ትንቢተ ሚክያስ - Micah

ምዕራፍ: 1 2 3 4 5 6 7


ምዕራፍ 3

1፤ እንዲህም አልሁ። የያዕቆብ አለቆችና የእስራኤል ቤት ገዦች ሆይ፥ እባካችሁ ስሙኝ፤ ፍርድን ታውቁ ዘንድ አይገባችሁምን?
2፤ መልካሙን ጠልታችኋል፥ ክፉውንም ወድዳችኋል፤ ቁርበታቸውን ገፍፋችኋቸዋል፥ ሥጋቸውንም ከአጥንታቸው ለያይታችኋል፤
3፤ የሕዝቤን ሥጋ በልታችኋል፥ ቁርበታቸውንም ገፍፋችኋቸዋል፥ አጥንታቸውንም ሰብራችኋል፤ ለአፍላል እንደሚሆን ሥጋ ለድስትም እንደሚሆን ሙዳ ቈራረጣችኋቸው።
4፤ የዚያን ጊዜ ወደ እግዚአብሔር ይጮኻሉ፥ እርሱም አይሰማቸውም፤ ሥራቸውንም ክፉ አድርገዋልና በዚያን ጊዜ ፊቱን ከእነርሱ ይሰውራል።
5፤ እግዚአብሔር ሕዝቤን ስለሚያስቱ ነቢያት እንዲህ ይላል፤ በጥርሳቸው ሲነክሱ በሰላም ይሰብካሉ፤ በአፋቸው ግን አንዳች በማይሰጥ ሰው ላይ ሰልፍን ያስቡበታል።
6፤ ስለዚህ ሌሊት ይሆንባችኋል እንጂ ራእይ አይሆንላችሁም፤ ጨለማም ይሆንባችኋል እንጂ አታምዋርቱም፤ ፀሐይም በነቢያት ላይ ትገባለች፥ ቀኑም ይጠቁርባቸዋል።
7፤ ከእግዚአብሔርም ዘንድ መልስ የለምና ባለ ራእዩቹ ያፍራሉ፥ ምዋርተኞችም ይዋረዳሉ፤ ሁሉም ከንፈራቸውን ይሸፍናሉ።
8፤ እኔ ግን በደሉን ለያዕቆብ፥ ኃጢአቱንም ለእስራኤል እነግር ዘንድ በእግዚአብሔር መንፈስ ኃይልንና ፍርድን ብርታትንም ተሞልቻለሁ።
9፤ ፍርድን የምትጠሉ ቅን ነገርንም ሁሉ የምታጣምሙ እናንተ የያዕቆብ ቤት አለቆችና የእስራኤል ቤት ገዦች ሆይ፥ እባካችሁ ይህን ስሙ።
10፤ ጽዮንን በደም፥ ኢየሩሳሌምንም በኃጢአት ይሠራሉ።
11፤ አለቆችዋ በጉቦ ይፈርዳሉ፥ ካህናቶችዋም በዋጋ ያስተምራሉ፥ ነቢያቶችዋም በገንዘብ ያምዋርታሉ፤ ከዚህም ጋር። እግዚአብሔር በመካከላችን አይደለምን? ክፉ ነገር ምንም አይመጣብንም እያሉ በእግዚአብሔር ይታመናሉ።
12፤ ስለዚህ በእናንተ ምክንያት ጽዮን እንደ እርሻ ትታረሳለች፥ ኢየሩሳሌምም የድንጋይ ክምር ትሆናለች፥ የቤቱም ተራራ እንደ ዱር ከፍታ ይሆናል።