ምዕራፍ 23
1፤ በለዓምም ባላቅን። ሰባት መሠዊያ በዚህ ሥራልኝ፥ ሰባትም ወይፈን ሰባትም አውራ በግ በዚህ አዘጋጅልኝ አለው።
2፤ ባላቅም በለዓም እንደ ተናገረ አደረገ፤ ባላቅና በለዓምም በየመሠዊያው ላይ አንድ ወይፈንና አንድ አውራ በግ አሳረጉ።
3፤ በለዓምም ባላቅን። በመሥዋዕትህ ዘንድ ቆይ፥ እኔም እሄዳለሁ፤ ምናልባት እግዚአብሔር ሊገናኘኝ ይመጣል፤ እርሱም የሚገልጥልኝን እነግርሃለሁ አለው። ወደ ጉብታም ሄደ።
4፤ እግዚአብሔርም ከበለዓም ጋር ተገናኘ፤ እርሱም። ሰባት መሠዊያዎች አዘጋጀሁ፥ በየመሠዊያውም ላይ አንድ ወይፈንና አንድ አውራ በግ አሳረግሁ አለው።
5፤ እግዚአብሔርም ቃልን በበለዓም አፍ አድርጎ። ወደ ባላቅ ተመለስ፥ እንዲህም በል አለው።
6፤ ወደ እርሱም ተመለሰ፥ እነሆም፥ እርሱና የሞዓብ አለቆች ሁሉ በመሥዋዕቱ ዘንድ ቆመው ነበር።
7፤ ምሳሌውንም ይመስል ጀመር፥ እንዲህም አለ። ባላቅ ከአራም አመጣኝ፥ የሞዓብ ንጉሥ ከምሥራቅ ተራሮች፤ ና፥ ያዕቆብን ርገምልኝ፤ ና፥ እስራኤልን ተጣላልኝ ብሎ።
8፤ እግዚአብሔር ያልረገመውን እንዴት እረግማለሁ?
9፤ በአምቦች ራስ ላይ ሆኜ አየዋለሁ፥ በኮረብቶችም ላይ ሆኜ እመለከተዋለሁ፤ እነሆ፥ ብቻውን የሚቀመጥ ሕዝብ ነው፥ በአሕዛብም መካከል አይቈጠርም።
10፤ የያዕቆብን ትቢያ ማን ይቈጥራል? የእስራኤልስ እርቦ ማን ይቈጥራል? የጻድቃንን ሞት እኔ ልሙት፥ ፍጻሜዬም እንደ እርሱ ፍጻሜ ትሁን።
11፤ ባላቅም በለዓምን። ያደረግህብኝ ምንድር ነው? ጠላቶቼን ትረግምልኝ ዘንድ ጠራሁህ፤ እነሆም፥ ፈጽመህ ባረክሃቸው አለው።
12፤ እርሱም መልሶ። በውኑ እግዚአብሔር በአፌ ያደረገውን እናገር ዘንድ አልጠነቀቅምን? አለው።
13፤ ባላቅም። በዚያ ሆነህ ታያቸው ዘንድ፥ እባክህ፥ ከእኔ ጋር ወደ ሌላ ቦታ ና ዳርቻቸውንም ብቻ ታያለህ፥ ሁሉን ግን አታይም፤ በዚያም ሆነህ እነርሱን ርገምልኝ አለው።
14፤ ወደ ጾፊምም ሜዳ ወደ ፈስጋ ተራራ ራስ ላይ ወሰደው፤ ሰባትም መሠዊያዎች ሠራ፥ በየመሠዊያውም ላይ አንድ ወይፈን አንድም አውራ በግ አሳረገ።
15፤ ባላቅንም። እኔ ወደዚያ ለመገናኘት ስሄድ በዚህ በመሥዋዕትህ ዘንድ ቆይ አለው።
16፤ እግዚአብሔርም በለዓምን ተገናኘ፥ ቃልንም በአፉ አድርጎ። ወደ ባላቅ ተመለስ፥ እንዲህም በል አለው።
17፤ ወደ እርሱም መጣ፥ እነሆም፥ እርሱ ከእርሱም ጋር የሞዓብ አለቆች በመሥዋዕቱ ዘንድ ቆመው ነበር፤ ባላቅም። እግዚአብሔር የተናገረው ምንድር ነው? አለው።
18፤ ምሳሌውንም ይመስል ጀመር፥ እንዲህም አለ። ባላቅ ሆይ፥ ተነሣ፥ ስማ፤ የሴፎር ልጅ ሆይ፥ አድምጠኝ፤
19፤ ሐሰትን ይናገር ዘንድ እግዚአብሔር ሰው አይደለም፥ ይጸጸትም ዘንድ የሰው ልጅ አይደለም። እርሱ ያለውን አያደርገውምን? የተናገረውንስ አይፈጽመውምን?
20፤ እነሆ፥ ለመባረክ ትእዛዝን ተቀብያለሁ፤ እርሱ ባርኮአል፥ እመልሰውም ዘንድ አልችልም።
21፤ በያዕቆብ ላይ ክፋትን አልተመለከተም፥ በእስራኤልም ጠማምነትን አላየም፤ አምላኩ እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ነው፥ የንጉሥም እልልታ በመካከላቸው አለ።
22፤ እግዚአብሔር ከግብፅ አውጥቶአቸዋል፤ ጕልበቱ አንድ ቀንድ እንዳለው ነው።
23፤ በያዕቆብ ላይ አስማት የለም፥ በእስራኤልም ላይ ምዋርት የለም፤ በጊዜው ስለ ያዕቆብና ስለ እስራኤል። እግዚአብሔር ምን አደረገ! ይባላል።
24፤ እነሆ፥ ሕዝቡ እንደ እንስት አንበሳ ይቆማል፥ እንደ አንበሳም ይነሣል፤ ያደነውን አስኪበላ፥ የገደለውንም ደሙን እስኪጠጣ አይተኛም።
25፤ ባላቅም በለዓምን። ከቶ አትርገማቸው፥ ከቶም አትባርካቸው አለው።
26፤ በለዓምም መልሶ ባላቅን። እግዚአብሔር የተናገረውን ሁሉ አደርጋለሁ ብዬ አልተናገርሁህምን? አለው።
27፤ ባላቅም በለዓምን። ና፥ ወደ ሌላ ስፍራ እወስድሃለሁ፤ ምናልባት በዚህ ሆነህ እነርሱን ትረግምልኝ ዘንድ እግዚአብሔር ይወድዳል አለው።
28፤ ባላቅም ምድረ በዳውን ከላይ ወደሚመለከተው ወደ ፌጎር ላይ በለዓምን ወሰደው።
29፤ በለዓምም ባላቅን። በዚህ ሰባት መሠዊያዎች ሥራልኝ፥ በዚህም ሰባት ወይፈን ሰባትም አውራ በግ አዘጋጅልኝ አለው።
30፤ ባላቅም በለዓም እንዳለው አደረገ፥ በየመሠዊያውም ላይ አንድ ወይፈንና አንድ አውራ በግ አሳረገ።