የሐዋርያት ሥራ - Acts

ምዕራፍ: 1 2 3 4 5 6 7 8 9 10 11 12 13 14 15 16 17 18 19 20 21 22 23 24 25 26 27 28


ምዕራፍ 7

1 ሊቀ ካህናቱም። ይህ ነገር እንዲህ ነውን? አለው፤
2 እርሱም እንዲህ አለ። ወንድሞችና አባቶች ሆይ፥ ስሙ። የክብር አምላክ ለአባታችን ለአብርሃም በካራን ሳይቀመጥ ገና በሁለት ወንዝ መካከል ሳለ ታየና።
3 ከአገርህና ከዘመዶችህም ወጥተህ ወደማሳይህ ወደ ማንኛውም ምድር ና አለው።
4 በዚያን ጊዜ ከከለዳውያን አገር ወጥቶ በካራን ተቀመጠ። ከዚያም አባቱ ከሞተ በኋላ እናንተ ዛሬ ወደምትኖሩባት ወደዚች አገር አወጣው።
5 በዚችም የእግር ጫማ ስንኳ የሚያህል ርስት አልሰጠውም፤ ነገር ግን ልጅ ሳይኖረው ለእርሱ ከእርሱም በኋላ ለዘሩ ርስት አድርጎ ይሰጠው ዘንድ ተስፋ ሰጠው።
6 እግዚአብሔርም ዘሩ በሌላ አገር መጻተኞች እንዲሆኑ አራት መቶ ዓመትም ባሪያዎች እንዲያደርጉአቸው እንዲያስጨንቁአቸውም እንዲህ ተናገረ፤
7 ደግሞም እግዚአብሔር። እንደ ባሪያዎች በሚገዙአቸው ሕዝብ ላይ እኔ እፈርድባቸዋለሁ፥ ከዚህም በኋላ ይወጣሉ በዚህም ስፍራ ያመልኩኛል አለ።
8 የመገረዝንም ኪዳን ሰጠው፤ እንዲሁም ይስሐቅን ወለደ በስምንተኛውም ቀን ገረዘው ይስሐቅም ያዕቆብን ያዕቆብም አሥራ ሁለቱን የአባቶችን አለቆች።
9 የአባቶችም አለቆች በዮሴፍ ቀንተው ወደ ግብፅ ሸጡት፤ እግዚአብሔርም ከእርሱ ጋር ነበረ፥
10 ከመከራውም ሁሉ አወጣው፥ በግብፅ ንጉሥ በፈርዖንም ፊት ሞገስንና ጥበብን ሰጠው፥ በግብፅና በቤቱ ሁሉ ላይም ቢትወደድ አድርጎ ሾመው።
11 በግብፅና በከነዓንም አገር ሁሉ ራብና ብዙ ጭንቅ መጣ፥ አባቶቻችንም ምግብን አላገኙም።
12 ያዕቆብም በግብፅ እህል መኖሩን በሰማ ጊዜ በመጀመሪያ አባቶቻችንን ሰደዳቸው፤
13 በሁለተኛውም ዮሴፍ ለወንድሞቹ ታወቀ፥ የዮሴፍም ትውልድ በፈርዖን ዘንድ ተገለጠ።
14 ዮሴፍም አባቱን ያዕቆብንና ሰባ አምስት ነፍስ የነበረውን ቤተ ዘመድ ሁሉ ልኮ አስጠራ።
15 ያዕቆብም ወደ ግብፅ ወረደ እርሱም ሞተ አባቶቻችንም፤
16 ወደ ሴኬምም አፍልሰው አብርሃም ከሴኬም አባት ከኤሞር ልጆች በብር በገዛው መቃብር ቀበሩአቸው።
17-
18 እግዚአብሔርም ለአብርሃም የማለለት የተስፋው ዘመን ሲቀርብ፥ ዮሴፍን የማያውቀው ሌላ ንጉሥ በግብፅ ላይ እስኪነሣ ድረስ፥ ሕዝቡ እየተጨመሩ በግብፅ በዙ።
19 እርሱም ወገናችንን ተተንኵሎ ሕፃናትን በሕይወት እንዳይጠብቁ ወደ ውጭ ይጥሉ ዘንድ አድርጎ አባቶቻችንን አስጨነቀ።
20 በዚያን ጊዜ ሙሴ ተወለደ በእግዚአብሔርም ፊት ያማረ ነበር፤ በአባቱ ቤትም ሦስት ወር አደገ፤
21 በተጣለም ጊዜ የፈርዖን ልጅ አነሣችው ልጅም ይሆናት ዘንድ አሳደገችው።
22 ሙሴም የግብፆችን ጥበብ ሁሉ ተማረ፥ በቃሉና በሥራውም የበረታ ሆነ።
23 ነገር ግን አርባ ዓመት ሲሞላው ወንድሞቹን የእስራኤልን ልጆች ይጐበኝ ዘንድ በልቡ አሰበ።
24 አንዱም ሲበደል አይቶ ረዳው፥ የግብፅን ሰውም መትቶ ለተገፋው ተበቀለ።
25 ወንድሞቹም እግዚአብሔር በእጁ መዳንን እንዲሰጣቸው የሚያስተውሉ ይመስለው ነበር፥ እነርሱ ግን አላስተዋሉም።
26 በማግሥቱም እርስ በርሳቸው ሲጣሉ አገኛቸው፥ ሊያስታርቃቸውም ወዶ። ሰዎች ሆይ፥ እናንተስ ወንድማማች ናችሁ፤ ስለ ምን እርስ በርሳችሁ ትበዳደላላችሁ? አላቸው።
27 ያም ባልንጀራውን የሚበድል ግን። አንተን በእኛ ላይ ሹምና ፈራጅ እንድትሆን የሾመህ ማን ነው?
28 ወይስ ትናንትና የግብፁን ሰው እንደ ገደልኸው ልትገድለኝ ትወዳለህን? ብሎ ገፋው።
29 ሙሴም ከዚህ ነገር የተነሣ ሸሽቶ በምድያም አገር መጻተኛ ሆኖ ኖረ፤ በዚያም ሁለት ልጆች ወለደ።
30 አርባ ዓመትም ሲሞላ የጌታ መልአክ በሲና ተራራ ምድረ በዳ በቍጥቋጦ መካከል በእሳት ነበልባል ታየው።
31-
32 ሙሴም አይቶ ባየው ተደነቀ፤ ሊመለከትም ሲቀርብ የጌታ ቃል። እኔ የአባቶችህ አምላክ የአብርሃም አምላክ የይስሐቅም አምላክ የያዕቆብም አምላክ ነኝ ብሎ ወደ እርሱ መጣ። ሙሴም ተንቀጥቅጦ ሊመለከት አልደፈረም።
33 ጌታም። የቆምህባት ስፍራ የተቀደሰች ምድር ናትና የእግርህን ጫማ አውልቅ።
34 በግብፅ ያሉትን የሕዝቤን መከራ ፈጽሜ አይቼ መቃተታቸውንም ሰምቼ ላድናቸው ወረድሁ፤ አሁንም ና፥ ወደ ግብፅ እልክሃለሁ አለው።
35 ሹምና ፈራጅ እንድትሆን የሾመህ ማን ነው? ብለው የካዱትን፥ ይህን ሙሴን በቍጥቋጦው በታየው በመልአኩ እጅ እግዚአብሔር ሹምና ቤዛ አድርጎ ላከው።
36 ይህ ሰው በግብፅ ምድርና በኤርትራ ባሕር በምድረ በዳም አርባ ዓመት ድንቅና ምልክት እያደረገ አወጣቸው።
37 ይህ ሰው ለእስራኤል ልጆች። እግዚአብሔር ከወንድሞቻችሁ እንደ እኔ ያለ ነቢይ ያስነሣላችኋል፤ እርሱን ስሙት ያላቸው ሙሴ ነው።
38 ይህ ሰው በሲና ተራራ ከተናገረው መልአክና ከአባቶቻችን ጋር በምድረ በዳ በማኅበሩ ውስጥ የነበረው ነው፤ ይሰጠንም ዘንድ ሕይወት ያላቸውን ቃላት ተቀበለ፤
39 ለእርሱም አባቶቻችን ሊታዘዙት አልወደዱም፤ ነገር ግን ገፉት በልባቸውም ወደ ግብፅ ተመለሱ፤
40 አሮንንም። በፊታችን የሚሄዱ አማልክት ሥራልን፤ ይህ ከግብፅ ምድር ያወጣን ሙሴ ምን እንደ ሆነ አናውቅምና አሉት።
41 በዚያም ወራት ጥጃ አደረጉ ለጣዖቱም መሥዋዕት አቀረቡ፥ በእጃቸውም ሥራ ደስ አላቸው።
42 እግዚአብሔር ግን ዘወር አለ የሰማይንም ጭፍራ ያመልኩ ዘንድ አሳልፎ ሰጣቸው፥ በነቢያትም መጽሐፍ። እናንተ የእስራኤል ቤት፥ አርባ ዓመት በምድረ በዳ የታረደውን ከብትና መሥዋዕትን አቀረባችሁልኝን?
43 ትሰግዱላቸውም ዘንድ የሠራችኋቸውን ምስሎች እነርሱንም የሞሎክን ድንኳንና ሬምፉም የሚሉትን የአምላካችሁን ኮከብ አነሣችሁ፤ እኔም ከባቢሎን ወዲያ እሰዳችኋለሁ ተብሎ እንዲህ ተጽፎአል።
44 እንዳየው ምስል አድርጎ ይሠራት ዘንድ ሙሴን ተናግሮ እንዳዘዘው፥ የምስክር ድንኳን ከአባቶቻችን ዘንድ በምድረ በዳ ነበረች፤
45 አባቶቻችንም ደግሞ በተራ ተቀብለው እግዚአብሔር በፊታቸው ያወጣቸውን የአሕዛብን አገር በያዙት ጊዜ ከኢያሱ ጋር አገቡአት፥ እስከ ዳዊት ዘመንም ድረስ ኖረች።
46 እርሱም በእግዚአብሔር ፊት ሞገስ አግኝቶ ለያዕቆብ አምላክ ማደሪያን ያገኝ ዘንድ ለመነ።
47 ነገር ግን ሰሎሞን ቤት ሠራለት።
48-
49
50 ነገር ግን ነቢዩ። ሰማይ ዙፋኔ ነው ምድርም የእግሬ መረገጫ ናት፤ ለእኔ ምን ዓይነት ቤት ትሠራላችሁ? ይላል ጌታ፥ ወይስ የማርፍበት ስፍራ ምንድር ነው? ይህንስ ሁሉ እጄ የሠራችው አይደለምን? እንዳለ፥ ልዑል የሰው እጅ በሠራችው አይኖርም።
51 እናንተ አንገተ ደንዳኖች ልባችሁና ጆሮአችሁም ያልተገረዘ፥ እናንተ ሁልጊዜ መንፈስ ቅዱስን ትቃወማላችሁ፤ አባቶቻችሁ እንደ ተቃወሙት እናንተ ደግሞ።
52-
53 ከነቢያትስ አባቶቻችሁ ያላሳደዱት ማን ነው? የጻድቁንም መምጣት አስቀድሞ የተናገሩትን ገደሉአቸው፤ በመላእክት ሥርዓት ሕግን ተቀብላችሁ ያልጠበቃችሁት እናንተም አሁን እርሱን አሳልፋችሁ ሰጣችሁት ገደላችሁትም።
54 ይህንም በሰሙ ጊዜ በልባቸው በጣም ተቈጡ ጥርሳቸውንም አፋጩበት።
55 መንፈስ ቅዱስንም ተሞልቶ ወደ ሰማይ ትኵር ብሎ ሲመለከት የእግዚአብሔርን ክብር ኢየሱስንም በእግዚአብሔር ቀኝ ቆሞ አየና።
56 እነሆ፥ ሰማያት ተከፍተው የሰው ልጅም በእግዚአብሔር ቀኝ ቆሞ አያለሁ አለ።
57 በታላቅ ድምፅም እየጮኹ ጆሮአቸውን ደፈኑ፥ በአንድ ልብ ሆነውም ወደ እርሱ ሮጡ፥
58 ከከተማም ወደ ውጭ አውጥተው ወገሩት። ምስክሮችም ልብሳቸውን ሳውል በሚሉት በአንድ ጎበዝ እግር አጠገብ አኖሩ።
59 እስጢፋኖስም። ጌታ ኢየሱስ ሆይ፥ ነፍሴን ተቀበል ብሎ ሲጠራ ይወግሩት ነበር።
60 ተንበርክኮም። ጌታ ሆይ፥ ይህን ኃጢአት አትቍጠርባቸው ብሎ በታላቅ ድምፅ ጮኸ። ይህንም ብሎ አንቀላፋ። ሳውልም በእርሱ መገደል ተስማምቶ ነበር።