች መማፀኛ ይሆናሉ።
16፤ በብረት መሣርያ እስኪሞት ድረስ ቢመታው ነፍሰ ገዳይ ነው፤ ነፍሰ ገዳዩም ፈጽሞ ይገደል።
17፤ ሰውም በሚሞትበት በእጁ ባለው ድንጋይ ቢመታው የተመታውም ቢሞት፥ እርሱ ነፍሰ ገዳይ ነው፤ ነፍሰ ገዳዩም ፈጽሞ ይገደል።
18፤ ሰውም በሚሞትበት በእጁ ባለው በእንጨት መሣርያ ቢመታው የተመታውም ቢሞት፥ እርሱ ነፍሰ ገዳይ ነው፤ ነፍሰ ገዳዩም ፈጽሞ ይገደል።
19፤ ደም ተበቃዩ ራሱ ነፍሰ ገዳዩን ይግደል፤ ባገኘው ጊዜ ይግደለው።
20፤ እስኪሞት ድረስ በጥላቻ ቢደፋው፥ ወይም ሸምቆ አንዳች ነገር ቢጥልበት፥
21፤ ወይም በጥላቻ እስኪሞት ድረስ በእጁ ቢመታው፥ የመታው ፈጽሞ ይገደል፤ ነፍሰ ገዳይ ነው፤ ደም ተበቃዩ ባገኘው ጊዜ ነፍሰ ገዳዩን ይግደለው።
22፤ ነገር ግን ያለ ጥላቻ ድንገት ቢደፋው፥ ሳይሸምቅም አንዳች ነገር ቢጥልበት፥
23፤ ወይም ሳያየው እስኪሞት ድረስ ሰው የሚሞትበትን ድንጋይ ቢጥልበት፥ ጠላቱም ባይሆን፥ ክፉም ያደርግበት ዘንድ ባይሻ፥
24፤ ማኅበሩ በመቺውና በደም ተባቃዩ መካከል ፍርድን እንደዚሁ ይፍረድ፤
25፤ ማኅበሩም ነፍሰ ገዳዩን ከደም ተበቃዩ እጅ ያድነዋል፥ ማኅበሩም ወደ ሸሸበት ወደ መማፀኛ ከተማ ይመልሰዋል፤ በቅዱስ ዘይትም የተቀባው ዋነኛው ካህን እስኪሞት ድረስ በዚያ ይቀመጣል።
26፤ ነፍሰ ገዳዩ ግን ከሸሸበት ከመማፀኛው ከተማ ዳርቻ ቢወጣ፥
27፤ ደም ተበቃዩም ከመማፀኛው ከተማ ዳርቻ ውጭ ቢያገኘው፥ ደም ተበቃዩም ነፍሰ ገዳዩን ቢገድለው፥ የደም ዕዳ አይሆንበትም፤
28፤ ዋነኛው ካህን እስኪሞት ድረሰ በመማፀኛው ከተማ ውስጥ መቀመጥ ይገባው ነበርና። ዋነኛው ካህን ከሞተ በኋላ ግን ነፍሰ ገዳዩ ወደ ርስቱ ምድር ይመለሳል።
29፤ እነዚህም ነገሮች ለልጅ ልጃችሁ በማደሪያችሁ ሁሉ ሥርዓትና ፍርድ ይሁኑላችሁ።
30፤ ነፍሰ ገዳይ ሁሉ በምስክሮች አፍ ይገደላል፤ በአንድ ምስክር ግን ማናቸውንም ሰው መግደል አይገባም።
31፤ ሞት የተፈረደበትን ነፍሰ ገዳዩንም ለማዳን የነፍስ ዋጋ አትቀበሉ፤ እርሱ ፈጽሞ ይገደል።
32፤ ዋነኛው ካህን ሳይሞት ወደ ምድሩ ይመለስ ዘንድ ወደ መማፀኛው ከተማ ከሸሸው የነፍስ ዋጋ አትቀበሉ።
33፤ ደም ምድሪቱን ያረክሳታልና የምትኖሩባትን ምድር አታርክሱአት፤ በደም አፍሳሹ ደም ካልሆነ በቀር ምድሪቱ ከፈሰሰባት ደም አትነጻም።
34፤ እኔ እግዚአብሔር በእስራኤል ልጆች መካከል አድራለሁና የምትኖሩባትን በመካከልዋም የማድርባትን ምድር አታርክሱአት።